የሴቶች ገፅ | ድንቋ አማካይ ኤደን ሺፈራው

ከደደቢት ጋር ስኬታማ ዓመታትን ያሳለፈችው ደፋር ፣ ግልፅ እና እልኸኛ እንደሆነች የሚነገርላት የተከላካይ አማካይዋ ኤደን ሺፈራው የዛሬው የሴቶች ገፅ እንግዳችን ናት፡፡

ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ሸጎሌ አካባቢ ነው። ገና ከሦስት ዓመቷ ጀምሮ ከታላቅ ወንድሟ ቢኒያም ሺፈራው ጋር በመሆን በመኖሪያ ቤታቸው ኳስን መጫወት የጀመረች ሲሆን የእናት እና አባቷን ከቤት መውጣት እየጠበቀችም ከአብሮ አደግ ጓደኞቿ ጋር መጫወቷ አልቀረም። በሂደትም በአካባቢዋ በሚገኘው አስፋው ሜዳ ከወንድሟ እና ከጓደኞቿ ጋር መጫወትን ቀጥላ የባርሴሎናውን ሰርጂዮ ቡስኬትን ምሳሌ እያደረገች ራሷን ማብቃት ላይ ትኩረት ማድረግ መጀመሯ ዛሬ በሜዳ ላይ በሚሰጣት ተመሳሳይ ሚና ጥንካሬን ፈጥሮላታል። “በጣም ልጅ ነበርኩኝ ፤ ክለብ ያላቸው ልጆች አስፋው ሜዳ እየመጡ ይሰለጥኑ ነበር ፤ ልክ እንደ ፕሮጀክት ዓይነት። እነሱ ሲጫወቱ እኔ እያየሁ በጣም እቀና ነበር። በሂደት ግን ዕድሜዬ ወደ አስራ ሦስት ሲገባ እንደ ፕሮጀክት ተሰበሰብን ፤ አሰልጣኛችን ራሱ በጣም ልጅ ነበር። ሰብስቦን መስራት ስንጀመር ቡድን ምን እንደሆነ ማወቅ ጀመርኩኝ። አስራ አንድ ተጫዋች በአንድ ቡድን እንደሚገባም ስረዳ የቡድን ስራ መሆኑንም ስገነዘብ በደንብ የእግርሷሱ ፍቅር ገባኝ። ” ስትል ኤደን የአስፋው ሜዳ ዕድገቷን ታስታውሳለች።

ኤደን በአስፋው ሜዳ ተስፋ የሚጣልበት ብቃት ማሳየቷ ወደ ክለብ ህይወት እንድትገባ በር እንደከፈተላት ታስባለች። ይህንን ስታስረዳም “ይመስለኛል ዘይቱና ያሲን ከክፍለ ሀገር ትመጣለች ፤ ኩዊንስ ኮሌጅ ገብታ ነበር። ኩዊንስ ኮሌጅ መጨረሻ ሊያልቅ ሲል አንድ ጨዋታ እየቀረ አሰልጣኙ ሮማሪዮን ስለኔ ታናግረዋለች። ያኔ ስጫወት ሰፈር አይታኝ ነበር። እና ‘ትምጣና ትሞክር’ ስትለው እሱ አንገራገረ ፤ ዕድሜዬም ትንሽ ስለሆነ ይመስለኛል። ከዚያ መጨረሻ ላይ አንድ ሁለት ጨዋታ ሲቀረው ጊቢ ተባልኩኝና ገባሁ ከገባሁ በኃላ ትዝ ይለኛል አስራአምስት ደቂቃ ብቻ ነው የተጫወትኩት ፤ ከዚያ ቡድኑ ፈረሰ። ቡድኑ ሲፈርስ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ገባው።” ትላለች።

