አሸናፊ በጋሻው በኢትዮጵያ እግርኳስ ላበረከተው የረዥም ዓመት አስተዋፅኦ የተዘጋጀው የእውቅና እና ምስጋና መርሐግብር በደማቅ ሁኔታ ማምሻውን በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኢንጅነር ኃይለየሱስ ፍስሐ፣ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የቡና ክለብ ፕሬዝደንት፣ ኢንስትራክተር አብርሐም መብራቱ እና የተለያዩ እንግዶች በክብር እንግድነት በታደሙት በዚህ የዕውቅና መርሐግብር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኀበር ፕሬዝደንት በአቶ ክፍሌ አማረ አሸናፊ በጋሻው ለኢትዮጵያ ቡና በታማኝነት በማገልገል ላበረከተው ከፍተኛ አገልግሎት ይህ የእውቅና ሽልማት መዘጋጀቱን በመክፈቻ ንግግራቸው ከተናገሩ በኃላ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ” በኢትዮጵያ እግርኳስ ያልተለመደ ሁኔታ በህይወት ያለ ተጫዋች ማክበር፣ ለወደፊት ትውልድም ብዙ መልክት ያለው እጅግ የሚደነቅ በቀጣይ ለብዙዎች ክለቦች ትምህርት የሚሰጥ ነው። በዚህ በጎ ተግባር የተሳተፋቹ የኮሚቴ አባላት ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለው። የኮሮና ቫይረስ ሁላችንም ወደ ቀልባችን የተመለስንበት ነው ። ለዚህም ማሳየው ብዙ በጎ የሆኑ ስራዎች መሠራታቸው ነው።” በማለት ተናግረዋል።
መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ አክለው ” ስለ አሸናፊ በጋሻው በዚህ አጭር ሰዓት ምንም መናገር አይቻልም። የዛሬውን ዝግጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማዘጋጀት ትልቁን ሚና ለተወጡ የኮሚቴ አባለት ምስጋና አቀርባለው። አሸናፊ ሰውነቱ ቀጭን፣ ቁመቱ አጭር ቢሆንም እጅግ ጀግና፣ ደፋር፣ ብልጥ እና ለቡና የታመነ ተጫዋች ነው።” በማለት እጅግ ልብ በሚነካ መልኩ ሰፊ ንግግር አድርገዋል።
በመቀጠል የተለያዩ አሸናፊን የሚገልፁ ንግግሮች በተለያዩ አካላት ከቀረቡ በኃላ ሀያ አንድ ደቂቃ የዘለቀ ዘጋቢ ፊልም ታይቷል። ለዚህ ፕሮግራም መሳካት ድጋፍ ላደረጉ የተለያዩ አካላትም የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።
በዚህ የእውቅና መድረክ ለአሸናፊ በጋሻው የ12 ቁጥር ማልያ በመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከተበረከተለት በኃላ የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ ኮሚቴ ለአሸናፊ የዋንጫ እና በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሚገኙ የአሸናፊ ወዳጆች የተሰበሰበውን 950,000 (ዘጠኝ መቶ አምስት ሺህ ብር) የገንዘብ ሽልማት አበርክተውለታል።
የአሸናፊ በጋሻው በመልዕክቱ ዕንባ እየተናነቀው ” ይህ ሽልማት ለኔ ብቻ የተበረከተ አይደለም። ለብዙዎች በዚህ ሂደት ላለፉ ወደፊትም ለሚያልፉ ተጫዋቾች የተደረገ ነው። በቀጣይነት እንዲህ ያሉ መድረኮች መመቻቸት አለባቸው። ለአንድ ክለብ መታመን ትርፉ ምን እንደሆነ አይታችኋል። በመጨረሻም ይህን መድረክ ላመቻቹ በሀሳብ በገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ በታላቅ ክብር አመሰግናለው።” ብሏል።
በዕለቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የሆኑት አቡበከር ናስር እና ሚኪያስ መኮንን ወደ መድረኩ ቀርበው የተሰማቸውን ስሜት ከገለፁ በኃላ ከአሸነፊ በጋሻው ለሁለቱ ወጣት ተጨዋቾች የአደራ መልዕክት አስተላልፏል “በቀጣይ እኔ በቡና ማልያ ዐሥራ አራት ዓመት በመጫወት የተያዘውን ሪከርድ መስበር አለባችሁ” በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መለያን በአደራ ሰጥቷቸዋል።
በመጨረሻም አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ የካፍ የአሰልጣኞች ስልጠና ወደ ኢትዮጵያ እድሉ ሲመጣ አሸናፊ በጋሻው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የ “ቢ” ኮርሱን እንደሚወስድና ፌዴሬሽኑ ይህን ዕድል እንደሚያመቻች ተናግረዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!