የደጋፊዎች ገፅ | ቆይታ ከወልቂጤ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ጋር

ወልቂጤ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲሳተፍ ካስቻሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የወልቂጤ ደጋፊዎች ማኀበር ፕሬዝደንት ካሚል ጀማል የደጋፊዎች ገፅ የዕለቱ እንግዳችን ነው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያ ድግሪ አለው። ተማሪ በነበረበትም ዘመን የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ማኀበር ም/ፕሬዝደንት በመሆን አገልግሏል። ከአስር ዓመት በላይ የማርሻል ስፖርት አሰልጣኝ በመሆን ከመስራቱም ባሻገር የተለያዩ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያዎችን  በግሉ በመክፈት የተማረውን ሙያ ወደ ትውልዱ ለማሻገር ሲሰራ ቆይቷል። ራሱን ከተለያዩ የስፖርት ሙያዎች ጋር አቆራኝቶ መኖር ከጀመረ ሰነባብቷል። በእግርኳስም የአሰልጣኝነት ኮርስ ከመውሰድ ጀምሮ እስከ ፌደራል ዳኝነት መዝለቅም ችሏል። የዘመናት ህልሙ የሆነውን ዓላማ ለማሳካት ኑሮውን ጠቅልሎ በትውልድ ከተማው ወልቂጤ በማድረግ በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፉ ባሻገር ወልቂጤ ከተማ እግርኳስ ክለብን በመደገፍ ብዙ ዋጋ ከከፈሉ እና ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማሻገር መልያውን ለብሶ በየሜዳዎቹ በመገኘት ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ አመራር በመስጠት እና በማስተባበር ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል። ወደፊትም ክለቡን ለማዘመን እና ከመንግስት ጥገኝነት አላቆ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ለማድረግ እየተጋ ይገኛል። ብርቱካናማውን መለያ ለብሰው ከፍ ብለው ከሚታዩ የክለቡ የልብ ደጋፊዊዎች መካከል አንዱ የሆነው የዛሬው እንግዳችን የወቅቱ የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ማኀበር ፕሬዝደንት ከሚል ጀማል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

‘ከሚል ማነው?’ ለሚል ራስህን አስተዋውቅ ?

የተወለድኩት ወልቂጤ ነው። በትምህርቴ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያ ድግሪ አለኝ። ትምህርቴንም ካጠናቀቀኩ በኃላ በተማህርኩት ትምህርት ሀገሬን ማገልገል አለብኝ ብዬ በማሰብ የተለያዩ ስፖርት ቤቶችን በመክፈት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (ማርሻል አርት) ከአስር ዓመት በላይ አሰልጥኛለው። እግርኳስን ከመጫወት ጀምሮ አሰልጣኝ ለመሆን ኮርስ እስከመውሰድ ደርሻለው። በዚህም ብቻ ሳላበቃ የእግርኳስ ዳኛ ለመሆን ከመምሪያ ሁለት አንስቼ እስከ ፌደራል ዳኝነት ደርሻለው። ብዙ በዳኝነቱ የመቀጠል ዕቅዱ ቢኖረኝም የመኪና አደጋ አጋጥሞኝ መቀጠል ሳልችል ቀረው እንጂ በዳኝነቱም ጥሩ ነበርኩኝ። በአጠቃላይ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ህይወቴ ከስፖርት ጋር የተያያዘ ነው።

ወልቂጤ ከተማን ለመደገፍ መነሻ የሆነህ ምክንያት ምንድነው?

ዕድገቴ ከስፖርት ጋር የተያያዘ ስለሆነ እና ወልቂጤ ትውልድ እና ዕድገቴ ስለሆነ ነው። ማንም ሰው በየትኛውም የሙያ ዘር ቢሆንም እንኳን መነሻ የሆነውን ቦታ የማስታወስ የመደገፍ ኃላፊነት አለበት። እኔ ደግሞ ስፖርቱን ስለምወድ እና የህይወቴ አካል ስለሆነ በአጋጣሚ የገባሁበት አይደለም። ባለኝ ዕውቀት ይህን ከፍተኛ ማኀበረሰብ የያዘን ቤተሰብ ማገልገል የሚሰጠው እርካታ ከፍተኛ በመሆኑ  ወልቂጤ ከተማን በመደገፍ ስፖርቱ በዕውቀት እንዲመራ ለማድረግ እና ውስጤ ቁጭት ስለነበር ክለቡን ለመደገፍ መነሻ ምክንያት ሆኖኛል። 

ከወልቂጤ ከተማ ጥንካሬ ጀርባ የአንተ አስተዋፆኦ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው። የተለየ ምክንያት አለህ ቅድም ከገለፅክልኝ ምክንያት ውጪ?

