የሙገር የፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ እና የተሳሳተው የስልክ መልዕክት መዘዝ ትውስታ…

ለአስራ ሰባት ዓመታት በሙገር ሲሚንቶ ቆይታ የነበራቸው አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሐንስ በክለቡ ቆይታቸው በ2007 ያጋጠማቸው አይረሴ አጋጣሚ እንዴት ያስታውሱታል? 

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ተጫዋቾች ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ ኮትኩቶ ለትልቅ ደረጃ በማብቃት ከሚታወቁ ጥቂት ክለቦች አንዱ ነበር። ምንም እንኳ የተቋም ክለብ ቢሆንም በዛ ሰዓት እንደነበሩ የተቋም ክለቦች እምብዛም ገንዘብ አባካኝ እና ውጤት ተኮርም አልነበረም።

በሙገር ሲሚንቶ ታሪክ ውስጥ በርካታ አንጋፋ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ቢኖሩም ለዛሬ ትውስታውን እንዲያጋሩን የጋበዝናቸው ለአስራ ሰባት ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች ክለቡን ያገለገሉት አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሐንስ ናቸው። በ2007 ሙገር ላለመውረድ በሚወጫትበት ወቅት የፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻ መርሀግብር ላይ በተሳሳተ የስልክ መልዕክት ምክንያት ያጋጠመውን አይረሴ ትውስታ እና በሙገር የነበራቸውን ቆይታ በአጭሩ ያጋራናል።

” በሕይወቴ ከማልረሳቸው ጨዋታዎች አንዱ ነው። እኛ አዲስ አበባ ስቴድየም ላይ ከመከላከያ ጋር ነበረን ከኛ ጋር ላለመውረድ ሲፎካከር የነበረው ኤሌክትሪክ ደግሞ ከወላይታ ድቻ ነበር የሚጫወተው። ጨዋታው ከባድ ነበር ምንም እንኳ ለመከላከያ የመርሐ ግብር ሟሟያ ጨዋታ ቢሆንም በጣም ጠንክረው ነበር የቀረቡት። እኛም ያለን አማራጭ አሸንፈን የሌላው ውጤት መጠበቅ ስለነበር ለማሸነፍ ጠንክረን ነበር የተጫወትነው። ከዛ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አከባቢ እንደ ምንም ግብ አስቆጠርንባቸው።

“ከብዙ ትግል በኃላ ጨዋታው ተጠናቀቀና አሸነፍናቸው። ከቡድናችን አባላቶች አንዱ ደውሎ ኤሌክትሪክ ተሸነፈ የሚል ዜና ይዞልን መጣ። በፕሪምየር ሊጉ ቆይተናል ብለንም ደስታችን ገለፅን። ስታዲየሙ እየዞርን ከደጋፊዎቻችን ጋር ደስታችን ገለፅን ተሰብስበንም ደስታችን ገለፅን በሊጉ መቆየታችን ልዩ ደስታ ፈጥሮብን ነበር። ደስታው ግን ብዙም አልቆየም፤ ድጋሜ ኤሌክትሪክ ነው ያሸነፈው ተብሎ ደስታችን ደፈረሰ ።

“ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ምክትል አሰልጣኙ ኤሌክትሪክ ተሸንፏል ሲል ሰማሁት ከጀርባዬ ነበር፤ እሱም ስልክ ደውሎ ነው መረጃውን ያገኘው። ዞር ብዬ ስጠይቀው አዎ አለኝ በዚች ቅፅበት ነው መረጃውን ያገኘነው። በድጋሜ ሌላ ዜና ሲሰማ ደግሞ የስሜት መቀያየሮች ነበሩ ፤ በተለይም በተጫዋቾች በኩል። የታወቀ ነው የስሜት መቀያየሩ የሚፈጥረው ነገር አለ። እኔ ግን ከጨዋታው አስቀድሜ የሰማሁት ነገር ስለነበር ብዙም አዲስ አልሆነብኝም። የሚሰሙ ነገሮች ነበሩ ብዙ መረጃዎች ይወጡ ነበር። ክለባችንም የነበረው ሁኔታ አስረድቶ የሁለቱም ጨዋታ በትኩረት እንዲታይልን ጠይቀን ነበር ፤ ከዛ ግን የተጠበቀው ነገር ነው የሆነው”

