በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ውስጥ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ካሳዩ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አጥቂው ጸጋዬ ተሾመ የዛሬ ባለተስፈኞች ተረኛ እንግዳችን ነው።
በተስፋ ቡድን ውድድሮች ላይ ሶከር ኢትዮጵያ በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ በመታደመ እንደነበራት ምልከታ እድገታቸውን ጠብቀው፣ የሚጫወቱበት ክለብ ተገቢውን ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ካደረጉላቸው ትልቅ ተጫዋቾች ይሆናሉ ብለን ያለፉት ሁለት ዓመታት በትኩረት ከተመለከትናቸው ታዳጊ ተጫዋቾች መካከል የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ጸጋዬ ተሾመ አንዱ ነው። ከለገጣፎ ከተማ ወደ ውስጥ በምታስገባ ገጠራማ ከተማ የተወለው ጸጋዬ ለትምህርት ቤት ውድድር በሚያሳየው እንቅስቃሴ ተገርመው በአካባቢው ለሚገኝ ቡድን፣ በመቀጠል ጎዶልያስ ለተሰኘ ክለብ በክረምት የታዳጊውች ውድድር ተሳታፊ ሆኗል። ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ውድድር ሲጫወት የተመለከተው አሰልጣኝ ደረጄ በ2010 የፈረሰኞቹ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ቡድን አባል በመሆን ሁለት ዓመት ቆይታ ካደረገ በኃላ ዘንድሮ ከ20 ዓመት በታች ውድድር በኮሮና ቫይረስ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ እየተጫወተ ቆይቷል።
ፍጥነቱን፣ በጉልበቱ ተጠቅሞ በሚወስናቸው ውሳኔዎቹ የሚያስቆጥራቸው ጎሎቹ የእርሱ መገለጫዎች ናቸው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በአመራሩ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ ለታዳጊዎች የሚሰጠው ትኩረት እየቀዘቀዘ በተጫዋች ግዢ ላይ መሠረት ያደረገ ቡድን መገንባት መጠመዱ በእድገቱ ላይ ፈተና ቢሆንም ክለቡ ፊቱን ለታዳጊዎቹ ትኩረት ከሰጠ የወደፊቱ ጥሩ አጥቂ የመሆን ዕድል አለው። በዛሬው የተስፈኛ አምዳችን ከሆነው ከፀጋዬ ተሾመ ጋር ያደረግነው አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።
“የተወለድኩት ከለገጣፎ ከተማ አስር ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ዳሌ በምትባል ገጠር ከተማ ነው። ለተሻለ ለትምህርት ቤተሰቦቼ ጋር ለገጣፎ በመምጣት እየተማርኩ በትምህርት ቤት ውስጥ እግርኳስ እየተጫወትኩ በማደርገው እንቅስቃሴ ጥላሁን በሚባል አሰልጣኝ የለገጣፎ ፕሮጀክትን እንድቀላቀል አደረገኝ። በኃላም ጎዶልያስ የሚባል ቡድን በአሰልጣኝ ወልዴ በሚሰለጥን ቡድን የክረምት ውድድሮችን ሳደርግ ቆይቼ የይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ውድድር ላይ አሰልጣኝ ደረጄ አይቶኝ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ያለፉትን ሦስት ዓመት እየተጫወትኩ ነበር። ለኔ በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ቆይታዬ በተለይ በ2011 የነበረው የአዲስ አበባ የታዳጊዎች ውድድር ላይ በአጠቃላይ 19 ጎል አስቆጥሬ በአዳማው ፍራውል ተቀድሜ ሁለተኛ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ ያጠናቀኩበት ዓመት በጣም አሪፍ ጊዜ ነበር። ዘንድሮም በኮሮና ቫይረስ ውድድሩ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በአምስት ጨዋታ አራት ጎል ነበረኝ። ፍጥነቴን ያገኘሁት በልጅነቴ ሯጭ የመሆን ፍላጎት ስለነበረኝ በተወለድኩባት ዳሌ ገጠር ከተማ ሯጭ ለመሆን በፕሮጀክት ውስጥ ታቅፌ ልምምድ እሰራ ነበር። በአጋጣሚ አሁን ኳስ ተጫዋች ልሁን እንጂ። ስለዚህ ልጅ ሆኜ የሩጫ ልምምድ አብዝቼ መስራቴ ትንፋሽ እና ፍጥነት እንዲኖረኝ አድርጎኛል።
“ወደፊት እድሉን ካገኘው በምወዳቸው ሁሌም በሚያበረታቱኝ ደጋፊዎች ፊት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ መድረክ ክለቡን ማገልገል እፈልጋለው። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት አስባለው። ለኔ ዚህ መድረስ የቤተሰቤ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው በተለይ ወንድሜ ወሰኑ ትልቅ ተጫዋች እንድሆን በጣም ይረዳኛል፣ ይደግፈኛል። እንዲሁም ለኔ እዚህ መድረስ አሰልጣኝ ደረጄን ማመስገን እፈልጋለው። እንደ ወንድሜ የማየው በቡና ተስፋ ቡድን የሚጫወተው ዳኛቸው ዘለቀን ማመስገን እፈልጋለሁ። እኔ ሜዳ ገብቶ መጫወት እንጂ ልምምድ ላይ ሰነፍ ነኝ፤ እርሱ ተው ጥሩ አይደለም እያለ እየመከረኝ ራሴን እንዳስተካክል አድርጎኛል። በአጠቃላይ ቤተሰቤን የቡድን አጋሮቼ፣ መላውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን አመሰግናለው።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