የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከዳዋ ሆቴሳ ጋር…

በዛሬው የ”ዘመናችን ከዋክብት” ገፅ ላይ ፈጣኑን አጥቂ ዳዋ ሆቴሳን እንግዳ አድርገነዋል።

በምዕራብ ጉጂ ቀርጫ ከተማ ተወልዶ ያደገው ዳዋ እንደማንኛውም ታዳጊ በልጅነቱ ኳስን አዘውትሮ ይጫወት ነበር። በተለይ ተጫዋቹ ከመኖሪያ ቤቱ ፊት ለፊት የሚገኝ የመጫወቻ ሜዳ ላይ ውሎውን ያደርግ እንደነበር ያስታውሳል። በሰፈር ውስጥ የሚገኙትን እኩዮቹን እጅግ በልጦ የሚታየው ዳዋ ራሱን በተሻለ ደረጃ የሚያሳይበትን ዕድል በትምህርት ቤቶች ውድድር አግኝቶ ወደ ትልቅነት የሚያደርገውን ጉዞ ጀመረ። በእነዚህ የትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ ተሳትፎ እያደረገም በቀጥታ በክለብ ደረጃ የመመረጡን እድል አግኝቶ ለትውልድ ሀገሩ ከተማ መጫወትን ያዘ። በነገሌ ቦረና እየተጫወተም ክለቡን ከኦሮሚያ ሊግ ወደ ብሔራዊ ሊግ የማሳደግ ሃላፊነቱን ከቡድን ጓደኞቹ ጋር ተረክቦ ግልጋሎት ሰጥቷል። ለማጠቃለያ ጨዋታዎች ድሬድዋ ያመራው ተጫዋቹም የክለቡን ህልም ለማሳካት ያለውን በሚሰጥበት ጊዜ የናሽናል ሲሚንት አሰልጣኞች እይታ ውስጥ ገብቶ ፊርማውን ለክለቡ አኖረ። በናሽናል ሲሚንት ቤት ለ2 ዓመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ መዲናዋ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞውን አደረገ። በተመሳሳይ ተጫዋቹ በፈረሰኞቹ ቤት ለ2 ዓመታት ከቆየ በኋላ አዳማ ከተማን ቀጣይ ማረፊያው በማድረግ እስከ ዘንድሮ ድረስ ለ4 ተከታታይ ዓመታት የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ሆነ። ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ እንደ አባቱ የሚያያቸውን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ተከትሎ ለሃዲያ ሆሳዕና ለመጫወት የቅድመ ስምምነት ፊርማውን አኑሯል።

ናሽናል ሲሚንት 2006 ላይ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበለት ተጫዋቹ ወዲያው በአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ እይታ ውስጥ ገብቶ ወደ ዋናው ብሔራዊ ቡድን እንዲካተት ሆነ። ከዛም በአሰልጣኙ የወጣቶች ቡድን ስብስብ ውስጥ ጉልህ ሚና ኖሮት ግልጋሎት ሰጠ። ባሬቶ ከተሰናበቱ በኋላ መንበሩን በያዙት አሰልጣኝ ዮሐንስ፣ ገብረመድህን እና አሸናፊ የመመረጥ እድል ያላገኘው ዳዋ ከቀናት በፊት ኮንትራታቸው ባበቃው አሰልጣኝ አብርሃም አማካኝነት ጥሪ ቀርቦለት ዳግም ወደ ብሄራዊ ተመልሶ ተጫውቷል።

ባለፉት 6 ዓመታት በጥሩ የእድገት ፍጥነት ላይ የሚገኘው ይህ አጥቂ ከሶከር ኢትዮጵያ ያደረገውን አዝናኝ ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የእግር ኳስ አርዓያህ ማነው?

አዳነ ግርማ እና ሳልሀዲን ሰዒድ ናቸው አርኣያዎቼ። በተለይ ደግሞ አዳነ። ከታዳጊነቴ ጀምሮ እንደ እርሱ ለመሆን እጥር ነበር።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ዳዋ ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው?

ጊዜው ከባድ ነው። ከቤት ውጪ መሆን የማይመከርበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። ይህ ቢሆንም ግን ስፖርተኛ ስለሆንኩ በተቻለኝ መጠን እንቅስቃሴዎችን እየሰራሁ ነው የምገኘው። የእኛ ስራ ያለ እንቅስቃሴ ከባድ ስለሆነ በዋናነት አካላዊ ብቃቴን መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጌ ስራዎቸን ስሰራ አሳልፋለሁ።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት?