ቅድም አንዳልኩህ ነው። ስፖርት ለኔ የህይወቴ አንዱ አካል ነው። ያም በመሆኑ ሁልጊዜ ውስጤ ቁጭት ነበረብኝ። ባለኝ አቅም፣ ለእግርኳስ ባለኝ ስሜት እንዴት አድርገን ነው ይሄን ክለብ ልናሻግረው የምንችለው ? በማለት እና ካለው በርካታ ማኀበረሰብ አንፃር በሊጉ ቢኖር ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት የራሱ አስተዋፆኦ ሊኖረው ይችላል ከሚል ነው። በመገናኛ ብዙኃን እንደምታየው ሌሎች ክለቦች በእግርኳሱ መነሻነት ባህላቸውን እና አካባቢያቸውን ሲያስተዋውቁ ሳይ ጤናማ ማኀበረሰብ ለመፍጠር እግርኳሱን ሲጠቀሙበት ሳይ ቁጭ ብዬ የማስበው ይህ ክለብ ፕሪሚየር ሊግ ቢገባ ካለው በየሀገሩ ከተበታተነው ማኀበረሰብ አንፃር  ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት ይጠቅማል በማሰብ ለመስራት አስቤበት ነው ወልቂጤን የደገፍኩት። በዚህም የመጀመርያ ዕቅዴ ተሳክቷል። በጣም ዕድለኛ ነኝ ፤ ክለቡን በኃላፊነት በተረከብንበት ሁለት ዓመት ውስጥ በአንደኛው ዓመት ወልቂጤ ፕሪሚየር ሊግ ሊገባ ችሏል። በቀጣይ ዓለም በደረሰበት የዘመናዊ እግርኳስ ጉዞ ውስጥ  ክለቡን ለማዘመን በጣም ልሰራቸው የማስባቸው ብዙ ዕቅዶች አሉኝ ፤ ፈጣሪ ከፈቀደ አደርገዋለው።

ወደ ወልቂጤ ከተማ ደጋፊ ማኀበር አመራርነት እንዴት ልትገባ ቻልክ ?

ከስፖርቱ ጋር ረጅም ዓመት ካለኝ ቁርኝነት አንፃር ከወሰድኳቸው ከርሶች፣ ከተማርኳቸው ትምህርቶች አኳያ እና ካለኝ የረጅም ዓመት ልምድ ተነስተው እርሱ ወደዚህ መጥቶ ክለቡን ቢያግዝ ፣ ቢደግፍ ወልቂጤን ወደ ትልቅ ምዕራፍ ለማሻገር ሊጠቅም ይችላል በሚል በሌለሁበት ነው ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት የተመረጥኩት። እኔም ምንም አላንገራገራገርኩም በደስታ ነው የተቀበልኩት። ምክንያቱም በውስጤ ቁጭት አለ። ያንን የክለቡን የዘጠኝ ዓመት ልፋትን እውን ለማድረግ አጋጣዊውን ለመጠቀም በማሰብ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖኛል ክለቡን በኃላፊነት ማገልገል ከጀመርኩ።

የወልቂጤ የመጀመርያ ጨዋታ ያየኸው መቼ ነው ?

በጣም በስሜት ልብ ብዬ ያየሁት ባቱ ላይ (ዝዋይ) በ2008 ነው። አምስቱን ጨዋታ እየተመላለስኩ አይቻለው።  ከዛ በፊት ባህርዳር በነበረው የብሔራዊ ሊግ ውድድር ላይ በተወሰነ መልኩ የማየት ዕድሉ ነበረኝ። ሆኖም በስርዓት የወልቂጤ ጨዋታዎችን ሳልቀር መከታተል የቻልኩት ዝዋይ ላይ በተካሄደው  ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት በነበረው እልህ አስጨራሽ ውድድር ነው። በዚህ ወቅት ሁሉም ደጋፊ እየተመላለሰ ቡድኑን በመደገፍ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲገባ ትልቅ አስተዋፆኦ አድርጓል። ይህ ወልቂጤ ወደ ከፍተኛ ሊግ የገባበት አጋጣሚ ሁሉንም የወልቂጤ ማኀበረሰብን ከሀገር ውስጥም ከውጪም ያለውን ያነቃቃ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ለሚደረገው ጉዞ መነሻ የሆነ ትልቅ ውጤት ነበር።  ከዚህ በኃላ እስካሁን ድረስ ወልቂጤ ባለበት ቦታ ሁሉ እየሄድኩ መከታተል የህይወቴ አንድ አካል ነው። ኃላፊነቱም ስላለብኝ ከዚህ በኃላም የተለየ ምክንያት ካልተፈጠረ በቀር ወልቂጤ በሜዳ ውስጥ ካለ እኔ እኖራለው።



