መረጃው ከስፖርት ኮሚሽን የተገኘ ነው።
በሀገራችን የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሲባል ስፖርታዊ ስልጠናዎች፣ ውድድሮች በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ መደረጉ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም የስፖርት ኢንደስትሪው ክፉኛ ተጎድቷል፣ ክለቦች የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፣ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች የሥነ ልቦና እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ወድቀዋል፡፡
በመሆኑም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የስፖርት እንቅስቃሴውን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እና የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ /ፕሮቶኮል/ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል ፡፡
በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሰው እንዳሉት ማነኛውም ሰው ለመኖር ኦክስጅን እንደሚያስፈልግ ሁሉ ስፖርት ለጤናችን ምን ዓይነት ዋጋ እንዳለው ከኮሮና ወረርሽኝ ለማገገም ባደረግነው ሂደት ተምረናል። በመሆኑም ሁሉም ህብረተሰብ ስፖርትን ሊያዘወትር እና ባህሉ ሊያደርገው እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ምንም እንኳ በችግር ውስጥ ብንሆንም ችግሩን ተቋቁመን ስፖርቱን ልናስቀጥል ይገባል፤ ለዚህም ስፖርቱ በሚጀምርበት ሁኔታ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡ ተገቢነት ያለው መሆኑን ሚንስትሯ ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በበኩላቸው የተለያዩ የዓለም ሀገራት የኮሮና ወረርሽኝ ላልታወቀ ጊዜ እንደሚቆይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ወረርሽኙን ከመከላከል ጎን ለጎን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጠቁመው፤ በእኛ ሀገር ሁኔታም ከዚህ በተራዘመ ጊዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መጀመር በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ሊያስከትል የሚችለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ ችግር ከፍተኛ ነው ብለዋል። በመሆኑም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ስልጠናዎች ፣ ውድድሮች እና የአካል በቃት እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መመሪያው አጠቃላይ የስፖርት እንቅስቃሴ በምን ሁኔታ መከናወን እንዳለበት የሚያሳይ ሲሆን የስፖርት ተቋማት/ ማኅበራት እንደ ስፖርታቸው ባህሪና ተጨባጭ ሁኔታ እና የሚሰጡት አገልግሎት የጥንቃቄ እና የአሠራር ሥርዓት ሊያዘጋጁ እንደሚችሉ ያመላክታል።
በተለይም ስልጠናዎች ሲጀመሩ ደረጃ በደረጃ በግልና በቡድን አነስተኛ ተሳታፊ ቁጥርን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ፣ የስፖርት ማህበራት አካዳሚዎች ፣ ክለቦች ፣ ማዕከላት ለበሽታ ያላቸውን ተጋላጭነት ባገናዘበ መልኩ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። እንዲሁም ወደ ስልጠና እና ወድድር የሚገቡ አካላት ምርመራ ማድረግ ፣ የንፅህና መጠበቂያ መጠበቂያዎችን መጠቀም እና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያገለግሉ ቦታዎች ፣ ቁሳቁሶች እና መሳሪያዎች ንፅህናቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ መመሪያው አስቀምጧል። መመሪያው የባለድርሻ አካላትን ሚና ከማስቀመጡ ባሻገር ስፖርቱን ወደነበረበት ለመመለስ ተጨማሪ በጀት ፣ የምርመራ ቂሳቁስ ፣ የስልጠና ካምፕ እና ትራንስፖርት አገልግሎት እና መሰል ችግሮች ሊገጥም እንደሚችል አመላክቷል።
በኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ተዘጋጅቶ ከቀረበው ረቂቅ መመሪያ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን በኮቪድ ውስጥ ሆነን እንዴት ስፖርቱን ማስቀጠል እንችላለን የሚል ዕቅዳቸውን አቅርበዋል። የቀረቡ ሰነዶችን መሠረት በማድረግም ተሳታፊዎች በተለይ በአሁኑ ሰዓት ስፖርቱን ማስጀመር እንችላለን አንችልም ፣ ስፖርቱ ከተጀመረ የተመልካች ፣ የበጀት ፣ ተጨማሪ የሰው ሀይል እና ሀብት ያስፈልጋል ይህን እንዴት እንፈታዋለን በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል
በመድረኩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሰው፣ የኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች እና ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ እና የቋሚው ኮሚቴ አባላት፣ የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ፕረዚዳንቶች እና የጽ/ቤት ኃላፊዎች ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ኮሚሽነሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!