የሴቶች ገፅ | የሠሚራ ከማል ወርቃማ ዘመናት

በቤተሰብ ጫና ሳትበገር የደመቀችው አማካይ ሠሚራ ከማል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

እግርኳስ መጫወቷን የሰሙት ቤተሰቦቿ አልደገፏትም ፤ በራሷ ግን እየተደበቀች ከሠፈር ጀምራ ቀስ በቀስ እስከ አህጉር ዓቀፍ ውድድሮች ድረስ የሀገሯን መለያ ለብሳ ተጫውታለች። ብዙዎች በአጨዋወቷ ተገርመው አድንቀዋታል። የመሀል ሜዳ ተጫዋቿ ሠሚራ ከማል የተወለደችው አዲስ አበባ ኮልፌ አጠና ተራ አካባቢ ነው፡፡ ለሴት ልጅ ኳስን መጫወት ከባድ በሆነበት ዘመን ከቤተሰቦቿ ተደብቃ ከወንዶች ጋር መንገድ ዳር እየተጫወች አሳልፋለች። ይሁን እንጂ በሴቶች ቡድን ውስጥ በክለብ ደረጃ መጫወትን አስባው አታውቅም ነበር። በምን ሁኔታ ወደ ሴቶች ቡድን እንደገባችም እንዲህ ታስታውሳለች ። “ከሴቶች መጫወት የምችለው እኔ ብቻ የሆንኩ ነበር የሚመስለኝ። እኛ ሠፈር ‘ኒኮላ ሜዳ’ የሚባል ሜዳ አለ። በክረምት ክለቦች ዕረፍት ላይ ሲሆኑ ተጫዋቾች እዛ ሜዳ ላይ ውድድር ያደርጋሉ። እንደአጋጣሚ የነራውዳ ዓሊ ቡድን የመክፈቻ ጨዋታ ነበረው። እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ቡድን መኖሩን አየሁ። የሠፈር ልጆች ‘ለምን እዚህ ቡድን አትገቢም ? ‘ አሉኝ እና አሰልጣኙን አናገርኩት። አስር ሰዓት ሾላ (የካ) መጥተሽ ልምምድ ስሪ ሲሉኝ እኔ ካለሁበት ኮልፌ ሩቅ በመሆኑ ሳይሳካ ቀረ። ያኔ ዘጠነኛ ክፍል ነበርኩ። ወደ አስረኛ ክፍል ስዘዋወር አብራኝ የምትማር ጓደኛዬ ጃን ሜዳ ባቢ የሚባል አሰልጣኝ የሴቶችም የወንዶችም ቡድን እንደሚይዝ ነግራኝ እዛ ሄደን ሞከርን እና የነቢኒያም (ግስላ) ቡድን ተቀላቅዬ መጫወት ጀመርኩ።”

ቤተሰቦቿ ከዕምነት አንፃር እግርኳስ እንዳትጫወት በተደጋጋሚ ቢከለክሏትም እሷ ግን ጥረቷን አላቆመችም። የጃን ሜዳውን ቡድን ተቀላቅላ ከሌሎች ወንድ እና ሴት ተጫዋቾች ጋር ሥልጠናዋን ከቀጠለች በኃላ ‘የኢትዮጵያ ሻምፒዮና’ በሚል የመጣው ውድድር ዕድገቷን አፋጠነላት። ለአዲስ አበባ ምርጥ ተመርጣ ወንጂ ላይ በነበረው የመጀመሪያ ውድድር ከተማዋን ወክላ ቀረበች፡፡ በውድድሩም በነበራት አስደናቂ ብቃት መነሻነት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምልመላ በአሰልጣኞቹ አሸናፊ በቀለ ፣ በለጥሽ ገብረማርያም እና ማስተር አዳነ አማካኝነት ይደረግ ስለነበር እሷም ይህን አጋጣሚ አግኝታ መመረጥ ቻለች፡፡ ራስን ለማስደሰት ካልሆነ በስተቀር አንድም ቀን ትልቅ ቦታ ላይ እደርሳለሁ ብላ አቅዳ ባታውቅም በፍጥነት ሀገሯን ወክላ መጫወት ቻለች፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጣ እያለ የካ ቅዱስ ሚካኤል የሚባል ቡድን ውስጥ ገብታ መጫወት የጀመረች ሲሆን ከብሔራዊ ቡድኑ መልስ ግን ኩዊንስ ኮሌጅ ወደተባለው ክለብ ገባች። “ከብሔራዊ ቡድን እንደተመለስን የኩዊንስ ኮሌጅ ባለቤት ‘እያስተማርኳቸው ደመወዝም እየከፈልኳቸው እኔ ጋር ይጫወቱ’ አለ። ከዛም ሮማሪዮ የተባለ አሰልጣኝ ቀጠረልን እና መስራት ጀመርን። ክፍለ ሀገር ያሉ ልጆች ከብሔራዊ ቡድን መልስ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው መስራት ከባድ ስለሆነባቸው አዲስ አበባ ያለን ልጆች ብቻ ነበርን ዕድሉን ልናገኝ የቻልነው። አስታውሳለሁ 15 ልጆች ነበርን ፤ ሦስት ተቀያሪ ነበረው ቡድኑ። በዚህ ቡድን ውስጥም አዲስ አበባ በሚደረግ ውድድር ላይ መሳተፍ ጀመርን።” በማለት ሠሚራ የፈጣኑን ዕድገቷን አጀማመር ታስታውሳለች።

