የዳኞች ገፅ | የዳኞች መብት ተሟጋች ሚካኤል አርዓያ

በግልፅነቱ እና ለዳኞች መብት በመታገል ይታወቃል። ያለፉትን ሠላሳ ዓመታት በዳኝነት ህይወት ያሳለፈው ፌደራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

በአስመራ ስታዲየም ኳስ በማቀበል ወደ ዳኝነቱ ገብቷል። ሜዳ ውስጥ በሚያሳየው ተውኔታዊ እንቅስቃሴ እና አዝናኝ ባህሪው በብዙዎች የስፓርት ቤተሰቦች ዘንድ ይታወቃል። በተለያዩ የስብሰባ መድረኮች ግልፅና ማለቂያ የሌላቸው ንግግሮቹ የእርሱ ሌላኛው መገለጫ ባህሪ ነው። ባለፉት ሠላሳ ዓመት ከረዳት እስከ ዋና ዳኛነት አገልግሏል። ፌዴራል ዳኛ ብቻ ሆኖ በቆየው የዳኝነት ህይወቱ ዙርያ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዳኞች ማኀበር የአመራርነት ቆይታው አስመልክቶ በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን የህይወት ልምዱን ሊያጋራን ሚካኤል አርዓያ ከኛ ጋር ሰፊ ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ!

ሌሎቹ የዚህ አምድ እንግዶችን በምጠይቀው ጥያቄ አንተን በመጠየቅ ልጀምር። ትውልድ እና እድገትህ የት ነው?

የተወለድኩት አስመራ ከተማ ነው። አስመራ ከተማ የተወለድኩ ይሁን እንጂ አብዛኛውን የዕድሜዬን ዘመን የኖርኩት በድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ ነው። እናቴ በትግራይ ክልል የምትገኝ ሲሆን ወላጅ አባቴ ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ እየኖሩ ይገኛሉ። እንግዲህ የልጅነት ህይወቴ ኳስ በመጫወት በማየት የተወሰነ ዓመት ትምህርቴን ስማር ቆይቼ ወደ ድሬደዋ እና አዲስ አበባ ትምህርቴን ተከታትዬአለው።

ሚካኤል ዳኛ እንዲሆን መነሻ ምክንያቱ ምንድነው ?

የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለው ይመስለኛል አስመራ ስታድየም በኳስ አቀባይነት አገለግል ነበር። በዛን ጊዜ ዓለም ንፀብህ የተባለ በጣም ትልቅ ዳኛ ነበር። ሁለት እግሩ ተጎድቶ የነበረው። ቀድሞ የኢትዮጵያ ዳኞች ኮሚቴ አባል ነበር። እርሱን እያየው ነው ወደ ዳኝነቱ ተገፋፍቼ የገባሁት። በኃላም በስም አውቃቸው የነበሩት ጌታቸው ገብረማርያም፣ ሰለሞን ዓለምሰገድ፣ በቀለ፣ ዓለም አሰፋን በኃለም ሲያጫውቱ ደርሻለው፤ እነርሱን እያየን ማደጋችን ወደ ዳኝነት ተስቤ ገብቻለው። እንዲሁም በተወለድኩበት አካባቢ ሠፈር ውስጥ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ልጅ ሆነን ዳኛ በመሆን አጫውት የነበረበት ሁኔታ በኃላ አድጌ ዳኛ እንድሆን መነሻ ምክንያት ሆኖኛል። በዚህ የጀመረው ዳኝነት ወደ ስልጠና ተቀይሮ ሳላስበው ወደ ዳኝነቱ ተማርኬ መግባት ችያለው።

በምን መልኩ ነው የዳኝነት ስልጠናውን ልታገኝ የቻልከው? እንድትማር ያነሳሳህ ሰው ነበር። ሄደህ እንድትመዘገብ ?

ኧረ በፍፁም የለም በራሴ ተነሳሽነት ነው ተመዝግቤ ኮርሱን እንድወስድ የሆንኩት። እንዴት መሰለህ ድሬዳዋ መጥቼ ትምህርቴን እየተማርኩ መኖር ከጀመርኩ በኃላ በአንድ አጋጣሚ አዲስ አበባ መጥቼ የዳኝነት ኮርስ እንደሚሰጥ ስሰማ በራሴ ተነሳሽነት ተመዝግቤ በ1982 የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስ መውሰድ ችያለው። ከዛም ተመልሼ ወደ ድሬደዋ ሄጄ የእግርኳስ ዳኛ በመሆን የትምህርት ቤት ውድድር ማጫወት ጀመርኩኝ። በጊዜው ከኔ ጋር ኮርሱን የወሰዱት ሰላሙ በቀለ፣ ቦጋለ አበራ ፣ ክንዴ ሀይሉ እና ሌሎቹም አብረውኝ ነው የተማሩት።

የመጀመርያ ጨዋታህን ታስታውሰዋለህ?

