የሰማንያዎቹ … | ታማኙ አሸናፊ በጋሻው

ለአንድ ክለብ እስከ መጨረሻው ታምኗል። እርሱ ከግብ ጠባቂነት እስከ አጥቂነት በፍፁም ታዛዥነት ለቡና ተጫውቷል። በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዘንድ እጅግ ይወደዳል፣ እርሱም ኢትዮጵያ ቡናን ይወደዋል። ይህ የሰማንያዎቹ ሁለገብ ድንቅ ተጫዋች አሸናፊ በጋሻው ማነው?

ሶከር ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተነሱ በእግርኳስ ውስጥ ትልቅ አበርክቶ የነበራቸውን የቀድሞ እግርኳስ ተጫዋቾች ያለፉበትን የእግርኳስ ህይወት ፣ ስኬት፣ ገጠመኝ እና ተሞክሮ በዘጠናዎቹ ኮከቦች በተሰኛው አምዷ ስታስቃኛችሁ መቆየቷ ይታወቃል። ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ በሣምንት አንድ ጊዜ ዘወትር እሁድ የሰማንያዎቹ ኮከቦች በሚል አዲስ አምድ ስር የእናተን የአንባቢዎቿን ፍላጎት ለማርካት ከአሸናፊ በጋሻው ጀምራለች።

ለእግርኳስ ከተፈጠሩ ምርጥ ተጫዋች አንዱ የነበረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሚሊዮን በጋሻው ታናሽ ወንድም ነው። ኮልፌ በሚገኙ በርካታ ሜዳዎች መኖራቸው እና የታላቅ ወንድሙ ለእግርኳስ መሰጠት አሸናፊን ወደ እግርኳሱ ሳይስበው እንዳልቀረ ይገመታል። በ1977 ኢትዮጵያ ቡና እና አሸናፊ በጋሻው ላይለያዩ አብረው እስከ ህይወት ፍፃሜ ሊተሳሰሩ በክለቡ ታሪክ የመጀመርያ ሆኖ በተቋቋመው የ “ቢ” ቡድን ውስጥ አባል ሆነ። ቀኝ መስመር ተከላካይ በመሆን በታዳጊ ቡድን ውስጥ መጫወት የጀመረው አስራ ሁለት ቁጥር ለባሹ አሸናፊ ከሁለት ዓመት የተስፋ ቡድን ቆይታ በኃላ ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ወደ ግብፅ አቅንተው ተጫዋቾች ሲጠፉ በጎደለው ቦታ ተተክቶ እንዲጫወት (ነፍስ ሄር) ጋሽ ሥዩም አባተ በ1979 ወደ ዋናው ቡድን አሳድገውታል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከስንት አንዴ የሚገኘውን ክስተት መጠቀም የቻለው አሸናፊ የቀኝ እና የግራ መስመር፣ የመሐል ተከላካይ፣ የተከላካይ አማካይ ፣ ቀጥተኛ አጥቂ እና በአንድ አጋጣሚ ለአስራ አምስት ደቂቃ ያህል ደግሞ ግብጠባቂ በመሆን አሰልጣኞቹ የሚያዙትን ሁሉ በፍፁም ታዛዥነት ሲፈፅም ቆይቷል።

ቀልድ አዋቂው እና ከራሱ ስም እና ጥቅም ይልቅ ለሚወደወዱት ክለብ ራስን መስጠት እንደሚገባ በፅኑ የሚያምነው ሁለገቡ ተጫዋች አሸናፊ በጋሻው በታዳጊ ቡድን ሁለት ዓመት በዋናው ቡድን ደግሞ በሚለብሰው መለያ ቁጥር አስራ ሁለት ዓመታት በድምሩ ለአንድ ኢትዮጵያ ቡና አስራ አራት ዓመታትን መጫወት ችሏል። በዚህም ቆይታው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከማሳካቱ በተጨማሪ የግብፁን ኃያል ክለብ አል አህሊን በደርሶ መልስ ውጤት ከውድድሩ ውጪ ባደረገው የቡና ስብስብ ውስጥ ነበር። ሌላው በኢትዮጵያ ቡና ታሪክ የመጀመሪያውን የምስራቅ እና መካከለኛው የክለቦች የአፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የንሐስ ሜዳልያ ባመጣው ቡድን አባላት ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚወስደው አሸናፊ በጋሻው ነው።

በኢትዮጵያ ቡና ወደ መጨረሻው አካባቢ አብሮት የተጫወተው አንዋር ያሲን (ትልቁ) አሸናፊ በጋሻው ለእርሱ ምን ዓይነት ተጫዋች እንደነበር እንዲህ በማለት ይገልፀዋል ” አሸናፊ በቡና አስራ አራት ዓመት በጥሩ አቋም መጫወት የቻለ ነው። በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችሎታውን እያሻሻለ የመጣ ነው። ሲጀምር ተከላካይ ሆኖ ከዛ ወጥቶ የተከለካይ አማካይ ፣ አጥቂ ፣ ግብጠባቂ ተጎድቶ ሲወጣ ግብጠባቂ ሆኖ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለው ሰው ነበር። አሸናፊ ተጫዋች በነበረበት ጊዜ አንድ የነዳጅ ማደያ ማስታወቂያ ነበር። ‘ማደያችን በየጊዜው እየተሻሻለ አገልግሎት መስጠት ላይ ይገኛል’ ይላል። አሸናፊ ቡና ውስጥ እንዲህ ነው። ከቀን ወደ ቀን የርሱ ጠቃሚነት ጎልቶ ወሳኝ ተጫዋችነቱ እየጨመረ ለቡድኑ ያለው ተቆርቋሪነትም እያደገ የመጣ ለቡና በብዙ ነገሩ ተምሳሌት የሆነ ልጅ ነው።” ለአንድ ክለብ ታምኖ መጫወት የተራራ ያህል በገዘፈበት በዚህ ዘመን አሸናፊ ለብዙዎች ምሳሌ ሊሆን በሚችል መልኩ በደስታውም በኃዘኑም ከኢትዮጵያ ቡና (ቡና ገበያ) ጋር የአስራ አራት ዓመታትን ቆይታ አድርጎ በ1991 መጨረሻ ላይ ከእግርኳስ ዓለም ራሱን አግልሏል።

የቀድሞ ደጋፊ የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኀበር ፕሬዝደንት የሆነው የህግ ባለሙያው አቶ ክፍሌ አማረ አሸናፊ ሲናገር “የቡና የጀርባ አጥንት የሆነ ደጋፊ ነው። ተጫዋች መሆኑን ብቻ አይደለም የማስበው። እንደ ተጫዋች የማየው ከሆነ ለቡድኑ ብዙ መስዕዋትነት የከፈለ ለሙያው የተሰጠ ፣ አሰልጣኞች የሚሰጡትን ትዕዛዝ እና ግዴታዎችን ሁሉ የሚወጣ ወታደር ነው። ከሜዳ ውጪ በሥነ-ምግባሩ የተመሰከረት በሙያው የታማኝነት እና የፅናት ተምሳሌት ነው። ቡና ሊፈርስ በተቃረበበት ወቅት ‘የክለቤን መጨረሻ አላይም። የክለቤን መትረፍና መኖር መጨረሻ ሳላይ የትም አልሄድም’ ብሎ ከደጋፊዎች ጋር ሆኖ አሁን ያለው አደረጃጀት እንዲኖረው ያደረገ የቡና ተምሳሌት ነው “። ሲል ይናገራል።

አመለሸጋው የእግርኳስ ሰው አሸናፊ ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። ኢትዮጵያ ቡና ሊፈርስ በተቃረበበት ወቅት በ1987 ላይ በጥቅማጥቅም በኩል በተሻለ ክፍያ እንውሰድህ ያሉ ታላላቅ ክለቦች ቢኖርም ‘የቡናን መጨረሻ ሳላይ የትም አልሄድም !’ በማለት በወቅቱ ከነበሩ ደጋፊዎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ቡናን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ቡና ከመፍረስ ተርፎ ዛሬ ይህ ሁሉ ደጋፊ መፈጠር የተቻለው እርሱ በለበሰው አስራ ሁለት ቁጥር መለያ ነው። በሚል የደጋፊው መለያ አስራ ሁለት ቁጥር እንዲሆን በማድረግ ትውልድ አልፎ ትውልድ እስኪተካ ድረስ አሸናፊ ሁሌም የሚታወስበት ታሪክ ተቀምጧል። ዛሬ በጀመርነው የሰማንያዎቹ ከዋክብት አምድ እንግዳችን የሆነው አሸናፊ በጋሻው በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አካፍሎናል።

“ስኬት በብዙ መንገድ እንደ ሰው ዕይታ ሊለያይ ይችላል። ለኔ በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ አሳካሁት የምለው በአንድ ክለብ ማለያ መጫወትን እና የኔ የመለያ ቁጥር ’12’ የደጋፊው ቁጥር መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያው የሴካፋ የክለቦች ዋንጫ ላይ የነሐስ ሜዳልያ ማግኘታችን እንዲሁም እስካሁን በማንም ያልተደፈረውን የግብፁን ኃያል ክለብ ከውድድሩ ውጪ ያደረግንበት ሁኔታ ለኔ በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ ካሳካሁት ስኬት ቀዳሚነቱን ይወስዳሉ። እነዚህ በኢንተርናሽናል ደረጃ ያስመዘገብናቸው መልካም ውጤቶች ብዙ ደጋፊዎችን ወደ ክለቡ ያመጣንበት በመሆኑ ለኔ የተለየ ቦታ የምሰጣቸው ስኬቶቼ ናቸው።