የወልቂጤን ደጋፊ በምን ትገልፀዋለህ ? 

በጣም ከባድ  ጥያቄ ነው ፤ በድንገት የምትመልሰው አይደለም። የወልቂጤ ማኀበረሰብ ለእግርኳስ የተፈጠረ ህዝብ ነው።  ብዙ መናገር እችላለው ሆኖም በአንድ ምሳሌ የወልቂጤን ደጋፊ ልግለፅልህ።  ‘ለአርባ አምስት ደቂቃ ጨዋታ ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር የሚጓዝ አስገራሚ የእግርኳስ ፍቅር ያለው ደጋፊ ነው። ላስታውሳለህ ዓምና ዲላ ላይ በዝናብ ምክንያት ጨዋታው ተቋርጦ ደጋፊው ወደ ቤቱ ተመልሷል። በድጋሚ ቀሪው አርባ አምስት ደቂቃ በሚካሄድበት ወቅት ለአርባ አምስት ደቂቃ ጨዋታ ድጋሚ አንሄድም ሳይል ለቀሪዋ ጨዋታ ሲል በድጋሚ ክለቡን ለመደገፍ የሚጓዝ ታማኝ እግርኳስን በእውቀት የሚመለከት ፣ ስራው መደገፍ እና መደገፍ ብቻ የሆነ ምርጥ ደጋፊ ነው። እኔም ደስተኛ ነኝ የዚህ ክለብ ደጋፊ አመራር በመሆኔ። 

አዲስ አበባ  የነበረውን ኑሮህን ትተህ ጠቅልለህ ወደ ወልቂጤ የገባኸው ለማኀበረሰቡ ካለህ አክብሮት ነው ማለት ይቻላል ? 

አዲስ አበባ ቤተሰቦቼ አሉ። ሆኖም በተማርኩት ትምህርት ማኀበረሰቤን ማገልገል ስላለብኝ ብዬ ነው ወደ ወልቂጤ ተመልሼ መኖር የጀመርኩት። የሰው ልጅ ሁሌም የተሻለ ነገር ማግኘት ይፈልጋል። ግን ጤናማ እና ብቁ የሆነ ሰውነቱ በአካል ብቃት የዳበረ ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ለሀገሬ አንድ ነገር ማድረግ ከፈጣሪም የማገኘው ዋጋ አለ በሚል ያስተማረኝን ማኀበረሰብ ማገልገል ስላለብኝ ነው የመጣሁት። ያወቅኩትን ለማሳወቅ የኔ ትልቅ ከተማ ላይ መኖር ብቻ በቂ አይደለም። ይህ የራሴ ብቻ ደስታ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ራስ ወዳድ ልሆን ስለምችል የራሴን ፍላጎት ወደ ጎን ትቼ ወደ ወልቂጤ በመምጣት ባለኝ ዕውቀት እና ልምድ እያገለገልኩኝ እገኛለው። አንድ ሺህ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ጂም አለኝ  ፤ የራሴ አዳራሽ ነው። ለማኀበረሰቡ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል።

ወልቂጤን በመደገፍ መቼም የማትረሳው ውጤት የቱ ነው። አንተን በጣም ያስደሰተህ ?

በወልቂጤ የተደሰትኩባቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም የተደሰትኩበት የታወቀ ነው። ክለቡ ሲመሰረት የነበረው ራዕይ ከዓመታት በኃላ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ነበር። ይህ ዕውን የሆነበት ዕለት መቼም የማልረሳው በጣም የተደሰትኩበት ቀን ነው። ሌላው ፕሪሚየር ሊግ ገብተን በኢትዮጵያ እግርኳስ በሁሉም ረገድ ባለታሪክ የሆነውን ጊዮርጊስን በደጋፊው ፊት ባደግንበት ዓመት ስናሸንፍ መመልከት የሚኖረው የደስታ ስሜት ቀላል የሚባል አይደለም። 

ወልቂጤ ከብዙ ልፋት እና ጥረት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባቱን ስታረጋግጥ ምን ተሰማህ ?