አዎ አስታውሰዋለው። መምሪያ አንድን ስልጠናን አዲስ አበባ ልውሰድ እንጂ የመጀመርያ ጨዋታዬን ያጫወትኩት ድሬደዋ ላይ ነበር። ለገሀሬ እና ሚካኤል ከዚራ በሚባሉ ትምህርት ቤቶችን መካከል የተደረገውን ጨዋታ ዋና ዳኛ በመሆን ያጫወትኩት። በመቀጠል የተለያዮ ጨዋታዎችን እያጫወትኩ ልምድ እያገኘው በመምርያ ደረጃ ለሰባት ዓመት ሠርቻለው።

ፌዴራል ዳኛ መቼ መሆን ቻልክ?

በ1990 ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ መካሄድ እንደሚጀምር ሲታወቅ አረባ ዳኞች እንሆናል ወደ ላይ እንድናድግ ሲደረግ በ1989 ፌደራል ዳኛ ሆኜ ወደ ላይ አደግኩ፣ ሰላሙ በቀለ፣ ዳንኤል ፍቃዱ፣ ከኔ ጋር ከነበሩት ዳኞች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

እንግዲህ ከ 1989 ጀምሮ እስከ 2010 ድረስ ሀያ አንድ ዓመት በፌደራል ዳኝነት ብቻ ነው የቆየኸው ወይስ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነሀል ?

አይ ኢንተርናሽናል ዳኛ መሆን እንዴት ተደርጎ? ኢተርናሽናል ዳኛ አልሆንኩም። ምክንያቱ ደግሞ ታሪኩ ብዙ ነው። በአጭሩ ላጫውትህ በተደጋጋሚ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን የሚሰጡ ፈተናዎችን ወስጃለሁ። አንዴ ምን ሆንኩ መሰለህ ፈተናውን ወስጄ ውጤት ሲገለፅ እኔ አራተኛ ደረጃ አግኝቼ አጠናቀኩ። በዓምላክ በጊዜው አስታውሳለው አምስተኛ ደረጃ ነበር ያገኘው። ለፊፋ የሚላከው አምስት ረዳት፣ አምስት ዋና ዳኛ ነበር። ያው በውጤቱ መሠረት አራተኛ ደረጃ ስለነበርኩ ኢንተርናሽናል ዳኛ እንደምሆን ነበር የምጠብቀው ሆኖም በፌዴሬሽኑ የነበሩ አመራሮች ሴራዎች ሰርተውብኝ እንዲሁም የወቅቱ የዳኞች ኮሚቴ አባላት ተጨምሮበት የኔን ስም ሳይልኩ ወረቀቱ ቆርጠው አውጥተው ለፊፋ ሳይልኩ አራተኛ የሆንኩት እኔን አስቀርተው ሰባተኛ የነበረውን ዳንኤልን በመላክ ህልሜን አጨናግፈውብኛል። በወቅቱ የፅህፈት ቤት ሀላፊ የነበሩትን አቶ አሸናፊን የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ለተፈፀመብኝ በደል አቤቱታ አቀረብኩኝ። በጣም ተከራከርኩኝ ምድነው ምክንያቱ ያልሆንኩበት ብዬ የዳኞች ኮሚቴንም ጠየኩኝ ሆኖም ምላሽ የሚሰጠኝ አጣው። በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግነው የማላልፈው ሰው አቶ ተካ አስፋውን ነው። ሽንጡን ገትሮ ተከራከረልኝ። ‘ምንድነው የወደቀበት ምክንያት ዝርዝር መረጃ አቅርቡ፣ ለፊፋም ደብዳቤ ላኩ። በዚህ ሰውዬ ላይ በደል ተፈፅሟል’ ብሎ ጠየቀልኝ። በአንተ ጉዳይ ዙርያ ለፊፋ ደብዳቤ ተልኳል በቅርቡ መልስ ይመጣል ጠብቅ ተባልኩኝ እሺ ብዬ ከጊዜ በኋላ መልሼ የፊፋ መልስ መጣ ወይ ስል አዎ መጥቷል። ሆኖም ግን ከፊፋ የመጣው ወረቀት ጠፍቷል ተባልኩ። ምንም ማድረግ አልቻልኩም በተፈፀመብኝ በደል አዝኜ ፈጣሪ አልፈቀደውም ብዬ ተውኩት። የኔ ወረቀት ጠፋ ተብሎ ከተነገረኝ በኋላ በሳምንቱ የምንያህል ተሾመ የቢጫ ካርድ ወረቀት ጠፋ የሚል ነገር ተሰማ (እየሳቀ…) ያው ራሱ ፌዴሬሽኑ መጨረሻ ጠፍቷል። ከዚህ ቀደምም መጀመርያ አካባቢ በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነትም ተወዳድሬ እድሜው ገናነው ብለው ያስቀሩኝ ሁኔታ ነበር። ብቻ ያሁሉ አልፏል እንጂ በደል ደርሶብኛል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባለመሆንህ ትቆጫለህ ?