አማካይዋ ወደ ኢትዮጵያ ቡናን የማምራት ዕድሉ ቢኖራትም አብዛኛውን ጊዜዋን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ለማሳለፍ የተገደደች ሲሆን በ1994 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታን ሲያደርግ በሬዲዮ እየሰማች እንደነሱ ለመሆን ፍላጎቷ እያየለ መጣ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስኬታማ የነበሩትን እነአዲስ ፈለቀ ፣ ሰሚራ ከማል ፣ ረውዳ እና ቱቱ በላይን የመሳሰሉ ተጫዋቾች የሚያሳዩትን እንቅስቃሴ ተመልክታ ጥረቷን ብትቀጥልም በኢትዮጵያ ቡና ከተጠባባቂ ወንበር ያለፈ በቂ ዕድልን ማግኘት ግን አልቻለችም፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ወደ አለቤ ሾው በመቀጠልም ወደ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አምርታለች። በተለይ ወደ ሴንትራል ካመራች በኃላ በነበረው ምቹ የሥልጠና መንገድ በይበልጥ እየተሳበች በመምጣቷ እሷም የተሻለ ተጫዋች መሆን እንደምትችል እምነቷ ከፍ ብሏል። “ሴንትራል ስገባ ማንነቴን እያወኩኝ መጣሁ ፤ በእግርኳሱ ማለት ነው፡፡ ልምዱንም እያዳበርኩኝ መጣሁ። አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ነበር አሰልጣኛችን። ብሬ ብዙ ትምህርት ሰጥቶኛል። ስለ እውነት ነው የምልህ ጥሩ ነገርም አግኝቼበታለሁ። የሴንትራልም ባለቤት ጥሩ ሰው ነው ፤ ለሴቶች እግርኳስ ያለው አመለካከት። በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቀው አላልፍም።” የሚለው አስተያየቷም ለሴንትራል ቆይታዋ ያላትን ቦታ ያመለክታል።

ከሴንትራል ከለቀቀች በኃላ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርታ የመጫወት ዕድል ቢኖራትም አጭር ጊዜ ቆይታ ከብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰብ ጋር ወዳስተዋወቃት ደደቢት አምርታለች፡፡ ከ2003 ጀምራም በደደቢት ስምንት በዋንጫ የታጀቡ ጣፋጭ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ ደደቢት እስከፈረሰበት 2010 ድረስም ቡድኑን በአምበልነትም ጭምር መምራት ችላለች። “በደደቢት ብዙ ዋንጫ አንስቻለሁ። ለእኔ ማለት ቤቴ ነው፡፡ ስለ እውነት ነው እጅግ በጣም ነው የምወደው። መጨረሻ ላይ ትንሽ አለመግባባት ቢኖርም ያሳደገኝ ቡድኔ ነው እና በጣም ላመሰግነው የሚገባ ክለብ ነው። በተለይ ደግሞ አቶ ዐወልን በሚገባ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። የመጀመሪያ ለሴቶች የፊርማ ገንዘብ ያስጀመሩ ስለሆኑ እጅግ በጣም ለሴቶች እግርኳስ እዚህ ደረጃ መድረስ አሁን ቢቀዛቀዝም የሆነ ሰዓት ተስፋ እንዲኖር ካደረጉት ዋናዎቹ ሰዎች መሀከል አቶ ዐወል አንዱ ናቸው።” በማለት ረጅም የስኬት ዓመታት ያሳለፈችበት ደደቢት ዛሬም ድረስ በልቧ እንዳለ አልሸሸገችም፡፡

2002 በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቆይታዋ በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ብትመረጥም ከተመረጠች በኃላ ተቀንሳ በኃላ ላይ ስለተጠራችበት ጊዜ እንዲህ ትላለች። “ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር የተመረጥኩት። ከዚያ ግን ከተወሰነ ልምምድ በኃላ ተቀነስኩኝ። ከልቤ ያዘንኩበት ቀን ያኔ ነበር ፤ በጣም አለቀስኩኝ። በ15ኛው ቀን መልሰው ጠሩኝ ፤ ገና ለውድድሩ ሳይሄዱ ማለት ነው። ከታንዛኒያ ነበር ጨዋታው። ሲደወልልኝ በጣም ደስተኛ ነበርኩኝ። ከዛ የብሔራዊ ቡድን ህይወቴን ጀመርኩኝ” ያለችው ኤደን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቆይታዋም ከቡድን አጋሮቿ ጋር በመሆን ሀገሯን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ችላለች። ከዛም በተጨማሪ በ2005 ለኦሊምፒክ ለማለፍ ጥሩ ዕድል በነበረው እና በመጨረሻ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ተረቶ የወጣው ብሔራዊ ቡድን ውስጥም የሀገሯን መለያ ለብሳ ተጫውታ አሳልፋለች፡፡

በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኗ በክለብ ያሳካቻቸው በተለይ በደደቢት ያሳለፈችባቸው የዋንጫ ዓመታት እና ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን የተጠራችበት ወቅት ለሷ የተለዩ ቢሆኑም ሁለት ያዘነችባቸው ወቅቶች ዛሬም ድረስ ከውስጧ እንዳልወጡ ትናገራለች። “ብዙ የምትጎዳባቸው ነገሮች ይኖራሉ። እኔ ግልፅ ተናጋሪ ነኝ ፤ ያየሁትን እናገራለሁ። ይህን በማድረጌ የሚደርሱብኝ ብዙ ነገሮች አሉ። ግን ከእሱ ውጪ አዳማ ላይ አስታውሳለው የዋንጫ ጨዋታ ከባንክ ጋር እየተጫወትን እስከ ዘጠና ደቂቃ 1-0 እየመራናቸው በጭማሪ ደቂቃ እኩል ሆኑ። ከዛም በመለያ ምት አሸነፉ ፤ ያኔ በጣም ነበር ያነባሁት። ይሄ ለእኔ አሳዛኙ ቀኔ ነበር። ሌላው እኔ በእግር ኳስ የተጫዋችነት ዘመኔ በጣም ብዙ በደል እና ችግር ደርሶብኛል። ይሄ ደግሞ እኔ ግልፅ በመናገሬ ነው ፤ በተለይ ከጋዜጠኞች ጋር። በተለይ የኢቲቪ ምርጫ ላይ ጋዜጠኞች ናቸው የመረጡት ተብሎ እኔ በጣም ጥሩ ብቃት ላይ ነበርኩኝ። በተከታታይ ዓመታት ጥሩ ሆኜ ምርጫው ላይ አልተካተትኩም። በዚያን ዓመት አቋማቸው ከኔ ዝቅ ያሉ ተካተው እኔ ያልተካተትኩት ጊዜ ነበር። እና በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወትህም ነው የምትመዘነው። እና ይሄ ደግሞ ከባድ ነው። አንድ ተጫዋች መመዘን ያለበት ሜዳ ገብቶ ቡድኑን በጠቀመበት ዓመት ነው።” ይሄ አሳዝኖኛል ለወደፊቱም መቀጠል የለበትም ሞራልም ይጎዳል።” ስትል በእግር ኳሱ ያሳዘኗትን ወቅቶች በቁጭት ተናግራለች፡፡

በአለባበሷ ስታይሊስት ከሚባሉ ተጫዋቾች ተርታ የምትሰለፈው ኤደን ለአባበስ የሰጠችሁ ትኩረት እንዲሁም ደግሞ የፀጉር አቆራረጥ መንገዷ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴዋ ባሻገር ቀልብን የሚስቡ መገለጫዎቿ ናቸው፡፡ የደደቢትን መፍረስ ተከትሎ በ2011 አዲስ አበባ ከተማን ዘንድሮ ደግሞ መከላከያን ተቀላቅላ በመጫወት ላይ የምትገኘው ኤደን ከሜዳ ላይ ጉብዝናዋ እና ደፋርነቷ ባሻገር ግልፅ እና ፊት ለፊት ተናጋሪ መሆኗም ለአምበልነቷ አስተዋፅኦ እንዳለው ታምናለች። ” አምበልነት በጣም ደስ ይላል። ይሄን ያህል ከባድ አይደለም። አንድ አንድ ቃለ መጠይቅ ሰማለሁ ፤ ሲያማርሩ። እኔን ግን ያከብሩኛል እኔም ስለማከብራቸው ፤ የዘራኸውን ነው የምታጭደው። ለቡድን ጓደኞቼ ክብር አለኝ። ሁሉንም እኩል ነው የማየው። እንደ ካፒቴን መብቷ ለጎደለባት እከራከራለው። ፊት ለፊት ነው የምጋፈጠው። ዋና የክለብ አመራሮች ጋር ሁሉ ገብቼ ነው የምናገረው። ጥያቄ አቀርባለሁ ፤ እንዲፈፀም አደርጋለሁ። ለዚህም ይመስለኛል ተጫዋቹ ለእኔ አክብሮት አላቸው። አዲስ አበባ ከተማም እያለው አምበል ነበርኩኝ። እዛም እንደዛው ነበር። አመራሮቹ እንደ ደደቢት ባይሆኑም ለልጆቹ መስጠት ያለብኝን ሁሉ ሰጥቻለው።”

