የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች የሚጀመሩበትን ሂደት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት የመነሻ ሰነድ ቀርቧል። ሰነዱ ከቀረበ በኋላም ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጀውን የውድድር ማስጀመሪያ የመነሻ ሰነድ ለክለቦች እያቀረበ ይገኛል። የዛሬ ሁለት ሳምንትም ፌደሬሽኑ የወንዶች ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ እና አንደኛ ሊግ ክለቦችን በሁለቱ የሊግ እርከን ከሚገኙ የሴቶች ክለብ ተወካዮች ጋር በጋራ በመጥራት ውድድሮች ሊጀመሩ የሚችሉበትን የመነሻ ሰነድ አቅርቦ ነበር። በጊዜውም ከወንዶች ፕሪምየር ሊግ ክለቦቸ ጋር ስብሰባውን የተካፈሉት የሴት ክለብ ተወካዮችም እነሱን ያማከለ አቅጣጫ ከመድረኩ ሳይነሳ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር። ከስብሰባውም በኋላ እነዚህ የሴቶች ክለብ ተወካዮች ለብቻቸው ሲመካከሩ የፌዴሬሸኑ ክቡር ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተገኝተው እነሱን ፌዴሬሽኑ እንደሚያግዝ እና በቅርቡ እነሱን የዋጀ ሰነድ ተዘጋጅቶ ጥሪ እንደሚደረግላቸው ቃል ገብተው ተለያይተው ነበር። ፕሬዝዳንቱ ቃል የገቡት ቀን ደርሶም በዛሬው ዕለት በሁለቱ የሊግ እርከን (ፕሪምየር ሊግ እና አንደኛ ዲቪዚዮ) የሚገኙ የክለብ ተወካዮች በካፍ የልህቀት ማኅከል ጥሪ ተደርጎላች ሰነዱ ቀርቦላቸዋል።
መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መጀመሪያ ከወንዶች ጋር ጥሪ የቀረበላቸው እግርኳሱን በፆታ ላለመለየት እና ፌዴሬሽኑ ለሁለቱት የፆታ ውድድሮች እኩል ዐይን እንዳለው ለማሳየት እንደሆነ ጠቁመው ስብሰባውን አስጀምረዋል። ሃላፊው አክለውም ዛሬ ለብቻቸው የሴቶች ቡድን ተወካዮች የተጠሩት ከወንዶች ጋር ሲሰበሰቡ ከመድረኩ የተቀመጠው አቅጣጫ እነሱን ያማከለ ሆኖ ስላላገኙት እና የሴቶች ውድድር በባህሪው ከወንዶች ስለሚለይ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከጽሕፈት ቤቱ ሃላፊው የመክፈቻ ንግግር በኋላ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስለመነሻ ሰነዱ መጠነኛ ገለፃ በማድረግ ሃሳባቸውን ቀጥለዋል።
“የስፖርት ኢንዱስትሪው በኮቪድ-19 ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ቆሟል። በዚህም ባለፉት 5 ወራት በዚህ ኢንዱስትሪ የሚኖሩ እና የሚጠቀሙ ግለሰቦች ሲጎዱ ቆይቷል። ከዚህ መነሻነት ፌዴሬሽናችን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እግርኳስን የምናስጀምርበትን የመነሻ ሰነድ ስናዘጋጅ ቆይተናል። ባለፈው እናንተን አካተን የወንዶችን ፕሪምየር፣ ከፍተኛ እና አንደኛ ሊግ ክለቦችን ጠርተን ነበር። ዛሬም ከእናንተ ጋር በደንብ እንወያያለን። በቀጣይም ዳኞች እና ታዛቢዎችን ጠርተን እንወያያለን። ይህንን ሁሉ የምናደርገው እግርኳስ እንዲቀጥል ስለምንፈልግ ነው።