ለምን አልቆጭም? በተለያዩ ጊዜያት የአካል ብቃትም ሆነ በሌሎች ፈተናዎች ጥሩ ሳልሆን በራሴ ድክመት ምክንያት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሳልሆን የወደኩበት ጥፋቶች አሉ። ማንም ላይ ምክንያት የማላቀርብበት። ሆኖም ከላይ የገለፅኩልህ ጉዳይ ግን ሁሉንም ፈተናዎች በጥሩ ሁኔታ አልፌ። ከሚፈለገው አምስት ሰው አራተኛ ሆኜ በማጠናቀቄ ኢንተርናሽናል ዳኛ መሆን ሲገባኝ ነገር ግን የተለያዩ ሸፍጥ እና ደባ ተሰርቶብኝ በመጨናገፉ በጣም ነው የምቆጨው። ግን አልናደድም፣ አልበሳጭም ለፈጣሪ ነው የምሰጠው።

ፌዳራል ዳኛ በነበርክበት ወቅት በሀገሪቱ ትልልቅ ጨዋታዎችን አጫውተሀል። ለምሳሌ እንደ ሸገር ደርቢ (ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና) ጨዋታን አጫውተሀል ?

ረዳት ዳኛ በነበርኩበት ዘመን ከአንዴም ሁለቴ ቡና እና ጊዮርጊስን አጫውቻለው። ወደ መሐል ዋና ዳኛ ስመጣ ግን በፕሪምየር ሊግ የሁለቱን ጨዋታ አላጫወትኩም። ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታን አጫውቻለው። ቡና እና ጊዮርጊስን በፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አላጫውት እንጂ ቡናም ጊዮርጊስም ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ክልልም፣ አዲስ አበባም ሲጫወቱ ተመድቤ አጫውቼ አውቃለው።

በዳኝነት ስትቆይ ሠራሁት የምትለው ስህተት ይኖራል ?

ብዙም የለም ግን አንዱ የሆንኩትን ልንገርህ። ፌደራል ዳኝ መጀመርያ እንደሆንኩ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ተሰጠኝ አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የመድን ጨዋታ ነበር። ለማጫወት ካለኝ ጉጉት አ ንዲሁም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ እንድዳኝ በመደረጌ ደስታ ስለነበረ። የጨዋታው ነገ ሊሆን እንደዛሬ ተኝቼ በህልሜ ጨዋታውን ሳራግብ አደርኩኝ። የጨዋታው ሰዓት ደርሶ ወደ ሜዳ ገብተን ከጨዋታው ውጭ ይሁን አይሁን። ብቻ ቡጉንጅ ይያዘኝ በቃ ጨዋታውን ስበጠብጥ ዋልኩ። ሳይታወቀኝ የመድኑ አጥቂ ሀሰን በሽር ጎል ሽሬዋለው። ብቻ ለኔ የመጀመርያዬ በመሆኑ ትምህርት ሆኖኛል። ከደጋፊዎች ከሚዲያ የቀረበብኝ ተቃውሞ ከዛ በኃላ እያስተካከልኩ፣ እየጠነከርኩኝ የመጣሁት።

ብዙ ጊዜ በተለያዩ መድረኮች የዳኞች መብት፣ ጥቅም እንዲጠበቅ ስትከራከር ፣ስትሟገት እና ስትቆረቆር አይሀለው። ለዳኞች የመቆርቆርህ ነገር የመጣው ከምድነው? እስቲ አጫውተኝ

ይሄ የመጣው አንደኛ ካለኝ ኃላፊነት ነው። የዳኞች እና የታዛቢዎች ማኀበር ም/ፕሬዝደንት በመሆኔ ነው። ሁለተኛ ከቀናነት የመጣ ይመስለኛል። እንዲህ የምከራከረው። ምክንያቱም ሰው ሲበድልህ እበድለዋለው ብለህ መነሳት የለብህም ለበደለህ ሰው ፈጣሪ ፍርዱን እንዲሰጠው ነው መተው ያለብህ። እኔ ያለኝ ባህሪ ዛሬ የምከራከርላችው ብዙን ጊዜ እኔን የበደሉኝ ሰዎች ናቸው። ግን በምንም ምክንያት ማንም ሰው እንዲጎዳ አልፈልግም። በማኀበሩ ኃላፊነት እስከተሰጠኝ ድረስ ማንም ሰው መጎዳት የለበትም። በምችለው ነገር ሁሉ በማድረግ መብታቸው እንዲከበር አደርጋለው። ለዚህም ነው ፍለፊት ተጋፍጬ ከኔ ራሴ ጥቀም ይልቅ የዳኞች መብት እንዲከበር ማድረግ የምወደው። ኢትዮጵያ ውሰጥ ዳኝነት ትልቅ ክብር እየተሰጠው አይደለም። ከቅርብ ጊዜያት ወደህ እርግጥ ነው ሙያው እየተከበረ ስለመሆኑ መሻሻሎች አሉ ። ሆኖም የሚቀሩ ብዙ ነገሮች አሉ።