አርሲ ነገሌ ላይ ነው ወደ ፕሪሚየር ሊግ መግባታችንን ያረጋገጥነው። እኔንጃ ምን ብዬ ደስታዬን ልግለፅልህ ? አንድ ገጠመኝ አለኝ ፤ እሱን ልንገርህ። ስታድየሙ ጭቃ ነው። በዛ ላይ ነጭ ልብስ ነው የለበስኩት። ይህችን ቀን ደግሞ ሁላችንም በጉጉት የምጠብቅበት ቀን ናት። ፈጣሪ ለዚህ ቀን ስላደረስከኝ ይህንንም ቀን ስላሳየህኝ አመሰግናለው ብዬ ጭቃ መሆኑን ረስቼ መሬት ተንበርክኬ ፀሎት ያደረኩበት ሁኔታ በጣም አስገራሚ ነበር። እግርኳስ በሰከንድ የሚለወጥ መሆኑን የተረዳሁትበት አጋጣሚ ነው። የዛን ዕለት ስለሆነው ነገር በቃላት የምገልፀው አይደለም። አዲስ አበባ ስታዲየም ከሊጉ ትላልቅ ቡድኖች ጋር ሲጫወት፣ ደጋፊዎቻችን ሲጨፍሩ ሳይ ሁሌም ትዝ የሚለኝ ያቺ አርሲ ነገሌ የሆንኳት ነገር ነው።

የዘንድሮ የወልቂጤ የሊግ ተሳትፎ እንዴት አየኸው?

ፕሪምየር ሊጉ መቋረጡ ለእኛ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ራሳችንን እንድናይ ጠንካራ እና ደካማ ጎናችንን እንድንፈትሽ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልናል። እንደሚታወቀው ወልቂጤ የራሱ የሆነ የተለያዩ አዲስ ፍልስፍናዎች ይዞ ነው የመጣው። ይሄ በነባር አሰልጣኞች ብቻ የማመን ነገር መቅረት አለበት። በአዲስ አቀራረብ  ብዙም የማይታወቅ ወጣት የሆነ በራሱ የሚተማመን ለራሱ ፍልስፍና ዕምነት እና ዕውቀት ኖሮት ሊያሻግር የሚችል አዳዲስ አስተሳሰብ ይዞ የሚመጣ በወጣት ተጫዋቾች ላይ መሠረት አድርጎ የሚሰራ ያልተለመደ አዲስ ፊት ይዘን መቅረብ አለብን።  ዝም ብለን ገባና ወጣ የሚል አሰልጣኝ ሳይሆን ለክለቡ አንድ መሠረት ጥሎ የሚሄድ አሰልጣኝ መቅጠር ያስፈልጋል ብለን በማመን ብዙ ውጣውረዶችን ተቋቁመን ደግያረጋልን ቀጥረናል። እግርኳስ በስም ሳይሆን በዕውቀት እና በአቅም ቡድን በመገንባት ነው የሚለካው። ደግነት ደግሞ በከፍተኛ ሊግ ከእኛ ጋር ሲጫወት ሁለት ጊዜ አይተነዋል። ይህ ሰው እኛ ጋር ቢመጣ ውጤታማ ይሆናል በማለት ያልተለመደ ነገር መሞከር አለብን ብለን አምነንበት ያደረግነው ተሳክቶልናል። በብዙ የእግርኳስ መለኪያዎች ስናየው አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም በወጣት የተገነባ ፣ ጥሩ ኳስ የሚጫወት ቡድን ተሰርቶ መልካም የሚባል የውድድር ዓመት አሳልፈናል። 

እንደ ደጋፊ ማኀበር ፕሬዝደንት ወልቂጤ በቀጣይ ዓመት ምን ለመስራት ያቅዳል? 