“ይሄን ሁሉ ቦታ ሸፍኜ ለመጫወት የቻልኩበት ምክንያት በወቅቱ የነበሩ አሰልጣኞቼ የሚሰጡኝ ምክር እና በኔ ባላቸው ዕምነት ኃላፊነቴን ለመወጣት ሙሉ ፍላጎት ስላለኝ ነው። ሌላው ተጫዋች እስከሆንኩ ድረስ በራስ መተማመኔን ከፍ አድርጌ ሁሉም ቦታ መጫወት እችላለው የሚል በራሴ ከፍተኛ ዕምነት ስላለኝ ለዛም ይመስለኛል። የኔ ቦታ ይህ ብቻ ነው የሚል ዕምነት የለኝም። የሚሰጠኝን ሁሉ መፈፀም አለብኝ ፤ ቡድኔን እስከጠቀመው ድረስ። ደግሞም አንድ ተጫዋች በየትኛውም መንገድ አሰልጣኙ የሚሰጡትን ነገሮች ሁሉ ተቀብሎ እና አምኖ የመተግበር እና ራሱን የማዘጋጀት ግዴታ አለበት። በእግርኳስ የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ ሁሌም ለየትኛውም ታክቲክ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። አንድ ተጫዋች ስኬታማ ለመሆን ከራሱ ውጤት ይልቅ ሁሌም የቡድንን ውጤት ማስቀደም ይገባዋል።

“የመጀመርያ በአጋጣሚ ከመብራት ኃይል ጋር ስንጫወት ዋናው ግብ ጠባቂ ፈቱሼ በጉዳት ምክንያት አልተሰለፈም ነበር። የፈቱሼ ተጠባባቂ የነበሩት ሁለት ግብ ጠባቂዎች ንጉሴ እና ታሪኩም በተለያየ ሰዓት በአንድ ጨዋታ ላይ ተጎድተው ይወጣሉ። በዚህ ሰዓት ምንም አማራጭ ያልነበረው ጋሽ ሥዩም አባተ ግብጠባቂ ሆኜ እንድጫወት አዘዘኝ ይሄን ተግባራዊ አድርጊያለው፤ ከእኔ ይልቅ የቡድን ውጤት ስለሚቀድም።

“ከሌሎች ክለቦች እኔን የመውሰድ ጥያቄዎች ነበሩ። በተለይ ቡና ሊፈርስ በተቃረበበት በ1987 ብዙ ጥያቄዎችን አስተናግጃለው። ሆኖም ቅድሚያ የምሰጠው እና የማልደራደርበት ኢትዮጵያ ቡና ሊፈርስ ተቃርቦ ጥየው ብሄድ የዘላለም የህሊና ፀፀት ይሆንብኝ ነበር። ቡና እንደማይፈርስ በውስጤ ዕምነት ስለነበር እና አንዳንድ ለቡና ፍቅር ያላቸው መስዋዕትነት የከፈሉ ደጋፊዎችን ስመለከት እኔ በሌላ ክለብ ሄጄ ከማገኘው ጥቅም ይልቅ እነርሱ ለቡና የከፈሉትን መስዋዕትነትን በማሰብ በቡና ቆይቼ ያንን ጥቅም ባጣ ይሻለኛል ብዬ በቡና ቆይቻለው። የዚህን መታመን ውጤቱን ደግሞ አሁን በበቂ ሁኔታ አግኝቼዋለው።

“በተጫዋችነት ዘመኔ ይህን አላደረኩም ብዬ የምቆጨው ለምሳሌ የኛ ተቀናቃኝ (ተወዳዳሪ) የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሲሆን እና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በተደጋጋሚ ሲወስድ እኛ ያንን ዋንጫ ባለማግኘታችን በጣም የሚቆጨኝ ነገር ነው።

“በእርኳስ ብዙ ገጠመኞች ቢኖሩኝም አንዱን ላንሳ።በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ብዙም ግምት ሳይሰጠን ነበር የተጓዝነው። ከተጋጣሚ ቡድን ጋር ካለው ችግር የተነሳ ቁርስ እና ምሳ እየበላን በከፍተኛ ተጋድሎ ለፍፃሜ ዋንጫ ለማለፍ ብንደርስም ተሸንፈን ለሦስተኛ ደረጃ ለመጫወት ተገደን ነበር። የደረጃ ጨዋታውን አሸንፈን ሜዳልያው የሚበረከትልን በንጋታው እሁድ ከፍፃሜው ጨዋታ በኃላ ስለነበረ ለአንድ ቀን የማደሪያ እና ለምግብ መክፈል የሚያስችል ገንዘብ በማጣት ያንን ሁሉ ቀን የለፋንበትን ሜዳልያችንን ሳንቀበል ወደ ሀገር ቤት የተመለስንበት አጋጣሚ መቼም የማረሳው ነው።