ዳኝነትን መቼ አቆምክ ?

ዳኝነትን ካቆም ሁለት ዓመት አስቆጥሬያለው። የዳኝነት ማቆሜን ዜና እናንተ ናችሁ ቀድማቹ ለህዝቡም ያሳወቃችሁት፤ አስታውሳለው። በሠላሳ ዓመት በዳኝነት ዘመኔ እጅግ አስደሳች ጊዜን አሳልፌያለሁ። ሙያው የሚጠይቀውን ሁሉ በምችለው መጠን አድርጌ በክብር አቁሜያለው። ሁሉም ክለቦች እንደወደዱኝ በሰላም ጀምሬ በሰላም ዳኝነቴን ጨርሻለው። በዚህ አጋጣሚ ክለቦችን ተጫዋቾችንም፣ አብረውኝ የነበሩትን የሙያ ባልደረቦቼን አመሰግናለው።

ብዙ ጊዜ ዳኝነትን ያቆሙ ሰዎች ወድያውኑ ወደ ጨዋታ ታዛቢነት (ኮሚሽነር) የሚገቡበት ዕድል ይመቻቻል። አንተ ከዳኝነት ከተሰናበትክ ሁለት ዓመት ሆኖሀል። እስካሁን ለምንድነው ኮሚሽነር ያልሆንከው ?

ብዙዎቹ ዳኝነትን ሲያቆሙ የተወሰነ ስልጠና ወይም ጊዜ ተሰጥቷቸው ኮሚሽነር እየሆኑ ነው። እኔም ኮሚሽነርነት ሆኜ ለመግባት ጠይቃለው። ሆኖም በኔ ላይ ምን እየተደረገ እንደሆነ አላቅም። እንዳልገባ እየተደረገ ነው። ከእኛ ጋር ዳኝነት ያቆሙ ሦስት ሰዎች ለብቻቸው ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ኮሚሽነርነት የገቡበት ሂደት አለ። ለኔ ግን እስካሁን አልተሰጠኝም። ፈጣሪ በፈቀደው ቀን ይሆናል ብዬ ዝም ብያለው።

መቼም አንተ ሜዳ ውስጥ ካለህ ብዙ ገጠመኞች ይኖሩሀል? ምክንያትም ጨዋታውን ቀለል አድርገህ ብዙ ጊዜ አስቂኝ ተውኔታዊ ስለምታደርገው። እስቲ በዳኝነትህ ዘመን የማትረሳው አሰቂኝ ወይም አስገራሚ ገጠመኝ አለህ ?

በጣም ብዙ ገጠመኝ አለኝ የተወሰኑትን ላካፍልህ። የማን ይሁን ጨዋታው ባላሰታውሰውም እያጫወትኩ እያለሁ ጥፋት ተስርቶ ፊሽካ ከነፋሁ በኃላ ትንሽ ተጫዋቹ ግዜ የሚየባክን መስሎኝ አንተ ፈጥነህ ትከልና ምታ ሰለው ለካ አሰቀምጠህ ምታ (ጀምር) ማለት ሲገባኝ ተክለህ ምታ ሰለው ተጫዋቹ ምን እንደምል አልገባውም ዝም ብሎ ኳስዋን ይዞ ቆሞ ሲያየኝ። ለምን ጊዜ ታባክናለህ ብየ ያለ ጥፋቱ ቢጫ የሰጠሁበት ሁኔታ ሁሉ ግዜ ይከነክነኛል።