በክለቡ ዋና እና ምክትል ፕሬዝደንት በተደጋጋሚ ክከተለያዩ ሚዲያዎች ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት መሠረት መጣል አለብን ብለን ስለምናምን የውጭ ሀገር ተጫዋቾችን ላለመጠቀም ወስነናል። በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ ከምናምንበት ፍልስፍና ሳንወጣ ዘንድሮ የነበሩብንን ጉድለቶች አስተካክለን በተሻለ ሁኔታ መጓዝ እንፈልጋለን። ክለቡንም እንደታላላቆቹ እንደ ዛማሊክ አል አል አህሊ ዓይነት ክለቦች አደረጃጀት እንዲኖረው ብዙ ያቀድናቸው ዕቅዶች አሉን። በቀጣይ ብዙ ስራዎች ይጠበቁብናል።

ወልቂጤ በርካታ ደጋፊ በሀገር ውስጥ እና በውጪ እንዳለው ይታወቃል። ይህን ደጋፊ አስተባብራችሁ ክለቡን ተጠቃሚ (በገቢ) ለማድረግ ምን እያሰባችሁ ነው ? 

በሀገርም በውጪም ሀገር ያሉ ደጋፊዎቻችን ክለቡን ለመደገፍ እንዲችሉ ዓመታዊ ወጪው፣ በታዳጊ ላይ ምን መስራት እንደሰብን እንዲሁም ወደፊት እንዴት ነው ክለቡ ከመንግስት በጀት ተላቆ ራሱን ችሎ የዛሬ አምስት ዓመት አክሲዮን እንዲሆን በማሰብ ሰነድ አዘጋጅተን በያሉበት ቦታ እንዲደርስ እያደረግን እንገኛለን። እስካሁን ከሁለት ሺህ በላይ ሰው ተመዝግቧል። ከዚህም በላይ ቁጥር ያለው ደጋፊ በቀጣይ ይመዘገባል ብለን እናምናለን። መታወቂያ ለመውሰድ ያለው ትንቅንቅ በጣም ነው የሚገርምህ። ይህም ብቻ አይደለም ወልቂጤ የጉራጌ ማሕበረሰብን የሚወክል ቡድን እንደሆነ ይታወቃል። በየክልሉ እና ወረዳዎች እስከ ቡታጅራ ድረስ “ቤተ ጉራጌ” በማለት ንዑሳን ኮሚቴ አቋቁመን ፅህፈት ቤት ለመክፈት እየተንቀሳቀስን እያለን ነው ይህ በሽታ የመጣብን። በቀጣይ ይህን ክለብ ከመንግሰት እጅ አላቀን ህዝባዊ መሠረት ያለው ቡድን ለመገንባት አደረጃጀቱን በደንብ ማዋቀር አለብን። አዲስ አበባ የሚገኘውን ደጋፊ ለመጠቀም ፒያሳ አካባቢ ቢሮ ከፍተን እየተንቀሳቀስን ነው። ሳይመዘገብ የሚጠበቅበትን ማንኛውም ድጋፍ የማያደርግ ደጋፊ ደጋፊ ነው ብዬ አላምንም። ትክክለኛ ደጋፊ ነው የሚባለው ከክለቡ ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ግዴታ እና ውዴታ ሲወጣ ነው።

የወልቂጤ የደጋፊ ማኀበር አወቃቀር እንዴት ነው ? 

የደጋፊ ማኀበሩ አወቃቀር የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ አለው። አስር የሚሆኑ የሥራ አስፈፃሚ አባለት በሁለት ዓመት አንዴ በጠቅላላ ጉባኤው ምርጫ ይመረጣሉ። በውስጡ የተለያዩ አደረጃጀቶች አሉት። የዲሲፒሊን ፣ የፀጥታ ክፍል ፣ የራሱ የኦዲት ክፍል አለው። ሌሎች ኮሚቴዎችም በውስጥ አሉበት። በዚህ መልኩ ነው አወቃቀሩ። ሌላው የማኀበሩ ትኩረት ክለቡን ማገዝ እንጂ ከመለያ ሽያጭ ይሄን ያህል ፐርሰንት ይሰጠን የማይል ፣ ደጋፊውን አሰባስቦ የአቅም ግንባታ የሚያደርግ ነው።

የደጋፊ ማኀበሩ በክለቡ የበላይ አካል (ቦርድ) ጋር ያለው ግንኝነት ምንድን ነው ?  በክለቡ ያላችሁ የስራ ድርሻስ እስከምን ድረስ ነው ? 

