“እውቅና መስጠት የሚያስወጣው ነገር የለም፤ የሚያስገኘው ግን ብዙ ነው” አቶ ኢሳይያስ ደንድር

በትናንትናው ዕለት ለአሸናፊ በጋሻው የተካሄደው ደማቅ የእውቅና አሰጣጥ መርሐግብርን አስመልክቶ የኮሚቴው አስተባሪ የነበሩት አቶ ኢሳይያስ ደንድር ይናገራሉ።

በህይወት ያሉ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋቾችን የማመስገን እና እውቅና የመስጠት ዝግጅት ባልተለመደበት ሁኔታ በትናንትናው ዕለት ለብዙዎች የስፖርት አካላት አስተማሪ በሆነ መልኩ ለቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሸናፊ በጋሻው በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል የተለያዩ የእግርኳሱ ሰዎች በታደሙበት እጅግ ባማረ ሁኔታ ተካሂዷል። ይህ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በማስተባበር ከፍተኛውን ሚና የተወጡት አንዋር ያሲን (ትልቁ)፣ አንዋር ሲራጅ (ትንሹ)፣ ፈቀደ ትጋ (ቲጋና)፣ ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር፣ ክፍሌ አማረ እና አብዱራህማን መሐመድ (አቡሸት) ናቸው። ይህ የእውቅና ፕሮግራም ለማካሄድ የታሰበበትን ምክንያት እና በቀጣይ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በሌሎች የእግርኳስ ባለውለታዎችን እውቅና ለመስጠት ምን እንደታሰበ ከአቶ ኢሳይያስ ደንድር ጋር ቆይታ አድርገናል።

ለአሸናፊ በጋሻው የተዘጋጀው የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራምን ለማካሄድ መነሻ ምክንያታቹ ምንድነው ?

እንደሚታወቀው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ፕሬዝደንት በነበርኩበት ወቅት በመብራት ኃይል እግርኳስ ከምስረታው ጀምሮ በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያደረጉ ከ13 በላይ ሰዎችን በተደራጀ ሁኔታ ባይሆንም የእውቅና ትንሽ የለውም በሚል ቢያንስ በዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ (በየሩብ ዓመቱ) እውቅና ስንስጥ ቆይተናል። ጅማሬያችን በማስተር ቴክኒሻን ጋሽ ሀጎስ ደስታ፣ ጋሽ ወንድማገኝ ከበደ፣ ዘሪሁን ተክሌ (ቢረጋ) ከደጋፊዎች በቀለ ሄኒ (ኮረንቲ)፣ ጋሽ ሁሴን ፣ ከተጫዋቾች ጋሽ በላይ አብርሀ (የኤልፓ የመጀመርያው አንበል)፣ ጋሽ ተስፋዬ ተክሉ፣ አፈወርቅ ኪሮስ እውቅና ስንሰጥ ቆይተናል። አሁንም አሸናፊ በጣም የምናከብረው የኢትዮጵያ ቡና እና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እንዳጋጣሚ የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ ተገናኝተን ስንጨዋወት እንደሚታወቀው አሸናፊ ብዙ የማያወራ ትልቅ ስብዕና ያለው ጭምት የሆነ፣ ሰው አክባሪ ተጫዋች ነው። ይህ ሰው ለደከመው ድካም በእግርኳሱ ላበረከተው ሥራ እውቅና ሊሰጠው ይገባል በሚል ሀሳቡን አመጣሁና ከሌሎች አብረውኝ ከሰሩ የኮሚቴ አባላት ጋር ተነጋግረን በሁሉም ሰው ጭንቅላት ውስጥ የነበረ በመሆኑ ሁሉም ደስተኛ ሆኖ ወደ እንቅስቃሴ ገባን። በኃላም ባለ ስምንት ገፅ ሰንድ አዘጋጅቼ ከዛሬ ሦስት ወር በፊት ይህን ፕሮግራም ለማድረግ ሥራዎችን መስራት ጀምረናል።

የተዘጋጀው ሰነድ ምን ላይ ያተኮረ ነው?