ሌላው ጋሽ ከማል ያደረጉኝን ላጫውትህ። ሀዋሳ እና ጊዮርጊስን ሀዋሳ ስታድየም እያጫወትኩኝ ነው። ጋሽ ከማል እየጮህ ይሳደባል። አላስፈላጊ ነገሮች ይናገራል ታገስኩት። በኃላ በጣም ተናድጄ እየሮጥኩ በቀይ ካርድ ላስወጣው ወደ እርሱ ልደርስ ስል ፊቱን ወደ ተጫዋቹ እያየ “የአንተ ሚኬኤሌ እግርህን ይስበር፣ እግርህ ይቆረጥ በደንብ አትጫወትም እንዴ!! እያለ ሲናገር ልሰጠው ያልኩትን ካርድ ትቼ እየሳኩኝ ተመለስኩኝ። ሜዳ ውስጥ ሚኬኤሌ የሚባል ተጫዋች እንደሌለ አውቃለው። ግን ጋሽ ከማል ከቅጣት ለማምለጥ የፈጠሩት ዘዴ አስደስቶኝ እየሳኩኝ ተመለስኩ። ጨዋታው ካለቀ በኃላ ጋሽ ከማል ሚኬኤሌ የሚባለው ተጫዋች ጥሩ ተጫወተ ወይ ብዬ ስጠይቃቸው ‘ውይ አውቀህብኛል እንዴ፤ ያላወቅሽብኝ መስሎኛል’ ተባብለን የተላለፍንበትን ወቅት መቼም አረሳውም።

አንድ የመጨረሻ ልጨምርልህ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማን ሳጫውት አንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ ያልተገባ ፍፁም ቅጣት ምት ለማግኘት ይፈልግና ይወድቃል። በዚህ ሰዓት ህጉ ዳኛን ለማሳሳት በመሞከር ቢጫ ካርድ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል ይላል። እኔ ደግሞ ቢጫ እና ቀይ ካርዱን የማስቀምጥበት የኪሴን ቦታ አቀያይሬ ነበር ለካ ቢጫ ሰጠሁት ብዬ ቀይ ካርድ አሳየሁት ተጫዋቹ ደንግጦ እንዴ ሚኬኤሌ ምን አደረኩኝ ቀይ የሰጠህኝ ይለኛል። እንዴ እኔም ግራ ተጋባው እና እጄ ላይ ያለውን ካርድ ስመለከት ቀይ ነው። ውይ ይቅርታ ብዬ ቀዩን ትቼ ወደ ቢጫ ማስጠንቀቂያ ቀየርኩት። በዚህ ሰዓት ተመልካቹ እንዴት ቀይ አሳይቶት በቢጫ ይቀይራል ብሎ ይነጋገርበት ጀመር። በንጋተው ኢንስትራክተር ሽፈራው በሚዲያ ተጠይቀው የኔ ውሳኔ ትክክል መሆኑን ሲናገር ነው የተረዱት። እነዚህ ገጠመኞቼ ናቸው።

በኢትዮጵያ ዳኞች ማኀበር በም/ፕሬዝደንት በመሆን እያገለገልክ ትገኛለህ። የአመራር ቆይታህ ምን ይመስላል?

የኢትዮጵያ ዳኞች ማኅበር በቀድሞ ጊዜ ገና ሊመሰረት በጥንስስ ውስጥ እያለ አመራር ሆኜ አልመረጥ እንጂ ማኀበሩ እንዲመሠረት የራሴን አስተዋፆኦ አድርጌአለው። የመጀመርያ የማኀበሩ ፕሬዝደንት ክንዴ ሙሴ ነበር። በስራ አስፈፃሚነት እነ ሊዲያ ታፈሰ፣ ጌታቸው የማነብርሀን እና ዘካርያስ ግርማ ሌሎችም ነበሩ። ማኀበሩን በጥሩ መሠረት ነው ገንብተውት፣ ጠንካራ ያደረጉት። እኔ አባል ነበርኩኝ በሆነ አጋጣሚ በጎደሉ አባላት ምትክ ተመርጬ ለተወሰነ ጊዜ አገልግያለው። በኃላ ላይ ሀዋሳ በተካሄደው አዲስ ምርጫ ም/ፕሬዝደንት ሆኜ ተመርጬ እስካሁ አለሁ። ያው የተወሰኑ ሰዎች ስንሯሯጥ አንዳንዶቹ ብዙም እየተንቀሳቀሱ አይደለም። ሌላው በማሕበሩ የሚታዮ ድክመት ከፌዴሬሽኑ አመራሮች በኩል አንዳንድ ነገሮች ከረው ሲመጡ የመሸሽ ነገር አለ። በተለይ እያጫወቱ የሚገኝ ዳኛች ካለ ከማኀበሩ ጎን ከመቆም ይልቅ የፌዴሬሽኑን አመራር በመፍራት ፊት ፊት ያለመጋፈጥ ነገር ይታያል። ሆኖም እኔ ብዙ ነገር ተጋፍጬ የዳኞች ጥያቄ እንዲስተካከል ለማድረግ በጠቅላላ ጉባኤ ለመደብደብ እንኳን የደረስኩበት ሁኔታ ነበር። በአጠቃላይ ይህ ማኀበር ጠናክሮ እዚህ ደረጃ የደረሰው ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት ነው። የሚገርመው እራሳቸው ባለሙያዎቹ ጭምር እኛን ያለማገዝ የማጥላላት ስራዎች ሲሰሩ ነበር። አሁን ግን እኛ እንታገል የነበረው ለእነርሱ መሆኑን እየተረዱ ሲመጡ የማገዝ፣ የመደገፍ ነገሮች መጥተዋል። አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ እኔ በግሌ ምንም ብጎዳም ሌላሰው ሲያገኝ ሲጠቀም ሳይ እኔ እንደተጠቀምኩ ነው የምቆጥረው። የዳኝነት ሙያ ተከብሮ በሁሉም ዘንድ መብታቸው እንዲከበር መደረጉን ሳይ ሁሌም ያስደስተኛል።