“ታላቅ ወንድሜ ሚሊዮን በጋሻው በጣም ዲሲፒሊንድ የሆነ ፣ ለቡድኑ መስዕዋትነት የሚከፍል ፣ ጠንካራ እና ታላቅ ተጫዋች ነው።

“ለአንድ ክለብ ታምኖ መጫወት ባለው ጠቀሜታ በእኔ እምነት ጊዜው ይርዘም እንጂ ዋጋህን ታገኛለህ። ከደጋፊው ትልቅ አክብሮት እና ታማኝነት እንዲኖርህ ያደርጋል። ጊዜው የቱንም ያህል ይሂድ እንጂ አንድ ቀን ትታወሳለህ ብዬ አምናለው። ክለብህን በአንዳንድ ተናንሽ ጥቅማጥቅሞች አሰልፈህ መስጠት አግባብ አይደለም። ስለዚህ ተጫዋቾች ለክለባቸው ታምንው ቢጫወቱ መልካም ነው እላለው።

” ለኢትዮጵያ ቡና ታማኝ ሆኜ እንድጫወት ምክንያት የሆነኝ በሚገርምህ ሁኔታ የቅርብ ደጋፊዎቹ ናቸው። አሁን በህይወት ያሉም የሌሉም አሉ እነዛ ለቡና ፍቅር ያላቸው ፣ መስዕዋትነት የሚከፍሉ ጥቂት ደጋፊዎች ናቸው። ለቡና ታማኝ ሆኜ በፍቅር እንድጫወት አድርጎኛል። ለአንድ ክለብ ታምኜ መጫወቴ ብድሩን አሁን አግኝቻለው። ከኔ ጋር በቡና ቤት አብውኝ የተጫወቱ ትልልቅ ተጫዋቾች አሉ። እኔን ለየት የሚያደርገኝ እኔ ስጫወት እለብሰው የነበረው ’12’ ቁጥር መለያ ለደጋፊዎች ሲሰጥ እና ሁልጊዜ መለያውን በለበሱት ቁጥር እኔን ማስታወሳቸውን በመስማቴ እና በማየቴ ትልቅ ደስታ እና ክብር ነው የተሰማኝ። ይህ ደግሞ በዚህ ዘመን ላሉት እና ወደፊት ለሚመጡት ትውልዶች ትልቅ መልዕክት አለው።

“አሰልጣኝ የመሆን ዕቅድ አለኝ። የወጣትነት የጎልማሳነት እድሜዬን ያሳለፍኩት በእግርኳስ ነው። ስለዚህ ይሄንን ልምዴን እንደገና በማሰልጠን አሁን ባለው ትውልድ ላይ አሻራዬን ብጥል እጅጉን ደስ ይለኛል።

“አልፎ አልፎ አሁን ያለውን እግርኳስ እከታተላለው። መስተካከል ያለበት በየሁለት ዓመቱ ከክለብ ወደ ክለብ የመቀያየር ሁኔታ አለ። ይህ ከኛ ዘመን ትንሽ ለየት ያለ ነው። እንጂ በእግርኳስ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሁለቱም ዘመን የራሳቸው አሻራ አላቸው።

“በቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር እና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነኝ። ዕድሜያቸው የስምንት እና የሁለት ዓመት ስለሆነ ገና ወደ እግርኳሱ አልገቡም። የተወሰነ ይሞካክራሉ ወደፊት ይቀጥሉበታል በዬ አስባለሁ። እኔን ለመተካት ይጫወታሉ የሚለውን ከጊዜ በኃላ የምናየው ይሆናል።

“ለኔ የተዘጋጀው የዕውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም እግርኳስን ካቆምኩ ከሃያ ዓመት በኃላ ይሄን ታላቅ ክብር በማዘጋጀታቸው በኢትዮጵያ የመጀመርያው ይመስለኛል። ኳስ ተጫዋች ካቆመ በኃላ የምስጋና ፕሮግራም ሲካሄድለት እኔ የመጀመርያው ሳልሆን አልቀርም። በዚህም በጣም ዕድለኛ ነኝ። ከእኔ በላይ ብዙ ያገለገሉ እና የለፉ ተጫዋቾች ይኖራሉ። ከምለው በላይ እጅጉን ደስተኛ ነኝ። ይህን ፕሮግራም በማስተባበር ለተሳተፉት ሁሉ ትልቅ ክብር አለኝ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