የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የተጫዋቾችን ዝውውርን በተመለከተ ሃሳብ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ውድድሮች የሚጀመሩበትን መንገድ በተመለከተ የመነሻ ሰነድ አዘጋጅቶ ለክለቦች እያቀረበ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም ፌዴሬሽኑ በሁለቱ የሊግ እርከኖች ላይ የሚሳተፉ የሴቶች ክለብ ተወካዮችን በካፍ የልህቀት ማኅከል ሰብስቦ መነሻ ሰነዱን አቅርቧል። ሰነዱ ከቀረበ በኋላም የፌዴሬሽኑ ክቡር ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ ጎን ለጎን ስለተጫዋቾች ዝውውር አስተያየታቸውን በሥፍራው ለተገኙ ተሰብሳቢያን አጋርተዋል።
“ሁላችሁም ማወቅ ያለባችሁ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተጫዋቾች የዝውውር መስኮትን እንዳልከፈተ ነው። በተለያዩ መንገዶች ክለቦች ተጫዋቾችን እያዘዋወሩ እንደሆነ እንሰማለን። ግን ይህ ምንም ህጋዊ እውቅና የለውም። እኔ እንደውም ክለቦች ዝም ብለው እየለፉ ያሉ ነው የሚመስለኝ። ይባስ ብሎ በየካፍቴርያዎች እና ምግብ ቤቶች ተጫዋቾችን እያስፈረማችሁ እንደሆነ በፎቶ በታገዘ መረጃ እንሰማለን። ይህ በጣም የሚገርም ነው። ለተጫዋቾች ክብር ይኑራችሁ። እስከማቀው ድረስ ሁሉል ክለብ ቢሮ አለው። ምናለ ቢሮ ወስዳችሁ በክብር ብታስፈርሟቸው። ይህ በጣም አሳፋሪ ነው። ቀድሜ እንዳልኩት ግን የዝውውር መስኮቱ ሳይከፈት የሚደረጉ ሩጫዎች ተቀባይነት የላቸውም። አይደለም ካፌዎች ውስጥ ቤተ-መንግሥት እና ፍርድ ቤት ውስጥ ያስፈረማችኋቸው ውሎች ዋጋ የላቸውም። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ አስቡበት።”
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም የክለብ አመራሮች ለእግርኳሱ የሚገባውን ክብር ለመስጠት ጥቃቅን ነገሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። “ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ነገርግን የእግርኳስን ክብር የሚያጎድፉ ነገሮችን ከማድረግ ብትቆጠቡ መልካም ነው። እርግጥ መሻሻሎች አሉ። አሁን ላይ ስብሰባዎች ላይ የሚኖሩ ሃሳቦች በክብረ ነክ ንግግሮች ታጅበው እና ማይክራፎን በመቀማማት አይደለም የሚሰነዘሩት። ይህ ጥሩ መሻሻል ነው። ግን ሌሎች እንደዚ ትንሽ የሚመስሉ ነገርግን የእግርኳስን ክብር የሚያቆሽሹ ነገሮች አሁንም አሉ። ሜዳ ላይ ኳስ ስንመለከት እንኳን ያደፈ ማሊያ የለበሰን ተጫዋች በቀላሉ እንለያለን። ይህ መሆን የለበትም። ስለዚህ ትንሽ የሚመስሉ እና በቀላሉ መስተካከል የሚችሉ ነገሮችን እያረምን ብንሄድ ለእግርኳሱ ጥሩ ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!