በሠላሳ ዓመት የዳኝነት ቆይታህ ያገኘሀቸው የምስጉን ዳኝነት ሽልማቶች አሉ ?

በጣም ይገርምሀል እስካሁን ያገኘሁት ሽልማት የለም። እዚህ ላይ አንድ ነገር መናገር እፈልጋለው። ወደፊትም መስተካከል አለበት የምለው ክፍተት አለ። በጣም የማምንበት ከድሮም ጀምሮ የምከራከርበት ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚካሄዱ የሴት፣ የወንድ የሊግ ውድድሮች አሉ። በነዚህ ውድድሮች ደግሞ ጨዋታዎቹን የሚመሩት ፌደራል እና ኢንተርናሽናል ዳኞች ናቸው። የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ግን ፌደራል ዳኞችም ኢንተርናሽናል ዳኞችም ብዛት ያላቸው ጨዋታዎችን በእኩል ብቃት ይዳኛሉ። አዳንዴም ፌደራል ዳኞቹ ከኢንተርናሽናል ዳኞች በላይ ብዙ ጠንከራ ጨዋታዎችን ሲመሩ ይታያል። ሆኖም ብዙ ጊዜ የምስጉን ዳኝነት ሽልማት ለፌደራል ዳኞች አይሰጥም። ለኢንተርናሽናል ዳኞች ብቻ ነው የሚሰጠው። የሚገርምህ ኮሚቴ እንኳን ሲመረጥ ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆነ ተብሎ ነው። ይህ አሰራር መስተካከል አለበት። ሽልማቱ ሊሰጥ የሚገባው በሜዳ ላይ ብቃት መሆን አለበት። በሀገሪቱ ደረጃ ኢንተርናሽናልም ፌደራልም ሁሉም እኩል ናቸው። ሁሉም የኢትዮጵያ ዳኞች ኢንተርናሽናል መሆን አይችሉም። በፊፋ የሚፈለገው ኮታ አስራ አራት ብቻ ነው። ይህችም ኮታ በትክክል የሚገቡባት አሉ እንዲሁም በዘመድ የምትገባባት ልትሆን ትችላለች። ፌደራል ዳኛው ዓመቱን ሙሉ በጥሩ ብቃት ካጠናቀቀ እና ነጥቡ ጥሩ የሆነ እንደሆነ በብቃት ተገምግሞ መሸለም አለበት። እኔ አንድ ጊዜ አስታውሳለው። በዶ/ር አሸብር የአመራርነት ዘመን ፌደራል ዳኛ አበጋዝ ሲሸለም ነው የማቀው። ይሄ በጣም መስተካከል አለበት። ሁሉም በኩል መታየት አለበት። ጥሩ ሆነው ዓመቱን የጨረሱትን ፌደራል ዳኞች ሞራል መጠበቅ ያስፈልጋል። የዳኞች ኮሚቴ አወቃቀር በራሱ መፈተሽ መስተካከል የሚገባው ነገር ነው። ኢንተርናሽናል የነበረ እያሉ ኮሚቴ የሚመርጡት አካሄድ መታረም አለበት። ለምሳሌ ነፍሳቸውን ይማረው እና ሽባባው እና ለማ የሚባሉ ፌደራል ዳኛ የነበሩ ከዚህ ቀደም የዳኞች ኮሚቴ ነበሩ ጠንካራ ስራ ሰርተው ያለፉ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ ፌደራል ዳኛ የነበረ ኮሚቴ አይሁን የሚል ህግ የለም።

አሁን ያለው የኢትዮጵያውያን ዳኞች ሁኔታ እንዴት ትገልፀዋለህ?