ባለፈው ሳምንት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበረው እና በወቅቱ የሙገር ሲሚንቶ ተጫዋች የነበረው ደስታ ደሙ ስለ ሁኔታው ሲገልፅም እንዲህ ብሎ ነበር። “በእግር ኳስ ሕይወቴ ካጋጠሙኝ አሳዛኝ ነገሮች አንዱ ነው። በሊጉ ለመቆየት መከላከያን አሸንፈን የሌሎች ውጤት መጠበቅ ነበረብን ፤ እንደምንም መከላከያን አሸነፍን ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ግን ኤሌክትሪክ ተሸነፈ የሚል መረጃ ደርሶን ደስታችንን በልዩ መንገድ ገልፅን ስቴድየም ዞረን ከየለደጋፊዎች ደስታችንን ካጋራን በኃላ ግን መረጃው ትክክል እንዳልሆነ እና ከፕሪምየር ሊጉ እንደወረድን ተገለፀልን። ሁኔታው ከባድ ነበር። ” ብሏል።
የቀድሞው የሙገር አሰልጣኝ ከትውስታው ጎን ለጎን በክለቡ ስለነበራቸው ቀይታም አጫውተውናል።

“ከሙገር ሲሚንቶ ጋር በጣም ጥሩ ግዜ ነበረኝ፤ ከሁለተኛ ቡድን ጀምሮ ነው መስራት የጀመርኩት። በሁለተኛው ቡድን ለስምንት ዓመታት ሰርቻለው። ዋናው ቡድን ደግሞ ከ2000 እስከ 2008 ግማሽ ድረስ ወደ አስር ዓመት የሚጠጋ ቡድኑን አሰልጥኛለሁ። የሙገር ዋናው ዓላማ ከውጤት ተኮር እግር ኳስ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ከዛ ይልቅ ወጣቶችን በማሳደግ እና ጥሩ እግር ኳስ በመጫወት ይታወቅ ነበር። ሙገር መፍረሱ በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ ሙገር በመፍረሱ እግርኳሳችን ብዙ ነገር አጥቷል። ቡድኑ በወጣት ተጫዋቾች አመላመል እና በማሳደግ ላይ የነበረው ጥንካሬ ስታይ ክለቡ በመፍረሱ እግር ኳሳችን ያጣው ነገር ታያለህ። ከተለያዩ አከባቢዎች ተጫዋቾች እየመለመለ ነበር የሚያሳድገው። ወደተለያዩ የታዳጊ ውድድሮች መልማዮች እየላከ ለሀገራችን እግርኳስ ብዙ አስተዋፅኦ አድርጓል። እንደ ተጫዋቾች ሁሉ እኔን ጨምሮ ለብዙ ባለሞያዎች ዕድል ፈጥሯል። ለዚ ሁሉ ደግሞ ኢንጅነር ግዛው መመስገን አለባቸው። በብዙ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ስድስት የሚደርሱ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ነበረን።

“ፌደሬሽኑም ለሙገር ሲሚንቶ ጥበቃ ማድረግ ነበረበት ለሃገሪቱ እግር ኳስ ብዙ ነገር ያበረከተ ክለብ መፍረስ አነበረበትም። ምንም እንኳ ዋንጫ የሚበላ ባይሆንም በታዳጊዎች ላይ የሰራው ሥራ ብዙ ነው።በትንሽ በጀት የሚንቀሳቀስ ቡድን ነበር።

” አሁን ክለብ አልባ ነው ያለሁት። የማሰልጠን ጥያቄ ከቀረበልኝ ግን ዝግጁ ነኝ። በማንኛውም ደረጃ ማሰልጠን እችላለሁ። ፈላጊ ካለ እኔም ወደ ማሰልጠኑ መመለሱ እፈልጋለው” ብሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