“በዋናነት ማሰብ ያለባችሁ ጉዞ እንዴት ቀንሰን ውድድር እናደርጋለን የሚለው ጉዳይ በተመለከተ ነው ። ውድድሮች ሲቀጥሉ በሁለት ዙር ቢደረጉም ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ጨዋታዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ በፊት ከምትጫወቱት የጨዋታ ብዛት በአንድ አራተኛ ባነሰ ሜዳ ጨዋታዎችን ማድረግ እንችላለን። ከዚህ ውጪ ኮቪድን እየተከላከልን እንዴት ውድድር እናደርጋለን የሚለውን ማየት አለባችሁ። ከዚህ መነሻነት ሁላችሁም የኮቪድ የጤና መኮንኖችን መቅጠር አለባችሁ። ግን የውድድሩ አካሄድ (format) ይለወጥ የሚባል ነገር አንቀበልም።
“ከፊፋ አምስት መቶ ሺ ዶላር ለፌደሬሽናችን ተልኳል። ግን ይህ ገንዘብ ለእናንተ አደለም። በተገቢው መንገድ እስከታች ወርደው ለሚሰሩ የክልል ፌደሬሽኖች የሚሰጥ እንጂ። ሲጀምር ፊፋ ገንዘቡን ሲልክም የምናውልበትንም ነገር አብሮ ስለሚልክ ገንዘቡ ቢሮ ውስጥ አበል ላይ አይውልም። ገንዘቡ መዋል ያለበት ነገር ላይ ከዋለ በኋላ የተረፈው ግን እናንተን ለማገዝ እንጠቀምበታለን።” በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ንግግር በመቀጠል አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ የተዘጋጀውን 31 ገፅ የውድድድር ማስጀመሪያ መነሻ ሰነድ አቅርበዋል። በቀረበው መነሻ ሰነድ ላይ የተካተቱ ተገቢ ምክሮችንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
– የጤና ባለሙያዎች ተወዳዳሪዎችን የሙቀት ልኬት መውሰዳቸውን ማረጋገጥ
– ሁሉም ተወዳዳሪዎች ከጨዋታው 48-72 ሰዓታት በፊት የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት ለአወዳዳሪው ማስገባት ይኖርባቸዋል
– በጨዋታ መቋረጥ ምክንያት ሴቶች የሚደርስባቸውን ጫና መረዳት
– የማቆያ ቦታዎች የመያዝ አቅም ማወቅ
– በሁሉም ቦታ ጠቃሚ ቁሳቁስ አቅራቢዎችን ማዘጋጀት
– በአዋጁ መሠረት በአንድ ተሽከርካሪ የተጓዥ ቀጥር መወሰን አለበት
– በዝግ ስታዲየም ውድድሮችን ማድረግ
– ምንም አይነት ህፃናት ተጫዋቾችን አጅበው ወደሜዳ እንዳይገቡ ማድረግ
– ቶሎ ቶሎ ኳሱን ከተዋሲያን በተደጋጋሚ ማፅዳት
– ሁለቱም ቡድኖች ወደሜዳ ሲገቡ ለየብቻ እንዲሆን ማድረግ
– ውድድሩ እስኪያልቅ ድረስ ሁሉም ቡድኖች አንድ ከተማ ላይ ወይም አንድ ቦታ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ
– በተመረጡ ውስን ሜዳዎች ውድድሮችን ማድረግ
– በመስመር ላይ ያሉ አሰልጣኝ ወይም ተቆጣጣሪዎች ማስክ ማድረግ አለባቸው
– አምስት ተጫዋቾች መቀየር ይቻላል- በ30ኛው እና 75ኛው ደቂቃ የውሃ እረፍት መኖር አለበት
– ሜዳ ላይ መትፋት፣ ዳኛን መክበብ፣ ፊትን ወደ ተቃራኒ ቡድን አዙሮ ማውራት፣ ድምፅን ከፍ አድርጎ መናገር ክልክል ነው
– የቅድመ ስብሰባ (ፕረስ ኮንፍረንስ) አይኖርም
– አጭር ቃለ መጠይቅ ሲደረግ 2 ሜትር ርቀት እንደተጠበቅ ይሆናል
-ፆታዊ ጥቃት እንዳይኖር መከታተል
የመነሻ ሰነዱ ከቀረበ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ ለሻይ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍቱ መልስም አቶ ኢሳይያስ መጠነኛ ንግግር አድርገዋል።
“እኛ እንደ ስራ አስፈፃሚ የተነጋገርነው ነገር አለ። እናንተ የምትወዳደሩበትን ሜዳ ምረጡ እንጂ ሜዳዎችን እና በውድድር ወቅት የሚኖሩ ቁሳቁሶችን በራሳችን ወጪ እናፀዳለን። እናንተ ብቻ ልዑካኖቻችሁ ከቫይረሱ የሚጠበቁበትን መንገድ ለይታችሁ ሥራዎችን ሥሩ።”