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በዳኞች ታሪክ ከድሮም ጀምሮ እውነቱን ለመናገር በርካታ ጀግና ዳኞችን አፍርታለች። አንዳንድ አላስፈላጊ ባህሪ ያላቸው ዳኞች ሊኖሩ ይችላሉ። ሰው ሲናገር የምትሰማው ነገር ሊኖር ይችላል። አይሆንም አያደርጉም ብለህ ደምድመህ የምትናገረ ነገር ላይኖር ይችላል። ፍርዱን ፈጣሪ ይስጠው። ግን ከድሮ ከእነ ጌታቸው ገ/ማርያም የሙስና ገንዘብ መመለስ የቻሉ። ከዛም በኃላ ስትመጣ እነ ኃይለ መልዓክ ተሰማ፣ ልዑልሰገድ በጋሻው እና ሌሎችም በነበሩበት ጊዜ በአፍሪካ ተፈላጊ ሆነው የሚያጫውቱበት ወቅት ነበር። አሁን ደግሞ ሊዲያ ታፈሰ፣ በዓምላክ ተሰማ ታስቀምጥ እና አሁን የመጡ ደግሞ ቴዎድሮስ ምትኩ፣ በላይ ታደሰ እና ሌሎችም ጀግኖች ዳኞች ናቸው። በካፍም፣በፊፋም እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ ሀገራት ክለቦች ሁሉ ሳይቀር በታሪክ ሰምተነው በማናቀው ሁኔታ በዓምላክ ያጫውተን የሚል ጥሪ ሲያቀርቡ ተፈላጊ እየሆኑ የመጡበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ የሆነው ብቃት ስላላቸው እና ከሙስና ጋር ስለማይገናኙ ነው። እዚህ በሀገር ውስጥ ይሰደባሉ ውጭ ሀገር ሲወጡ ግን ተከብረው ፣ ሀገራቸውን ስም ከፍ አድርገው አስጠርተው ይመለሳሉ። ሌሎችም እጅግ በጣም ጎበዝ የሆኑ በብሔራዊ ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ፣ በሴቶች ጨዋታ የሚዳኙ ሴቶችም ጭምር ከአፍሪካ ከሚመጡ ዳኞች በተሻለ ሲያጫውቱ ትመለከታለህ። አሁን በቅርብ ያጣነው ጌዲዮን የሚበል ወጣት ዳኛ ለእኔ በግሌ በትልቅ ደረጃ የምጠብቀው በጣም ጎበዝ ዳኛ ነበር። ሞት ቀደመው እንጂ። ሌሎችም ሴትም ወንድም ጥሩ ጥሩ ብዛት ያላቸው ዳኞች አሉ። ይሄን ስታይ አሁን ያለው የዳኝነት ደረጃችን ከፍተኛ መሆኑን ምስክር ነው።

የዳኞች የመተካካት ሁኔታ እንዴት ነው። አንዳንዶች የአካል ብቃታቸው እየወረደ እንኳን ለወጣቶቹ ሲለቁ አትመለከትም። በዚህ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድነው ?

ዳኝነት ዘላለም የምትኖርበት ቦታ አይደለም። ከዚህ በፊት የነበሩ ጠንካራ ዳኞች ነበሩ እነረሱ እየተኩ ሄደው በዓምላክ ጋር ደርሷል አሁን ደግሞ ቴዲ ብቅ ብሏል። በአጠቃላይ አንተርናሽናል ላይ ያሉት በላይ ታደሰ ፣ አማኑኤል ኃይለሥላሴ ፣ ሀይለኢየሱስ ባዘዘው፣ ብሩክ የማነህ ፣ ረዳቶቹም ጨምሮ ሌሎችም አሉ። እየተተካካህ ነው የምትሄደው። አሁን ያለው የፌዴሬሽን አመራር ከዚህ በፊት ከነበሩት በተሻለ የሚያዳምጡ ናቸው። በግልፅ ነው የምናገረው ዳኝነት የዘላለም የሚኖት ርስት አይደለም። እድሜህ እየገፋ ይሄዳል። ከስር ደግሞ ወጣቶች፣ በጣም ጎበዝ የሆኑ ጠንካራ ዳኞች አሉ። ጠንካራ የሆኑትን ወደ ላይ እየወጣህ እድሜያቸው የገፉት ደግሞ ወደ ታች መውረድ አለባቸው። ቃል ይገባላቸዋል ግን ሊፈፅ አልቻለም። የዳኞች ኮሚቴ ጠንክሮ በመስራት ለውጥ ማሳየት አለበት። ወጣት ዳኞች ማደግ አለባቸው።

አሁን ላሉት ወደፊት ለሚነሱት ዳኞች ምን መልዕክት ታስተላልፈለህ ?

