ሶከር ሜዲካል | ፊት ላይ የሚደርሱ ስብራቶች

አገጭ ፣ ጉንጭ ፣ ጥርስ እና የመሳሰሉት የፊት አካላት በግጭት ወቅት ጉዳት የሚደርስባቸው አካላታችን ናቸው። በዛሬው ዐምዳችን የምንመለከተው የፊት አጥንቶች ሲሰበሩ የሚደርሱ ጉዳቶችን ነው።

 

Mandibular Fracture (የአግጭ ስብራት)

የዚህ ስብራት መገለጫዋች ህመም ፣ ማበጥ ፣ መገጣጠሚያን ለማንቀሳቀስ መቸገር ፣ ለማላመጥ መቸገር፣ የአይን ጉዳት እና የጥርስ ስብራት ናቸው። በህክምና ወቅት ተያያዥነት ያላቸው ከፍተኛ ጉዳቶች ማለትም እንደ ጭንቅላት ጉዳት እና የምላስ ወደ ኋላ በመመለስ የአየር ቱቦን መዝጋት ሊኖሩ ስለሚችሉ እነዚህን በትኩረት መከታተል ይገባል። እንደዚህ ያሉት ጉዳቶች ላቅ ላሉ ችግሮች ሊዳርጉ ስለሚችሉ በሆስፒታል መታከማቸው የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ይታሰባል።

 

Maxillae Fractures (የጉንጭ አጥንት መሰበር)

እነዚህ ጉዳቶች በአብዛኛው ብቻቸውን የሚከሰቱ ሳይሆን ከተጓዳኝ የአጥንት ስብራቶች ጋር ተያያዥነት አላቸው። ከጭንቅላት ስብራት ጋርም ቁርኝነት ሲኖረው ተጫዋቾች እርስ በእርስ አልያም ከግብ ቋሚ ጋር ሲላተሙ የሚከሰት ጉዳት ነው ።

ጉዳቱን በbandage ማከም ፤ ተጓዳኝ ጉዳቶችን መመልከት ፤ የአተነፋፈስ ችግር እንዳይፈጠር መቆጣጠር እና IV fluids (RL) መስጠት ከህክምና መንገዶቹ የሚጠቀስ ነው።

የአፍንጫ ስብራት

አፍንጫ በአጠገቡ ባሉ በርካታ የደም ስሮች አማካኝነት ስብራት በሚያጋጥምበት ወቅት ደም መፍሰስም በተጓዳኝነት ይከሰታል። ከዚህ በተጨማሪ ያሉ ምልክቶች እብጠት ፣ የቆዳ ቀለም መጥቆር (ደም መቋጠር)፣ የአፍንጫ ህመም ናቸው።

የአፍንጫ መድማትን ለማቆም ጎዝ በመጠቀም ቦታውን መድፈን የተለመደ ነው። ቀዝቃዛ ነገሮችን በመጠቀም እንደዚሁ ያበጡ ቦታዎችን ለማከም ይቻላል። እነዚህ ስሜቶች ከቆዩ የውስጠኛው የአፍንጫ አጥንት ተሰብሮ ሊሆን ስለሚችል ወደ ሆስፒታል መላክ አስፈላጊ ነው። ህመምን ለመቆጣጠር ማስታገሻ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ አያጠራጥርም።

 

የጆሮ ጉዳቶች

Pinna የተባለው የውጨኛው የጆሮ ክፍል በርካታ የደም ስር ያለውና ለጉዳት የተጋለጠ ነው። ደም መቋጠር በሚስተዋልበት ወቅት በአፋጣኝ ደሙን ማስወገድ ይገባል።

የጭንቅላት አጥንት (Basal Skull Fracture) ሲሰበር በጆሮ ፈሳሽ (CSF) ሊፈስ ይችላል። በዚህን ወቅት ወደ ሆስፒታል መላክ ይገባል።

Traumatic Perforation አልያም በግጭት የተነሳ የውስጠኛው የጆሮ ክፍሎች ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። መገለጫዎቹም ለመስማት መቸገር (ጉዳቱ በደረሰበት በኩል) እና ሚዛን መሳት ሊሆኑ ይችላሉ። ስፔሻሊስትን ማማከር አስፈላጊ ሲሆን ከዚህ ጋር በተጓዳኝ ተጫዋቾች ጆሯቸውን ከእርጥበት መከላከል ይኖርባቸዋል።

 

የአይን ጉዳቶች

መገለጫቸው የተለያዩ የሆኑት የአይን ጉዳቶች እስከ አይን መታወር የሚደርስ ከፍተኛ ጉዳት ሊታይባቸው ስለሚችል በአግባቡ ማከም የግድ ይላል።

በግጭት ወቅት የአይን ሽፋሽፍት መጥቆር ይስተዋላል። እራሱን የቻለ እና የተለየ ህክምና ባይኖረውም ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳቶች በቅርበት መከታተል አስፈላጊ ነው።

አይን ጋር ተያይዞ ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርሱ ጉዳቶች የሚደርሱ ሲሆን እነዚህ ከቀላል የቆዳ መሰንጠቅ እስከ ከፍተኛ የአጥንት ጉዳት ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን ሁሉንም የአይን አካባቢ የሚደርሱ ጉዳቶችን አንድ የሚያደርጋቸው ለህይወት አስጋ እንደሆኑ ታስበው መታከማቸው ሲሆን ከእዚህም ባሻገር አቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል መላክ እና በአይን ስፔሻሊስቲ እንዲታከሙ ማድረግ ወሳኝ ነው።

ለተጨማሪ መረጃዎች በግብዓትነት የተጠቀምነውን Football Emergency Medicine Manual የተሰኘውን መፅሐፍ መመልከት ይቻላል።

ያጋሩ