አሸናፊ በጋሻው ማነው? የፕሮግራሙ ዓላማው ምንድነው? ከዚህ የሚገኘው ውጤት ምንድነው? መርሐግብሩ እንዴት ነው የሚቀጥለው የሚል እና በመጨረሻው የማጠናቀቂያ ሥራ ላይ ለአሸናፊ ገንዘብ ሰብስበህ ዘጠኝ መቶ አምስት ሺህ ብር መስጠት ብቻ አይደለም። በዚህ ገንዘብ ምን ሊሰራ ይችላል የሚለውን እስከማገዝ፣ ወደ ሥራ እንዲገባ የተዘጋጀ ሰነድ ነው። የሰጠነውን ገንዘብ ጨረሰው የሚል ነገር ማውራት ለሁላችንም አይጠቅመንም በሚል ልናግዘው በሚያስፈልጉ ነገሮች ከጎኑ እንድንሆን የተዘጋጀ ሰነድ ነው።

የተጫወተበት ክለብ ኢትዮጵያ ቡና በዚህ እውቅና አሰጣጥ ተግባር ላይ የነበረው ተሳትፎ እንዴት ነው?

እውቅና ሲሰጥ የሚሰጠው አካል ይወስነዋል። ለአሸናፊ ይህን እውቅና ማነው የሚሰጠው እኛ ብንሰጠው እግርኳሱን እንደሚወድ እንደ ጓደኛ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቢሰጠው ግን ለርሱ የተለየ ስሜት ይኖረዋል። እኛ የማይታይ እጅ ሆነን ነው መስራት የምንፈልገው። በማለት የክለቡን አመራሮች አነጋገርን አቶ ክፍሌ አማራ ከቡና ተወክሎ አብሮን ሲረዳን ቆይቷል።

ይህ እውቅና የመስጠት ጉዳይ ቀጣይነት አለው ?

ይህ ኮሚቴ ጊዜያዊ ነው። የአሸናፊን ጉዳይ ብቻ ይዞ የተነሳ ኮሚቴ ነው። ይሄ ቢሆንም ከዚህ ሥራ ተነስቶ በዋናነት ይህን ተግባር በሥራቸው፣ በእቅዳቸው አካተው መንቀሳቀስ ያለባቸው አካላት አሉ። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ የተጫዋቾች ማኀበር፣ ክለቦች ሌሎችም የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ መሳተፍ አለባቸው። እውቅና መስጠት በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ብቻ መለካት የለበትም። ጎበዝ፣ ለሰራህው ስራ እናመሰግናለን ማለትም እውቅና ነው። እውቅና ለመስጠት ፍላጎት እና ቀናነት ይፈልጋል እንጂ የተለየ ነገር አይጠይቅም። ስለዚህ በሌሎች ይህ ሀሳብ መለመድ አለበት።

እውቅና መስጠት ጠቀሜታው ምንድነው ?

እውቅና መስጠት ለእዛ ሰው የሠራኸው ሥራ ጥሩ ነው ከማለት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ሰው በሥራው ሂደት ውስጥ መቼም ሰው ብቻውን የቆመ አይደለም። ብቻውን አይሰራም ቤተስብ፣ ጓደኛ፣ ሲወድቅ ሲነሳ፣ ሲሸነፍ፣ በእግርኳሱ ሲጎዳ አብሮ የተጨነቀ በቅርብ ሆኖ የሚያይ የሚያግዝ ሰው ይኖራል። እውቅና ስትሰጥ እነዚህን ሁሉ ሰዎች የበለጠ ከዛ ሰው በላይ ማስደሰት ነው። ሌላው እውቅና መስጠት የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ ለማነሳሳት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። እውቅና መስጠት የሚያስወጣው ነገር የለም፤ የሚያስገኘው ግን ብዙ ነው። ለዛ ሰው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እንዲህ ያለ ነገር አለ ብለው መነሳሳትን ይፈጥራል። እንደምታቀው አሸናፊ ኢትዮጵያ ቡና ብቻ ተጫውቶ ያለፈ ነው። አሁን ለምሳሌ እኔ በግሌ የኤልፓ አመራር የነበርኩ ደጋፊም ጭምር ነኝ። ጥሩ ነገር ለማድረግ የ”X” ክለብ ወይም የ”Y” ክለብ አባል መሆን አይጠበቅብህም። እውቅና ለሁሉም የሚያስፈልግ በጎ ሀሳብ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!