ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ ዐስራ ሠባት ሜዳዎች ሊገመገሙ ነው

የ2013 የእግርኳስ የሊግ ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት 17 ሜዳዎች ከኮሮና ቫይረስ አንፃር ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ በሦስት ኮሚቴዎች ሊገመገም ነው፡፡

በ2013 የውድድር ዓመት ዳግም ሊጎቹን ለማስጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶች ሲያካሂድ የነበረ ሲሆን በተለይ ደግሞ ለውድድሩ የሚረዱ ሀሳቦችን ያዘለ ፕሮቶኮል አቅርቦ ከመንግስት አካላት ምላሽን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ውድድሩን ከማካሄዱ በፊት ግን ለዚህ ወረርሽን ጥንቃቄ ሊረዱ የሚችሉ ቅድመ ሁኔታዎች የተቀመጡ ሲሆን ከነዚህም መካከል አንዱ ተዟዙሮ ከመጫወት ይልቅ በተመረጡ ሜዳዎች ላይ ውድድሮቹን ማካሄድ ይቻል ዘንድ ፌዴሬሽኑ ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ በተዋቀሩ ሦስት ኮሚቴዎች በመታገዝ ሜዳዎችን ሊገመግም ተዘጋጅቷል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆን አስራሰባት ስታዲየሞች ለውድድሩ ይረዳሉ በሚል ተመርጠው ግምገማ እንደሚደረግባቸው የነገሩን ሲሆን ከነዚህ አስራ ሰባት ሜዳዎች ምቹ የሆኑት ተለይተው ለውድድር እንደሚቀርብም ገልፀውልናል፡፡ ለፕሪምየር ሊጉ ውድድር የተመረጡ ሜዳዎች በሊግ ካምፓኒው የሚመራ ሲሆን ሌሎች ውድድሮች ግን በፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች መሪነት ይካሄዳልም ብለዋል ሀላፊው በኮሚቴው የተካተቱትን በአጠቃላይ ስንመለከት ከፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከጤና ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የማዘውተሪያ ስፍራ እና ባለሙያዎች ከዚህም ባሻገር የሊግ ካምፓኒው አባላት በሶስቱም ኮሚቴዎች ውስጥ ተካተው ሜዳዎቹን የሚመለከቱ ይሆናል፡፡

ለሴቶች አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊግ በልዩ ሁኔታ የወንዶች ፕሪምየር ሊግ የሚደረግባቸው ሜዳዎችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የተነገረ ሲሆን የሀዋሳ እና የባህርዳር ስታዲየም ግን በፌዴሬሽኑ ለሴቶች ውድድር እንዲደረጉ አቅጣጫ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች የአዲስ አበባ ስታዲየም እና የአበበ ቢቂላን ሜዳን እንዲጠቀሙ በሚል ፌድሬሽኑ አቅጣጫ አስቀምጧል ፡፡

ለግምገማ የቀረቡ ስታዲየሞች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ለፕሪምየር ሊግ – አበባ ቢቂላ ስታዲየም (አዲስ አበባ) ፡ አዲስ አበባ ስታዲየም፣ ሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም፣ አዳማ ስታዲየም፣ ድሬዳዋ ስታዲየም ፣ ባህርዳር ስታዲየም፣ መቐለ ስታዲየም፣ ጅማ ስታዲየም

ለከፍተኛ ሊግ – ኢትዮጵያ መድን ሜዳ (አዲስ አበባ)፣ ወላይታ ሶዶ ስታዲየም፣ አበበ ቢቂላ ስታዲየም (አዲስ አበባ)፣ ወልዲያ ሼህ አላሙዲን ስታዲየም

ለአንደኛ ሊግ – ወንጂ ስታዲየም፣ ባቱ (ዝዋይ) ስታዲየም፣ ሰንዳፋ ሜዳ፣ ደብረማርቆስ ስታዲየም፣ ጎንደር ስታዲየም፣ ነቀምት ስታዲየም

አኚህ ሜዳዎች ለቅድመ ግምገማ የቀረቡ እንጂ ሙሉ በሙሉ ውድድር የሚደረግባቸው እንዳልሆኑ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