በክለቡ ዋና ስራ አስፈፃሚነት ቦታ ውስጥ ሀምሳ በመቶ ድምፅ አለው። የማኀበሩ ፕሬዘዳንት በክለቡ ሥራ አስፈፃሚ በሚወሰኑ ማናቸውም ውሳኔዎች ውስጥ አንድ አካል ነው። የእኛ ደጋፊ እንደሚታወቀው አቢዮታዊ ነው። የሚነሱ ሀሳቦችን ለክለቡ አመራሮች የሚቀርቡ ነገሮች ካሉ ወድያውኑ ነው ተቀብሎ የሚያስተላልፈው። በአጠቃላይ በጣም ጤናማ የሆን ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከክለቡ አመራሮች ጋር አብሮ ይሰራል። በክለቡ ወሳኝ በሚባሉ የስብሰባ አጀንዳዎች ሲኖሩ እንኳን የደጋፊው ማኀበር ፕሬዘዳንት ከሌለ ስብሰባዎች አይካሄዱም። የዚህን ያህል ነው ግንኙነቱ።

ለአንተ በወልቂጤ ምርጡ ተጫዋች ማነው ?

ዳግም ንጉሴ ለኔ ምርጡ ነው። ሜዳ ውስጥ ባለው እንቅስቃሴ ያየኸው እንደሆነ ከእነ ስህተቱም ቢሆን እርሱ ለኔ ምርጡ ነበር። አዕምሮውን እና እግሩን አቀናጅቶ ይጫወታል፣ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ አገልግሎት ይሰጣል። ዘንድሮም ለወልቂጤ ብዙ ጨዋታ ያደረገ እርሱ ብቻ ነው።

ወልቂጤን በመደገፍህ የተደሰትክበት ቀን ቢኖርም ያዘንክበትን ወቅት አጫውተኝ…

ሜዳችን ቅጣት ተጥሎበት በአዲስ አበባ ስታድየም ተጫውተን በአዳማ ከተማ የተሸነፍንበት ጨዋታ በጣም ያዘንኩበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈን ከመጣን በኃላ የተሸነፍነው ጨዋታ ነው። እኛ የወልቂጤ ደጋፊዎች ቃል የገባንበት ነገር አለ። በአሰልጣኝ ጉዳይ ላይ በአስተላለፍ አወጠጥ ላይ እከሌን ቀይረው እከሌን አስገባው እያልን ጣልቃ በምንም መንገድ አንገባም። የአዳማን ጨዋታ ስናየው የተጫዋቾች አጠቃቀም ላይ ስህተት ነበር። እንሸንፋለን ብዬ ተጀመሮ እስኪያልቅ ድረስ ተጨንቄ በማየት የፈራሁት ደርሶ የዛን ዕለት በጣም ነው ያዘንኩት። ብናሸንፍ ኖሮ ደረጃችን ወደ አራተኛ ደረጃ እናሻሽላለን ብለን ጠብቀን ነበር። ጊዮርጊስን አሸንፎ ስለመጣ ከደመወዝ ጋር ተያይዞ ያለበትንችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ባለኃብቶች ቃል የገቡበት ሁኔታም ነበር።  ቢያሸንፉ ኖሮ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ምክንያት ይሆን ነበር። የገቢ ማሰባሰብያ ፕሮግራም ሁሉ በኮሮና ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።  ብቻ በቦርዱ ላይ የነበረው ሞራል ክስክስ ነው ያለው። አንዳንዴ ትልቅ ነገር ታስብ እና ባልጠበከው ነገር የሆነ ነገር ሲፈጠርብህ ስሜትህ ይጎዳል።

ውድድሮች እስከተቋረጡበት ጊዜ ድረስ ከእግርኳሳዊ ሀሳብ ውጪ አላስፈላጊ የሆኑ የእግርኳስ መንፈስን የሚረብሹ ድርጊቶች በደጋፊዎች መሐል እየተንፀባረቁ ነበር። እንደ አንድ ደጋፊ ማኀበር ፕሬዘደንት ይሄን እንዴት ታየዋለህ?

በዚህ ነገር ላይ በጣም ረዥም የሆኑ ሀሳቦች አሉኝ። ጊዜም ወስጄ የፃፍኳቸው ፕሮፖዛሎች አሉ። ሜዳ ውስጥ የሚፀባረቁ ነገሮች እንኳን አኛ ሀገር አይደለም በአደጉ ሀገሮች የሚታዩ ናቸው። በሰከንድ በሚፈፀም ስህተት ደጋፊውን ወደ አላስፈላጊ ነገሮች ይወስዱታል። ይህ የሚሆነው ደግሞ እግርኳስን ከምንም ነገር ጋር ሳያያይዙ በመቃወም ብቻ ነው። ኳስ ዘር፣ ጎሳ፣ ኃይማኖት እና ፆታ የለውም። ሁሉም ሰው በዕኩልነት ስሜቱን የሚገልፅበት ነው። ስሜትህን ስታፀባርቅ አጠገብህ ካለው ወንድምህ ፣ እህት ጋር ልትጋጭ ትችላለህ። ዘጠናው ደቂቃ ካበቃ በኋላ ግን አጀንዳ ተደርጎ የሚደረግ አላስፈላጊ ነገር ለሀገርም ፣ ለክለብም፣ ለስፖርትም የማይጠቅም እንደሆነ ፅኑ ዕምነት አለኝ። ወደ ፊትም ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረግ እፈልጋለው። እንዴት ነው የኔ ቡድን ሲጫወት ኃላፊነት ወስጄ ጨዋታው በሠላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ መስራት ያለብን የሚለውን እኛ እንሰራለን። የኛ ማኀበረሰብ ደግሞ በየቦታው ተበታትኖ የሚሰራ በመሆኑ በግል የምንፈጥራቸው ችግሮች ማህበረሰቡ ላይ የሚፈጥሩት ተፅእኖ ቀላል የማይባል ስላልሆነ ከሁሉም ደጋፊዎች ጋር ተቻችለን አብረን ሰርተን የምንኖር መሆኑን ይህን አብሮነት የማይቀበል ፣ የማያደርግ ደጋፊ የወልቂጤ ደጋፊ አይደለም የሚል አቋም አለን። በእኛ ክለብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ክለብ ላይ እግርኳሳችን እንዲያድግ ከእኛ የሚጠበቀው መደገፍ እና መደገፍ ብቻ ነው። ዳኛ የዳኝነቱን ስራ ይሰራል፣ ተጫዋች የተጫዋችነቱን ስራ ይሰራል። አሰልጣኝም የአሰልጣኝነቱን ስራ ከሰራ ከዚህ በፊት የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ነገሮች ይወገዳሉ ብዬ አምናለው። መንግስት ብዙ መሠረተ ልማት አቁሞ ባላደገ እግርኳስ ይሄን ያህል ወጪ እያደረገ የሚገኘው የሰዎች ንብረት ፣ ክብር ፣ ህልውና እና ለመንካት አይደለም። ከዚህ አንፃር በእኔ ዕምነት  ማኀበሩን እስከ መራው ኃላፊነት እስከተሰጠኝ ድረስ ይህን አቋም ይዤ ነው የማራምደው፣ የምንቀሳቀሰው

ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሊግ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በአዲስ አበባ ስትጫወቱ በተፈጠረ ችግር ታስረህ ነበር ? 

ለእኛ ለወልቂጤ ደጋፊዎች ትልቅ ትምህርት የሰጠ አጋጣሚ ነው። በዕለቱ በአዲስ አበባ ፌደራል ሜዳ የተፈጠረው ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ አምነን ከዚህ በኃላ ወልቂጤን የምንወድ ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ የሆነ አላስፈላጊ ተግባር ላለፈፀም ቁጭ ብለን ተነጋግረን ጠቃሚ ውሳኔ ያሳለፍንበት ነው። እኔም በወቅቱ የደጋፊው ተወካይ መሪ እኔነኝ ለተፈጠረው ነገር ኃላፊነት እወስዳለው ብዬ ደጋፊው በሠላም እንዲሄድ ሦስት ቀን የታሰርኩበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።

በመጨረሻ…

እግርኳሱ የሚወክለው መቶ ሚሊዮን የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብን ነው። ስፖርት አሁን በመንግስት በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህ አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል። ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት የሁሉም ሰው አስተዋፆኦ ያስፈልጋል። ሁሉም ባለበት የሙያ መስክ ጠጠር በመወርወር የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት። ከግል ስሜት እና ከዘረኝነት አስተሳሰብ ወጥተን ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ሁላችንም  የማናቀውን እየጠየቅን የምንችለውን ነገር ማድረግ አለብን ። ሁሉም ሰው በጥምረት በአንድነት ተቀራርቦ መስራት ይገባል። ስፖርት ትልቅ ብራንድ ነው። እዚህ ላይ በጣም ትኩረት ተስጥቶበት ሊሰራ ይገባል እላለው። እግርኳስ የሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድግ  ሀብት ነው።
                                                                                          

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