በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ትውስታዎች ፣ የብሔራዊ ቡድን አጀማመር እና የሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫን ትዝታ እያወሳን ቆይተናል። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያን ብቸኛ አህጉራዊ ድል ከመንግሥቱ ወርቁ ሚና ጋር አብረን እናስታውሳለን።
ማስታወሻ ፡ በገነነ ሊብሮ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እና የልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ የታላቁን ሰው ህልፈት ተከትሎ በተከታታይ ያወጣቸው ፅሀፎች ዋነኛ ግብዓት እንደሆኑ እንገልፃለን።
በ1949 እና 51 በተደረጉት ቀዳሚዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ዕድል የነበራት ኢትዮጵያ አንዴ በሱዳን ሁለት ጊዜ ደግሞ በግብፅ ሽንፈቶችን ከማስተናገድ ያለፈ የድልም ሆነ ግብ የማስቆጠርን ታሪክ መፃፍ አልቻለችም። በእርግጥ ደቡብ አፍሪካን በፌርፌ አልፋ በፍፃሜው በግብፅ በተረታችበት የመጀመርያው ውድድር ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች። ይህ ግብፅ ላይ ተከናውኖ የነበረው አህጉራዊ ዋንጫ ግን ብሔራዊ ቡድኑ ልምድ ቢያካብት የተሻለ ጥንካሬ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ያመላከተ በመሆኑ ዛሬ ላይ እንኳ በማንመለከተው ሁኔታ የንጉሱም ችሮታ ታክሎበት በኳሳችን ታላቅ ባለውለታ ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ መሪነት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ሄዶ እንዲዘጋጅ በር የከፈተ ነበር። በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ ስብስብ ለጨዋታ ከሀገር ወጥቶ በዛው መቅረት በማይታሰብበት በዚያ ዘመን ወደ ግሪክ አቀና። መዲናዋን አቴንስን እንደዋና መቀመጫው አድርጎም ወደ ሩማንያ ፣ ዩጎዝላቪያ እና ወደመሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት በማቅናት በርከት ያሉ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል። በእነዚያ ወቅቶች ዩጎዝላቪያን 2-1 በማሸነፍ የሀገሬው ህዝብ በራሱ ቡድን ላይ ቁጣውን እንዲያሰማም ምክንያት ሆኖ ነበር። ታዲያ በዚህ ወቅት ትምህርቱን እንኳን ያልጨረሰው ወጣቱ መንግሥቱ ወርቁ ገና በለጋ ዕድሜው ከጎረቤት ሀገራት አልፎ አውሮፓ ድረስ የመሄድ እና ሌላውን ዓለም የማየት ዕድልን አግኝቷል። እንደዘበት ከቋራ ለተነሳው የወደፊቱ የሀገር ጀግና እነዛ ሦስት እና አራት ዓመታት በህይወቱ ያላሰባቸውን ብዙ አዳዲስ ነገሮች ያየባቸው እንደነበሩ መገመት አያዳግትም።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተከናወነው ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከቀድሞዎቹ ውድድሮች በተሳታፊዎች ቁጥር የጨመረ ነበር። ዘጠኝ ያህል ሀገራት በውድድሩ ላይ የመሳተፍ ሀሳብ ኖሯቸው ሞሮኮ አስቀድማ ራሷን በማግለሏ እንዲሁም ግብፅ የሁለተኛው ውድድር አሸናፊ በመሆኗ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አዘጋጅ ሆነው በቀጥታ ሲያልፉ ቀሪዎቹ ሥድስት ቡድኖች ለሌሎቹ ሁለት ክፍት ቦታዎች በማጣሪያ አልፈው ቱኒዚያ እና ዩጋንዳ ወደ ቀደማዊ ኃይለሥላሴ ስታድየም እንዲመጡ ሆነ። በዚህም መሰረት ጥር 06 ቀን 1954 ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከቱኒዚያ ጋር አደረገች። ይህ ጨዋታ የእስካሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የግብ አካውንቱን የከፈተበት እንዲሁም ተፅዕኖውን ያሳየበት ነበር። ቱኒዚያ እስከ እረፍት 2-1 በመራችበት ጨዋታ ኢትዮጵያ 4-2 ስታሸንፍ መንግሥቱ ወርቁ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በሉቻኖ ቫሳሎ ለተቆጠረችው የመጀመሪያ እና የፍፁም ቅጣት ምት ጎልም የእሱ መጠለፍ መንስኤ ሆኖ ነበር። (ሌሎች የታሪክ መረጃዎች በዚህ ጨዋታ መንግሥቱ አንድ፣ ሉቻኖ ሁለት ስለማስቆጠራቸው ይገልፃሉ።) በውጤቱም ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 2-1 ከረታችው ከያኔዋ ዩናይትድ አረብ ሪፐብሊክ (ግብፅ) ጋር ለፍፃሜ ደረሰች።
ግብፅ የሁለት ጊዜ ቻምፒዮን መሆኗ ብቻ ሳይሆን በሁለት አጋጣሚዎች ኢትዮጵያን በ4-0 ውጤት አሸንፋለች። ከዚህም በላይ ቡድኑ በኦሊምፒክ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻለበትም ወቅት በመሆኑ ኢትዮጵያን አሸንፎ ንግስናውን የሚሰልስበት ጨዋታ እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነበር። ቡድኖቹ በንፅፅር ቢታዩ እንኳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አውሮፓ ሄዶ የመዘጋጀት ዕድል ይግጠመው እንጂ በሸራ ጫማ ልምምድ የሚሰራ አልፎ አልፎም በእግር ወደ ስታድየም የሚሄድበት ጊዜ በመሆኑ ለጨዋታው የበታች ሆኖ ቢገመት አይገርምም። በሌላ በኩል ደግሞ በራሱ ሜዳ የተዘጋጀውን ውድድር ከማሸነፍ ባለፈ በእግርኳስ እየተሳበ ወደ ስታድየም የመምጣት ልምድን እያዳበረ የነበረው የአዲስ አበባ ነዋሪ ለስፖርቱ ያለው ፍቅር እንዳይሸረሸር ማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን የወቅቱን ታላቅ ቡድን እና ከአንዴም ሁለቴ በሰፊ ጎል ያሸነፈውን ቡድን የመበቀያ አጋጣሚ ስለነበር ጣይቱ ሆቴል የከተሙት መንግሥቱ እና ጓደኞቹ በቀላሉ እጅ ለመስጠት እንደማይፈቅዱ ግልፅ ነበር።
ቀኑ ከጥምቀት ጋር በመግጠሙ ህዝቡ ከበዓሉ መልስ የያኔውን የኃይለሥላሴ ስታድየም መሙላቱ አልቀረም። በጉጉት የተጠበቀው ጨዋታ ሲጀምርም እንደተገመተው ሁሉ ግብፆች አግብተው መምራት ጀመሩ። እንደ ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሁሉ በዚህም ጨዋታ ኢትዮጵያዊያኑ በጫማ ጉዳይ መቸገራቸው ግን አልቀረም። ቡድኑ የተጫማው ጫማ ለጨዋታው የሚመች አልነበረም። ሆኖም ማሸነፍን ብቻ የሚያስቡት የያኔዎቹ የብሔራዊ ቡድኑ ተሰላፊዎች ህመሙን ተቋቁመው መቀጠል ነበረባቸው። መንግሥቱ ጫማው የፈጠረባቸውን ህመም ለሊብሮ እንዲህ ገልፆለት ነበር።