ከፕሬዝዳንቱ አጭር ንግግር በኋላ ከተለያዩ ክለቦች የመጡ ተወካዮች ሃሳቦቸን ወደ መድረኩ ሰንዝረዋል።
“ሴቶቹን አስባችሁ ውድድሮች የሚጀመሩበትን መንገድ ለመቀየስ መስራታችሁ በጣም የሚያስመሰግናችሁ ነው። በተጨማሪም ሜዳዎችን ሳኒታይዝ የማድረጉን ስራ ፌዴሬሽኑ ይችላል ማለታችሁ አስደስቶኛል። ግን እግረ መንገዳችሁን የልምምድ ቦታዎችን እና ሆቴሎችንም እንደ ሜዳው ሁሉ ብታፀዱልን ጥሩ ነው።” ( አቶ ዳዊት – ድሬዳዋ ከተማ)
“ከዚህ በፊት ከምናወጣው ወጪ የበለጠ ወጪ በቀጣይ ዓመት እንደምናወጣ ይገባኛል። ይህንን ደግሞ እንቸለዋለን ወይ የሚለው መታየት አለበት። ስለዚህ በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር ሊደግፈን ይገባል።” (አቶ ገመቹ – አዳማ ከተማ)
“የምንቀጥራቸው የኮቪድ የጤና መኮንኖቸ ተጠሪነታቸው ለማን ነው? ለፌዴሬሽኑ ወይስ ለጤና ሚኒስቴር? ከዚህ በተጨማሪ በኮቪድ መከላከል ላይ ትልቅ ስራ የሰሩ ክለቦቸን የመሸለም እና እውቅና የመስጠት ነገር ቢታሰብበት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተባሉትን ነገሮች በአግባቡ ያልሰራ ክለብ ምንድነው ቅጣቱ?” (አቶ ዮናስ -ልደታ ክፍለ ከተማ)
“በሙሉ ጊዜ ኳስ ተጫዋችነት (professional) በክለባቸን ያሉ ተጫዋቾችን በተባለው መልኩ መቆጣጠር እንችላለን። ግን በቢጫ ቴሲራ የምንይዛቸው እና ከትምህርት እየመጡ የሚጫወቱትን ተጫዋቾቸችንን እንዴት ነው የምናደርገው? ይህ በፕሮቶኮሉ ቢታይ መልካም ነው።” (አቶ ልዑል – ባህር ዳር ከተማ)
“የውድድር ሜዳዎችን ስንመርጥ በዛው በከተማው የሚገኙ የልምምድ ቦታዎችን ታሳቢ ብናደርግ። አለበለዚያ አሁን መርጠን በኋላ ልንቸገር እንችላለን።” ( አቶ ሽፈራው – ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ)
በተጨማሪም ከሜዳ እና ከውድድር ደንቦች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሃሳቦች ከቀረቡ በኋላ ከመድረኩ ምላሾች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል።
“እንደ ፌዴሬሽን ትልቅ ወጪ ነው ያለብን። በተለይ ይህ የሴቶች ውድድር ብዙ ወጪ ያስወጣናል። የመመዝገቢያ፣ የዳኛ እና የኮሚሽነር ክፍያ እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚዳኙ ዳኞች የምርመራ ሂሳብ አትከፍሉም። ይህንን ሁሉ እኛ ነው የምንቸለው። በተጨማሪም ሜዳዎችን ለማፅዳት ቃል ገብተናል። ስለዚህ ይህ በቂ ነው። ከዚህ በላይ አንችልም። ጫናዎችን ወደ ራሳችን ያመጣነው እናንተን ለማገዝ ነው።
“መንግስት ይደግፈን የምትሉት አይገባኝም። ሁላችሁም እኮ የመንግስት ክለቦች ናችሁ። አይ የፌዴራል መንግስ ካልደገፈን የምትሉ ከሆነ አይሆንም። በየአካባቢያችሁ የሚያስተዳድሯችሁን የመንግስት አካላት ለኮቪድ ብላችሁ ተጨማሪ በጀት አሲዙ።”
“የጤና መኮንኖቹ ከፌዴሬሽናችን እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጥሩ መግባቦት እንዲሰሩ እናደርጋለን። በተለይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር። ግን ዋና ሃላፊነቱ እናንተ ክለቦች ጋር ነው ያለው። በትንሽ ብር የኮቪድ መኮንