የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ቅጥር ነገ አቅጣጫ ይሰጥበታል

ለሃያ አምስት ቀናት አሰልጣኝ አልባ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር አስመልክቶ ነገ በሚደረገው የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ አቅጣጫ ይሰጥበታል።

የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን የሁለት ዓመት የውል ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ ኮንትራታቸውን እናራዝም ወይም ለተወሰነ ጊዜ ምንም ዓይነት ውድድር የሌለ በመሆኑ አሰልጣኝ አያስፈልግም በሚል ሁለት በተለያዩ ሀሳቦች ዙርያ መከራከርያ ተነስቶ ባልተለመደ ሁኔታ በድምፅ ብልጫ ኢትዮጵያን ለሃያ አምስት ቀን አሰልጣኝ አልባ አድርጓት ቆይቷል።

2022 በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጥቅምት ወር መጨረሻ የሚደረጉበትን ጊዜ ካፍ በድንገት ማሳወቁን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ በድጋሚ አሰልጣኝ የመቅጠር ግዴታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ጥቅምት ወር የሚካሄደውን የማጣርያ ጨዋታ ለማድረግ የመንግስትን ውሳኔ እየጠበቀ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ ነገ ማክሰኞ ቀን የሥራ አስፈፃሚው አባላት 04:00 ላይ መደበኛ ስብሰባውን እንደሚያደርግ እና ዋናው አጀንዳው የዋልያዎቹ አሰልጣኝን ቅጥር አስመልክቶ መነጋገር እንደሆነ ሰምተናል።

እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የቴክኒክ ኮሚቴው የአሰልጣኙን የቅጥር ሁኔታ እንዲያስፈፅም አቅጣጫ እንደሚሰጠው የተገለፀ ሲሆን ራሳቸው አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ዳግም የዋልያ አሰልጣኝ የመሆናቸው ጉዳይ የተቃረበ እንደሆነ ሰምተናል። በትናንትናው ዕለት በአሸናፊ በጋሻው የእውቅና መርሐግብር ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ አብረው በመምጣት እና አንድ ላይ በመቀመጥ መታደማቸውም ይታወቃል።

በቅርብ ጊዜያት ይጠናቀቃል በሚባለው የአሰልጣኙ ቅጥር ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮች ካሉ እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!