“ከዕረፍት በኋላ እግሬ እየደማ ነበር የተጫወትኩት። ያን ጊዜ ጫማ እንዳሁኑ ከወጪ ተገዝቶ አይመጣም ፤ እዚሁ ነው የሚሰራው። እግርህን ወረቀት ላይ ታደርግና እግርህ ዙሪያ ልክ ምልክት ተደርጎበት ነው የሚሠራልህ። ታድያ ጫማው ሲመጣ ይጠብሀል። ያ ጫማ ደግሞ በግርግር ነው የተሰራው። ” ብሎ ነበር። በዚህ ህመም ውስጥ ሆነው ከዕረፍት ሲመለሱ ግብፆች ውጤት ከማስጠበቅ ይልቅ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ይበልጥ በማጥቃት ነበር የቀጠሉት። ተቀየሮ የገባው ተክሌ ኪዳኔ ቡድኑን አቻ ቢያደርግም ግብፆችም በቶሎ ምላሽ ሰጡ። ጨዋታው በግብፅ 2-1 መሪነት ቀጥሎ ህዝቡ ስጋት ውስጥ በወደቀባቸው ደቂቃዎችም የተስፋዬ እና የጌታቸው ጥምረት በሉቻኖ ድንቅ አጨራረስ ጨዋታውን ወደ ጭማሪ ደቂቃ ወሰደው።
ዘጠና ደቂቃው ተገባዶ ወደ ጭማሪ ሰዓት ሲያመሩ ኢትዮጵያዊያኑ በረቱ። መንግሥቱ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ቱኒዚያ ላይ ባስቆጠራቸው ግቦች የግብፆቹ ዓይን አርፎበት በአግባቡ ቢይዙትም ለጓደኞቹ ኳሶችን ለማድረስ ይታገላል። በዚህ አስጨናቂ ሰዓት ኢታሎ ሦስተኛዋን ግብ ከመረብ አገናኘ ፤ 3-2። ይህን ጊዜ ግብፆች ዳግም አቻ ለመሆን ይበልጥ ማጥቃት ጀመሩ። በጨዋታው ሁለት ግብ ስላስቆጠሩም ሦስተኛውን ለመድገም ልበ ሙሉ ሆነው ማጥቃታቸውን ቀጠሉ። የአዲስ አበባ ስታድየምን የሞላው ህዝብም ይበልጥ ጭንቀት ውስጥ ገባ። እንግዶቹ አንድ ካጋቡ ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት እና ወደ ሌላ ጭንቀት መግባቱ ነው። ይህ ጭንቀት ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድናችን ሱዳንን 2-0 እየመራ በነበረበት ሰዓት ከነበረው አዲስ አበባ ስታድየምን የሞላው ሰው ጭንቀት ጋር ይመሳሰል ነበር። የተጋጣሚ አንድ ጎል ነገሮችን ወደ ኋላ ትመልሳለች። የኢትዮጵያ አንድ ጎል ደግሞ ጭንቀትን አራግፋ ደስታውን እርግጥ የማረግ አቅም ነበራት። መንግሥቱ ሀሳቡ ሁሉ ይህችን ግብ ማስቆጠር እና ሕዝቡን እፎይ ማስባል ነበር። ግን እንዴት ? የተመደበበት ተከላካይ ጥፍንግ አድርጎ ይዞታል። ታላቁ ስምንት ቁጥር የእሱን ትኩረት የሚያሳጣበት መላ ይፈልግ ገባ። አዎ መንግሥቱ ወርቁ መላ አላጣም። ምን አደረገ ? ሜዳ ላይ ያደረገውን እንዲህ አስታውሶታል። ” እኔ ጋር ያለው ተከላካይ ሊለቀኝ አልቻለም። ከዛ መሀል ሜዳ አብረን ቆመን ዞር ብዬ ገላመጥኩትና ሲጠጋኝ ሆዱ ላይ አልኩት ፤ ይሄን ጊዜ ፈራኝ። ቢመጣ ኖሮ ተደባድበን መውጣታችን ነበር። ከዛ ስመታው ትንሽ ራቅ ሲልልኝ በአጋጣሚ ኳሱ ለእኔ ተሰጠኝ ያንን ይዤ እየሮጥኩኝ በረኛው ሲወጣ በአናቱ ላይ አገባሁትና በቃ እሮጥኩኝ። ከዛ በኋላ የግብፅ ነገር አከተመ። መረቡ ላይ ተንጠልሕዬ ስለነበር እጄ ደም በደም ሆነ። ይሄን ሁሉ ያወኩት ስወጣ ነበር።”
በጡጫ የተፀነሰችው የመንግሥቱ ጎል ጭንቀት እና ሥጋትን ከህዝቡ ላይ አስወግዳ ድልን አወጀች ፤ ኢትዮጵያ የሁለት ጊዜ የአራት ግቦች ሽንፈቷን ብድር መልሳ የአፍሪካ ቻምፒዮን ሆነች። አዲስ አበባም ቀውጢ ሆነች። ምናልባትም ያ ጨዋታ እና ድል የሕዝቡን የእግርኳስ ልክፍት በይፋ ያስጀመረ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ከ120 ደቂቃዎች ፍልሚያ በኋላ ይህን ታላቅ ታሪክ ፅፎ በክፍት መኪና ሳይሆን በሁለት ሠዓታት የእግር ጉዞ በሕዝብ ጭፈራ ታጅቦ ወደ ጣይቱ ሆቴል ደረሰ። የሆቴሉ ሠራተኞችም ተጫዎቾቹን ከፍ አድርገው እየተሸከሙ ተቀበሏቸው። በዚህ እግር ኳሳችን የክፍለ አህጉር ድል እንኳን ካየ ወደ 15ኛ ዓመቱ በተቃረበበት ጊዜ ተመሳሳይ አህጉራዊ ድል ቢገኝ በምን መልኩ እንቀበለው ደስታችንስ እስከየትኛው ጥግ ይደርስ ይሆን ?
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!