ስፖርት ለሰላም ማኅበር በድሬዳዋ ከተማ በመገኘት ድጋፍ አድርጓል

ከተመሰረተ አንድ ዓመት ከመንፈቅ የሆነው ስፖርት ለሰላም ማኅበር በድሬደዋ ከተማ በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።

በስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች በተለይ በእግርኳሱ አካባቢ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ለማራቅ እና ሁሉም የእግርኳስ ቤተስብ ምንም አይነት ሁከት ሳይመለከት በሰላም የሚወደውን ክለብ እንዲደግፍ ለማድረግ፣ አስራ ስድስቱም የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን ስፖርቱን መነሻ በማድረግ የማቀራረብ፣ የማገናኘት ሥራ ለመስራት ታስቦ እንዲሁም ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ችግር ያጋጣማቸውን መርዳት ዓላማው አድርጎ በኢትዮጵያ ቡና እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጥምረት የተቋቋመው ይህ ማኅበር ወደ ድሬደዋ በመጓዝ ድጋፍ አድርጓል።

የማኅበሩ አንዱ ዓላማ የሆነው በጎ ተግባር ለመፈፀም አስራ ስድስት በመሆን በትናትናው ዕለት ወደ ድሬዳዋ በማቅናት በቅርቡ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቤት ንብረታቸው የፈረሰባቸውን ነዋሪዎች የቁሳቀቁስ ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ የፈረሱ ቤቶቻቸውን በአዲስ መልክ በመስራት በስራው ላይ በጉልበታቸው ተሳትፎ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለቤት መሥሪያ የሚሆን ቆርቆሮዎችና የሚስማር ድጋፍ እና ለተጎዱት ወገኖች ድጋፍ ለመስጠት ለሚጓዙት 16 የማህበሩ አባላት መጓጓዣ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰርቪስ እንዲጠቀሙ ፈቅዶላቸዋል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ለሚያደርጉት መልካም ተግባር እገዛ ማድረጉን ለማወቅ ችለናል።

በዚህ በጎ አላማ ላይ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊ ማኀበር አብረው በመሆን ተሳትፎ አድርገዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