Soccer Ethiopia

በቡና ወቅታዊ የዝውውር ሁኔታ እና የደጋፊዎች ቅሬታ ዙርያ ሥራ አስኪያጁ ማብራርያ ሰጥተዋል

Share

ለ5ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ላይ የነበሩ ክንውኖች እና በተጨዋቾች ዝውውር ዙርያ ክለቡ ያጋጠመውን ተግዳሮት አስመልክቶ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከ2008 ጀምሮ በየዓመቱ ሲከናወን የነበረው ይህ የቤተሰብ ሩጫ ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በህብረት መሮጥ ባይቻልም በተለየ መልኩ ለደጋፊዎች የተሰጠውን 12 ቁጥር የሚወክል ታሪካዊውን (12-12-12) ቀን በመጠቀም ባሳለፍነው ማክሰኞ በድምቀት መካሄዱ ይታወቃል።

በዚህ የቤተሰብ ሩጫ ላይ የነበረውን ሒደት እና በዕለቱ ከማልያ ጥራት ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎችን አስመልክቶ እንዲሁም የክለቡ የተጫዋቾች ዝውውር ሒደት ምን እንደሚመስል የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በክለቡ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ቢሆንም ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ይሄን መርጠን አቅርበናል።

“ማልያውን (ቲሸርቱን) በተመለከተ ከዚህ ቀደም ዓምና እና ካቻምና በነበረው የቲሸርት አቀራረብ አሰርተን የምናቀርብ ከሆነ የምናተርፈው ትርፍ አይኖርም። በተቻለ መጠን የሩጫን መርህን የሚያሳይ በማድረግ በአነስተኛ ወጪ ክለቡን አትራፊ በሚያደርግ መልኩ ማመቻቸት አለብን በሚል ከዚህ ቀደም አብሮን ከሰራው ድርጅት ጋር ሠላሳ ሺህ ማልያ እንዲያቀርብ ውል ገብተን ተስማምተናል። በተስማማነው ውል መሰረት የቲሸርቱ ጨርቅ ላይ ችግር የለውም ሆኖም ግን የስፌት፣ የልኬት (የሳይዝ) አንዱ እጅጌ ከፍ ይላል አንዱ ዝቅ ይላል የማለት በአጠቃላይ ጥሩ ያልሆነ ጥራት የሌለው ቲሸርቶች እንደቀረበ ተገንዝበናል አይተናል። በውላችን መሠረት የፈለግነውን ቲሸርት ባለማቅረቡ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን የሚወስደው ድርጅት በመሆኑ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጠን ደብዳቤ ፅፈናል። ከሚሰጠን ምላሽ የሚያሳምን ከሆነ ልንቀበለው፣ ያማያሳምን ከሆነ ደጋፊያችን ከደረሰባቸው የሞራል ውድቀት ተነስተን መውሰድ የሚገባንን እርምጃ እንወስዳለን።

ይሄም ሆኖ በሩጫው 28,095 ማልያ ሸጠን አምስት ሚሊየን አንድ መቶ ዘጠና ሺ አምስት መቶ ሰባ አምስት ብር ገቢ አግኝተናል። ከስፖንሰር ሀበሻ ቢራ ደግሞ አንድ ሚልየን ብር በድምሩ ከዚህ ሩጫ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተናል። ይህ ገቢ ደግሞ እስካሁን ከተካሄዱ የቡና ሩጫዎች ሁሉ ከፍተኛው ገቢ ነው። በዚህም የምንፈልገውን ገቢ አግኝተናል ስኬታማ ሆነናል። ሆኖም ደጋፊያችን በማልያው ደስተኛ እንዳልሆነ እናውቃለን። ለዚህም ለተፈጠረው ክፍተት በፅህፈት ቤቱ ስም ደጋፊውን ይቅርታ እጠይቃለው። ዞሮ ዞሮ ግን ክለቡ የፋይናስ አቅሙ ስለ ተደገፈ ደስተኛ ሊሆኑ ይገባል። እኛም ለእነርሱ ክብር አለን። በመጨረሻም በኢትዮጵያ ቡና ህልውና ላይ አንደራደርም የማንችል ከሆንን ለቀን እንወጣለን። አንድ ደቂቃ አንቀመጥም።” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ተከታታይነት የሌለው ቡድን መስራት ለምን አልተቻለም። የሚለው ጉዳይ መልስ ያስፈልገዋል። ለዚህም እግርኳሱ የሚመራበት ሲስተም ትክክል ካለመሆኑ የመነጨ ነው ብዬ አምናለው። የውል ዘመኑ ቢበዛ ሁለት ዓመት ቢያንስ ደግሞ አንድ ዓመት ነው። እንድያውም አንዳንድ ተጫዋቾች ከአንድ ዓመት በላይ አንፈርምም፣ ቅድሚያም የምንፈልገው ነገር አለ እያሉ ነው። ለዚህም ተጨባጭ ማስረጃ አለን። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተጫዋቾች ዝውውር ስርዓት ተከታታይነት ያለው ቡድን እንዳትሰራ እንቅፋት ሆኗል። አንድ ተጫዋች በአስራ ስድስት ዓመት ውስጥ አስራ ስድስት ክለብ እየዞረ እየተጫወተ ነው። የማልያ፣ የክለብ ፍቅር ቀርቷል። ሁለት ዓመት ይፈርምልሀል አንድ ዓመት ይጫወታል አንዱን ዓመት መታያ ያደርገዋል ይህ ነው እየሆነ ያለው። ተጫዋቾች ገንዘብ ማግኘት መጠቅም እንዳለባቸው አምናለው። ሆኖም ግን የዝውውሩ መንገድ ከሁለት ዓመት ወደ ሦስት፣ አራት፣ አምስት ከፍ ማለት አለበት። የፊፋ ህግም የሚያስቀምጠው ይሄንኑ ነው። አምስት ዓመት ታስፈርማለህ፣ አራተኛው ዓመት ውሉን ለማደስ ትሞክራለህ ከተሳካ አብሮህ ይቆያል። ካልተሳካ አምስተኛ አመቱን ጨርሶ ወይም አስቀድመህ ሸጠህ ትለያያለህ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሁልጊዜ የቦስማን ህግ ነው ያለው። ከክለብ ወደ ክለብ የሚደረግ ዝውውር የለም። ይሄን ክለቦች፣ ፌዴሬሽኑ ራሱ የተጫዋቾች ማኅበር ችግሩ እንዲስተካከል መስራት አለበት። አለበለዚያ ግን ወጥ የሆነ ቡድን መስራት አይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ በእግርኳሱ ፕሮፌሽናልነት እየሞተ ነው። አሁን አሁን ደግሞ የአንድ፣ የሁለት ዓመት ቅድሚያ ይሰጠን የሚሉ ነገሮች በስፋት እየመጡ ነው። ይሄን ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና አይችልም። ምክንያቱም ገቢ የሚያገኘው በየወሩ ስለሆነ በአጠቃላይ አሰራሩ ሙሉ ለሙሉ መስተካከል አለበት።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top