በግሌ ጥሩ ጊዜ የነበረኝ በአዳማ ቤት ነው። በአዳማ ለ4 ዓመታት ተጫውቻለሁ። በአራቱም ዓመታት ደግሞ በግሌ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ከእኔ የሚጠበቀውን ነገር ሁሉ አድርጌያለሁ።

ዳዋ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

በልጅነቴ በቀለም ትምህርቴ ጎበዝ ነበርኩ። ኳሱን ብዬ አቆምኩት እንጂ ተጫዋች ባልሆን እገፋበት ነበር። ቤተሰቦቼም ትምህርት በደንብ እንድማር ይፈልጉ ስለነበር ትምህርቴን ቀጥዬ በትልቅ ደረጃ ሰራተኛ እሆን ነበር። ታላላቆቼም በትምህርታቸው ጥሩ ቦታ ላይ ስለሆነ ያሉት እነሱን እከተል ነበር።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች ማነው?

አብሬው ተጣምሬ መጫወት የምፈልገው ከአንድ ተጫዋች ጋር ነው። እሱም ዳዊት እስጢፋኖስ ነው። ዳዊት ጥሩ ብቃት ያለው ተጫዋች ነው። በተለይ አጨዋወቱ ለአጥቂ የሚመች ነው። ከዚህ መነሻነት ከዳዊት ጋር ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድህ ተጫዋች ይኖር ይሆን?

እውነት ለመናገር ብዙ የሚከብደኝ ተጫዋች የለም። ግን አዳማ እያለሁ አብሮኝ የሚጫወተው መናፍ ዐወል በአንፃራዊነት ይከብደኛል። ልጁም ጎበዝ ተጫዋች ነው። እና ልምምድ ላይ ትንሽ ይፈትነኛል።

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ያንተ ምርጥ ተጫዋች ማነው?

በአሁኑ ሰዓት ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ሃገራችን ላይ አሉ። በአንፃራዊነት ግን ጥሩ እድገት ካሳዩ እና ምርጥ ብቃታቸው ላይ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ሱራፌል ዳኛቸውን እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን እመርጣለሁ።

ከአሰልጣኞችስ?

ከአሰልጣኞች ውበቱ አባተ እና ገብረመድህን ኃይሌ ለእኔ ምርጥ ናቸው። በግሌ እንደውም ከሁለቱ ጋር የመስራቱን እድል ባገኝ ደስ ይለኛል።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበት አጋጣሚ መቼ ነው?

ጊዮርጊስ እያለሁ ዋንጫ ያገኘንባቸው ዓመታት ለእኔ የተደሰትኩባቸው ጊዜያት ናቸው። በተለይ በመጀመሪያ የጊዮርጊስ ዓመቴ ዋንጫውን ስናገኝ ደስ ብሎኝ ነበር።

የተከፋህበትስ ጊዜ ይኖር ይሆን?

አለ። ነገሌ እያለን ቡድናችንን ለብሔራዊ ሊግ ለማብቃት ጫፍ ደርሰን ነበር። ለማጠቃለያ ውድድርም ድሬዳዋ ሄደን ነበር። በጊዜው 4 ቢጫ ካርዶች ነበሩብኝ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ድሬዳዋ ላይ ስንጫወት ባላስፈላጊ ጥፋት ቢጫ አይቼ ከቀጣይ ጨዋታ ውጪ ሆንኩ። የሚገርመው ቀጣዩ ጨዋታችን ለዋንጫ ለማለፍ እና ወደ ብሔራዊ ሊግ ለማደግ የሚደረግ የመጨረሻ ግጥሚያ ነበር። ግን እኔ ሳልሰለፍ ቀረሁ። ቡድኑ ደግሞ በአጥቂ ቦታ አማራጭ አልነበረውም ነበር። በጨዋታውም ተሸንፈን አላማችን ሳይሳካ ቀረ። በወቅቱም በጣም በራሴ እና በቡድኔ ተከፍቼ ነበር።

በእግርኳሱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛክ ማነው?

ከተጫዋቾች ለከነዓን ማርክነህ እና ምኞት ደበበ ከአሰልጣኞች ደግሞ ለአሸናፊ በቀለ ቅርበት አለኝ። ብዙ ጊዜ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ሲያጋጥመኝ ከእነሱ ጋር ነው የምመክርበት። በተለይ ደግሞ ከምኞት ጋር እንደ ሚስጥረኛ ነን። አሸናፊንም እንደ አባቴ ነው የማየው። ጥሩ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን ጥሩ ሰውም እንድሆን ይመክረኛል።

ኳስ ተጫዋች መቼስ ገጠመኝ አይጠፋውም። ሜዳ ላይ ወይም ከሜዳ ውጪ የገጠመህ ነገር ካለ አጫውተኝ እስኪ?

