“ለውጦች በማድረግ ክለቡን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና ግልፅነት የተሞላበት አሰራር ለማምጣት እየሰራን ነው። የክለባችን ቤተሰብም ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን” አቶ ቴዎድሮስ ካሕሳይ አዲሱ የወልዋሎ ዓ/ዩ ምክትል ፕሬዝደንት
ክለቡን ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ሰለሞን ገብረፃዲቅ ህይወት ካለፈ በኃላ በሦስቱም ዓመታት የተለያዩ አመራሮች በመሾም እና በመሻር ለዓመታት የሚዘልቅ የተረጋጋ አወቃቀር መገንባት ያልቻሉት ወልዋሎዎች አሁንም ለውጦች ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በተወሰኑ የአመራር ቦታዎች ለውጥ አድርገው በተቀሩት ደግሞ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ያወጡት ቢጫዎቹ ከአሰልጣኞች ቡድን ውጪ በሌሎች ቦታዎች ላይ በርካታ ለውጦች አድርገዋል። ሶከር ኢትዮጵያም በለውጦቹ ዙርያ ከአዲሱ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ካሕሳይ ጋር ቆይታ አድርጋለች።
ስለ ተደረጉ ለውጦች
ብዙ ለውጦች እያደረግን ነው። ከዚህ በፊት በክለባችን በነበረው መዋቅር በፅህፈት ቤት እና በቦርድ መሀከል ስራ አስፈፃሚ የሚባል ነበር። በአሁኑ አወቃቀራም ግን ይህ እንዲፈርስ አድርገናል። በስራ ክፍፍሉም የተወሰኑት ወደ ፅህፈት ቤት የተወሰኑት ደግሞ ወደ ቦርድ እንዲሸጋገሩ አድርገናል። የክለቡ ፅሕፈት ቤት ከዚህ በፊት ከነበረው የስራ ድርሻ ተጨማሪ ሌሎች ስራዎችም ስለሚጠበቅበት ፅሕፈት ቤታችን የተሻለ ስራዎች እንዲሰራ የማሻሻያ ስራዎች እያደረግን ነው። በግልፅ መመዘኛዎቹ ሁሉ በሚታወቁበት መንገድ የስራ ቅጥር አውጥተናል።
የተደረጉት ለውጦች እና አስፈላጊነታቸው
የተቋማዊ አወቃቀራችን በአዲስ መልክ ነው የሰራነው። በፅሕፈት ቤት የቆዩን ግለሰቦችም ከአዲሱ የአወቃቀር አሰራር የሚሄዱ አይደሉም። በትምህርት ደረጃ እና ለክለቡ የሚመጥን ልምድ ያላቸው ግለሰቦች መቀጠር እንዳለባቸው ስላመንን ነው ወደዚህ ውሳኔ የደረስነው።
ስለ ተጫዋቾች ዝውውር እና ወቅታዊ ሁኔታ
ከለውጡ ጎን ለጎን ተጫዋቾችም በመመልመል ላይ እንገኛለን። ለዚህ እንዲረዳንም ከወልዋሎ ጋር ቅርበት ያላቸውና በእግር ኳሱ የተሻለ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የተገነባ የቴክኒክ ኮሚቴ በቦርድ በኩል አቋቁመን ወደ ስራ ገብተዋል። ከአሰልጣኙ ጋር አብረው የሚሰሩት እነዚህ ግለሰቦች የባለፈው ዓመት የቡድናችን ክፍተቶችን ለሟሟላትም ሰፊ ቅድመ ዳሰሳ አድርገው ወደ እንቅስቃሴ ገብተዋል።
የክለቡ የዓመታት ችግር የሆነው ወጥነት ያለው ቡድን የመገንባት ችግር ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው ?
በአሰልጣኞች መምጣት እና መሄድ የሚመሰረት ቡድን እንዲኖረን አንፈልግም ብለን ወስነናል። ቡድናችን የራሱ የታወቀ የአጨዋወት ባህል እንዲኖረው እና ወጥነት ያለው ቡድን እንዲኖረን በሂደት እንሰራለን። በአጭር ግዜ የሚከናወን ነገር ባይሆንም በአጨዋወት እና በታዳጊዎች ዕድገት ቢያንስ መሰረት ጥለን እናልፋለን። ለዚህ እንዲረዳንም ከክለባችን ቤተሰባዊ ቅርበት ያላቸው እና በእግርኳሱ ልምድ ያላቸው ግለሰቦችን በቴክኒክ ኮሚቴ ዓይነት አድርገን ከቴክኒካል ዳይሬክተር ጋራ በመሆን ዓመቱን ሙሉ የክለባችን ጨዋታዎች እንዲገመግሙልን ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነው።
በመጨረሻ …
በአዲስ አወቃቀር ነው ስራ የጀመርነው፤ ያደረግነው ግልፅ የቅጥር ሒደትም ከዚህ በፊት ተደርጎ አያውቅም። ይህም ከዚህ በፊት በደጋፊ በኩል ይነሳ የነበረውን የግልፅነት ጥያቄ ለመመለስ ነው። ለውጦች በማድረግ የክለቡን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና ግልፅነት የተሞላበት አሰራር ለማምጣት እየሰራን ነው። የክለባችን ቤተሰብም ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን። የደጋፊ ማህበር በአዲስ አወቃቀር ዳግም ለመገንባትም በእንቅስቃሴ ላይ ነን። ምንም እንኳን ይህ የኛ ዋነኛ ስራ ባይሆንም እኛም ግን አቅጣጫዎች በማስቀመጥ አሰራሩ ለማስተካከል በጥረት ላይ ነን።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!