በኩዊንስ ኮሌጅ ዋንጫን አንስታ የአንድ ዓመት ብቻ ቆይታን አድርጋ በደመወዝ መስማማት ሳይችሉ ስለቀሩ እሷ እና ሌሎች ጓደኞቿ ቡድኑን ለመልቀቅ ተገደዱ። በኩዊንስ ኮሌጅ አምስት መቶ ብር ይከፈላት የነበረችው ሠሚራም በመለያ ስጦታ ብቻ በነፃ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመራች። በምግብ ብቻ ለአንድ ዓመት በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወተች የቆየች ሲሆን በሂደት ግን ቡድኑ እየተጠናከረ በመምጣቱ የደመወዝ ክፍያን በመጀመሩ እሷም ተጠቃሚ መሆኗን በመመልከቷ ለስድስት ዓመታት በክለቡ ግልጋሎትን ከሰጠች በኃላ ከቡድን አጋሯ ሽታዬ ሲሳይ ጋር ወደ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተዘዋውራለች፡፡ በቆይታዋም የአዲስ አበባ ዲቪዚዮን ዋንጫን አግኝታለች፡፡ በዚህ ወቅትም ለኢትዮጵያ ዋናው እና ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኖች ተመርጣ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ እስከ ሚሊኒየሙ ድረስ ሀገሯን ያገለገለች ሲሆን በአንድ አጋጣሚ ወደ ግል ስራ የምትገባበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንዳሰለፈችው እንዲህ ትናገራለች። “በአዲስ አበባ ስታዲየም የኮንጎ ብሔራዊ ቡድንን ስንገጥም የምርት ገበያ ኃላፊ የነበረችው ዶክተር እሌኒ ተጋባዥ እንግዳ ነበረች። ጨዋታውን አይታ ስለነበር በሦስተኛው ቀን ቢሮ ጠርታኝ እዛው ተቀጥሬ እንድሰራ የምትፈልግ መሆኑን ነግራኝ ነበር። በወቅቱ በሴንትራል በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ውስጥ ስለነበርኩ ሳልነግረው ጥዬ መውጣት ከበደኝ።”

የሠሚራ ፈጣን ዕድገት ግን ብዙ ሳይዘልቅ ነበር ከእግርኳስ ጋር ለመለያየት ወስና የነበረው። በወቅቱ ስፖርቱን በደንብ ሳትጠግበው ሀገሯንም በሚገባ መጥቀም በምትችልበት ዕድሜዋ ያቆመችው ከኃይማኖቷ ጋር በተያያዘ ነው ቢባልም እሷ ግን ሌላም ምክንያት እንደነበራት ትናገራለች። ” በጊዜው እየከበደኝ መጣ። ቤተሰቦቼ ኃይማኖቱን አጥብቀው ከሚይዙት መሀል በመሆናቸው ስጫወትም በጣም በጫና ውስጥ ሆኜ ነበር። ‘እግርኳሱን አቁሚ ! መቀጠል ከፈለግሽ ግን የእኛ ልጅ አይደለሽም ! ‘ እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩኝ ተስፋ እየቆረጥኩኝ መጣው። ሌላው ግን በወቅቱ ወደ ለንደን ኦሊምፒክ ለማለፍ አንድ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ይቀረን ነበር። በወቅቱ በፌዴሬሽን ውስጥ የነበረው አሰራር በጣም ደስ የማይል ነበር። ሴቶች ላይ የነበረው አመለካከት መጫወት እንድቀጥል የሚያደርገኝ አልነበረም። በእሱ እና የቤተሰብ ጫናም ተጨምሮ ነው በወቅቱ ላቆም የቻልኩት እንጂ በጣም ልጅ ነበርኩ።” ትላለች። በራሷ የግል ጥረት በትልቅ ደረጃ ስሟን ማፃፍ የቻለችው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጣ እንኳን በቴሌቪዥን ስትታይ ቤተሰቦቿ እሷን ላለማየት ቴሌቪዥን ያጠፉ እንደነበረም የገለፀች ሲሆን ያንን የልጅነት ጊዜዋን በእግርኳሱ አሳልፋ በዛው አለመዝለቋ እንደሚያናድዳትም አልሸሸገችም።

ሠሚራ ትልልቅ ተጫዋቾች በነበሩበት ቡድኖች ውስጥ ተጫውታ ማሳለፏ ቢያስደስታትም በአንድ ወቅት የገጠማትን ጉዳት ግን በአሳዛኝ አጋጣሚነት አትረሳውም። “ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ናይጄሪያ ላይ ጨዋታ ነበረን። ከናይጄሪያ ጋር ጉዳት ገጥሞኝ ነበር። ህይወቴን ላጣ የምችልበት ዕድልም ነበር። ረጅም ጊዜም ራሴን አላውቅም ነበር። ያ ጊዜ ለእኔ ከባድ ነበር።” ትላለች።

ዛሬ ላይ ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ስኬታማዋ ሠሚራ ከማል ወደ ኋላ ተመልሳ ስለወርቃማ የእግርኳስ ዘመኗ ካወጋችን በኋላ በመጨረሻ ይህን ብላናለች። “ወርቃማ ጊዜያቶችን አሳልፊያለሁ። ልረሳው የማልችለው አስደሳች የእግርኳስ ህይወት ነበረኝ። ሰዎች የሚሰጡኝ አክብሮትም የተለየ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ለለንደን ኦሊምፒክ 90 ደቂቃ እየቀረን ከውድድሩ የተሰናበትንበት ጊዜ እና በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫ አራተኛ የወጣንበት ጊዜ ልዩ ትዝታዎቼ ነበሩ። በዚህ አጋጣሚ ለሴቶች እግርኳስ የለፉትን ሁሉ አመሰግናለሁ ፤ በተለይ ለአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!