በመጀመርያ ንፁሁ ልብ መኖር አለበት። አዳዲስ የሚወጡ የተሻሻሉ ህጎችን ማንበብ አለባቸው። ያነበቡትን ደግሞ ሜዳ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እራሳቸውን ከሱስ መጠበቅ፣ ከሁሉም ነገር ፀድቶ መገኘት፣ ደፋር መሆን እና ሁሉንም ጨዋታዎች ሳያበላልጡ በእኩል ማየት ያስገልጋል። እንዲሁም ግኑኝነት ከማን ጋር ማድረግ እንዳለባቸው መለየት አለባቸው። ጥሩ ሆነህ ስትቀርበው ጥሩ ሆኖ የማይጠጋህ ይኖራል። ስለዚህ ለሙያቸው ታማኝ ሆነው እነንዲሰሩ እመክራቸዋለው።

በዳኝነት ዘመንህ ለዳኞች መብት ስትከራከር፣ ስትሟገት ቆይተሀል። ለዚህ ሁሉ የረጅም ዓመት ላበረከትከው አስተዋፅኦ በራሳቸው ተነሳሽነት ዳኞች እና የጨዋታ ታዛቢዎች የገንዘብ እና የስጦታ የዕውቅና ሽልማት አበርክተውልሀል። ይሄ ሲሆን ምን ተሰማህ?

እኔ በዳኝነት ዘመኔ ብዙ ዓመት ኖሬያለው። እንደዛ ቀን የተደሰትኩበት ዕንባዬ መጥቶ ያለቀስኩበት ቀን የለም። ምክንያቱም ለኔ ትልቅ ክብር የተደረገልኝ ስለሆነ ነው። በጣም ነው የተደሰትኩት አክብረውኝ ይሄን ሲያደርጉ መመልከት ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። ከዚህ በኋላ እድሜ ጤና ሰጥቶኝ የበለጠ እነርሱን ለማገልገል እዳ አለብኝ ብዬ የተነሳሳሁበት ጊዜ ነበር። የሽልማቱ ማነስ እና መብዛት አይደለም። በክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ የሚገኙ ዳኞች እና የጨዋታ ታዛቢዎች በሙሉ ተሰባስበው በኢትዮጵያዊ ስሜት ተወዳጅነት አግኝተህ መሸለም በራሱ በጣም ነው ያስደሰተኝ። ሌላው በሽልማቱ ወቅት ትልቅልቅ አባቶች ስለ ለኔ ስሜቴን የሚነካኝ ንግግር ሲናገሩ በጣም ነው በደስታ እንባዬ የመጣው። ከዚህ በፊት የተበደልኳቸውን በደሎች ሽልማቱ ያስረሳኝ። በዚህ አጋጣሚ ይህን መልካም ተግባር ላደረጉልኝ በሙሉ በፈጣሪ ስም ከልብ አመሰግናለው።

ከዳኝነት ውጭ በምን የስራ ላይ ነው የተሰማራኸው?

በፌደራል ስፖርት ኮሚሽን በተለያዩ የሥራ መደቦች ሥሰራ ቆይቻለው። በስራዬም በጣም ደስተኛ ነኝ። አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተመድቤ በጋራ በስፖርታዊ ጨዋነት የምሰራው ስራ ቆይቻለው።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል ?

የቤተሰብ ህይወቴ እኔ አባት እና እናት አሉኝ። ሁሉም ሰው የሚመክረኝ ነው። ወደ ትዳር የገባሁበት ነገር የለም። እኔ በግልፅ ነው የምናገረው የኮሮና በሽታ ሲመጣ ብቸኝነቴን ያወኩት አሁን ነው። በችግር ሰዓት አጠገብህ ሰው እንዲኖር ትፈልጋለህ ትንሽ ብቸኝነቱ እየተሰማኝ ነው። አሁን ፈጣሪ ከፈቀደ ወደ ትዳር የምገባበት ይሆናል።

በመጨረሻ…

ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ በመጀመርያ ሚዲያዎችን ነው። ለዳኞች ዕድገት የሚዲያዎች አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነበር። የስፖርት ቤተሰቡ፣ ደጋፊዎች ማመስገን እፈልጋለው። ክለቦች መመስገን አለባቸው ለዳኞች ለሚያደርጉት ድጋፍ። ስፖርት የሰላም የወንድማማችነት፣ የፍቅር ፣ የአንድነት መገለጫ ነው። ማንኛውም በስፖርት ውስጥ ያለ ባለሙያ እራሱን ከፖለቲካ ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት ነፃ ሆኖ ሙያና ሙያውን ብቻ አስቦ ማገልገል አለበት። ከማንኛውም ነገር ነፃ ሆኖ ማገልገል ይጠብቅበታል። እኛ ስፖርቱን በሙያ መምራት እንጂ ሌላ ነገር ውስጥ መግባት የለብንም። የስፖርት መርሁ በኦሊምፒክ ስፖርትም ቢሆን ከማንኛውም ነገር የፀዳ መሆኑን እንዳለበት የሚናገረው። ስለዚህ ሁላችንም በአንድነት ሆነን ስፖርቱን ማሳደግ አለብን እላለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