ልክ ነህ አይጠፋም። ለመጀመሪያ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ለግጥሚያ ሲሸልስ አመራን። ሁላችንም ገና ታዳጊ ስለሆንን የውጪ ሃገር ጉዞ ልምድ የለንም። ሲሸልስ እንደደረስን በቀጥታ ወደ ሆቴል አመራን። ሰዓቱም ምሳ ሰዓት ስለነበር ለመመገብ ሁላችንም ተዘጋጀን። ከዛ ስሙን አሁን የማልጠቅስልክ የቡድን አጋራችን ብፌ አነሳ እና ያነሳውን ፓስታ የሚበላበት ሹካ አጣ። እንደምንም አስተናጋጇን በምልክት ጠርቶ ማንኪያ እያሳያት ብራዘር ብራዘር ያላት ነገር መቼም አልረሳውም። ሹካ በእንግሊዝኛ ምን ማለት እንደሆነ ስለማያውቅ ነው ማንቂያ እያሳየ ብራዘር ያላት።

ስለ ምግብ ካነሳክ አይቀር ዳዋ ምግብ ላይ እንዴት ነው? ጥሬ ስጋ በጣም እንደምትወድ አቃለሁ?

ስፖርተኛ ምግብ ላይ አይታማም። ያወጣውን ላብ መተካት ስላለበት በደንብ መመገብ አለበት። እኔም የምመርጠው ምግብ የለኝም። የምጠላውም ምግብ የለም። ያገኘሁትን እመገባለው። እንዳልከው ግን ለጥሬ ስጋ ልዩ ፍቅር አለኝ።

ዳዋ ጎል አግብተህ ደስታህን የምትገልፅበት መንገድ ትንሽ ለየት ያለ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ንገረን እስኪ?

በፊት በፊት እንደውም አልጨፍርም ነበር። በተለይ ማሪዮ ባሎቴሊን ስለምወደው እና ስለማደንቀው እንደሱ ጎል ካገባሁ በኋላ ዝም ነበር የምለው። አሁን አሁን ግን ትንሽ እየተለወጥኩ ነው። የሃገሬ የባህል አጨፋፈር አለ። እሱን ለማስተዋወቅም ደግሞ ጎል ሳገባ እጨፍራለሁ።

የግል ህይወትክ ምን ይመስላል?

ጎጆ መስርቻለሁ። ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነኝ። ከባለቤቴ እና ከ3 ዓመት ወንድ ልጄ ጋር በአዳማ ከተማ እየኖርን ነው።

ምን የተለየ ባህሪ አለህ?

ይሄን ያህል የተለየ ባህሪ የለኝም። ግን በዋናነት ሁለት ባህሪዎች አሉኝ። አንደኛው ቀልደኛ መሆኔ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰው ከተቀየምኩ ወይንም ካኮረፍኩ በቶሎ አለመመለሴ ነው። ሰውን እንደ አመጣጡ አስተናግዳለሁ። በተለይ የመጣው ሰው ለቀልድ ክፍት ከሆነ በደንብ እንቀላለዳለን። እኔም እየቀለድኩበት እሱም እንዲቀልድብኝ ነው የምፈልገው። ነገርግን እሱ እየቀለደብኝ እኔ ስቀልድበት የሚያኮርፍ እና የሚበሳጭ ሰው ያናደኛል። ቀልድ እስከሆነ ድረስ የሚወራው ነገር ምንም ማለት አደለም። አልያም ደግሞ እሱም ሰው ላይ መቀለድ የለበትም። ከዚህ ውጪ ግን በቀልድ የሚያኮርፈኝ ሰው በጣም ያበሳጨኛል። እስከ መጨረሻው ላላወራው ሁሉ እችላለሁ። ለቁምነገረኛም ሰው ግን ጥሩ ቁምነገረኛ ነኝ።

በመጨረሻ…?

በቅድሚያ ለስፖርት ቤተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለው። ሁላችንም የጤና ባለሙያዎችን ምክር እየሰማን ማድረግ ያለብንን ነገር እንድናደርግ አደራ እላለሁ። በመቀጠል በእግርኳስ ህይወቴ እድገት ላይ ጥሩ አሻራቸውን ያሳረፉትን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!