በእግርኳሱ ከዚህም በኃላ ጠንክሬ ሰርቼ ለብሔራዊ ቡድን ዳግም ለመጫወት እና ከሀገር ውጪ በሚገኙ ክለቦች ጭምር የመጫወት ዕቅድ አለኝ የምትለዋ ኤደን ሽፈራው በመጨረሻም በእግርኳሱ እዚህ አድርሰውኛል ያለቻቸውን እንዲህ አመስግናለች።

“በቅድሚያ ፈጣሪ እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ። ጤና እና ሰላም ከሌለህ ምንም ነገር ማድረግ አትችልም። የትኛውም ብቃት ቢኖርህ መድረስ የምትፈልገው ቦታ ያለሱ ቸርነት ያለሱ እርዳታ አይሆንም። እና እሱን ላመሰግን እወዳለሁ ፤ እመቤቴ ማርያምንም እንደዛው። ከዛ በተረፈ ከሰማይ በታች እናቴ እና አባቴን አመሰግናለሁ። ከልጅነቴ ጀምሮ ምንም ተፅዕኖ ሳያደርሱብኝ እንደልቤ እንድሆን አግዘውኛል። እንደውም የግል ትምህርት ቤት ነበር የምማረው ግን የመውጫው ሠዓት ለልምምድ ስለልተመቸኝ ካልወጣሁ ብዬ አለቀስኩ። ተቀብለውኝም የመንግሥት ትምህርት ቤት አስገቡኝና ልምምዴን በአግባቡ እንድሰራ ረድተውኛል። እጅግ በጣም ባለውለታወቼ ናቸው። በጣም ነው የምወዳቸው ፈጣሪ ዕድሜ ይስጥልኝ። ከዛ በተረፈ በአሰልጣኝነት ለእኔ ትልቅ ቦታ ያለው አሥራት አባተ ነው፡፡ ሁሉም አሰልጣኞች ለእኔ ትምህርት ቤቶቼ ናቸው፡፡ ግን ለእኔ እዚህ ቦታ መድረስ በቃ አሥራት አባተ ከፍተኛውን ቦታ ይወስዳል። ከዚያ ውጪ አንድ ዓመትም ቢሆንም የሰራነው አሰልጣኝ ፍሬው ወልደገብርኤል በሥራ የሚያምን ወንድ ሆኖ እንደ እህት የሚሰራ ሰው ነው እና እሱንም አመሰግናለሁ፡፡ ኮሎኔል ዐወልም ለሴቶች እግርኳስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ማመስገን እፈልጋለሁ። ጋዜጠኛ ዳግም ዝናቡንም ምስጋና ይገባዋል። ለሴቶች በጣም ይቆረቆራል። አንድ ክለብ ሊፈርስ ሲል እየሮጠ ሄዶ ያተርፋል። አንድ ተጫዋች ሲከፋት በኳስ መንገድ በአጠቃላይ እንደ ወንድም አይዞሽ ብሎ ከጎን ሚቆም ሰው ነው ፤ ላመሰግነው እወዳለሁ። በህይወቴ ለውጥ ለላመጡ ላልጠቀስኳቸው በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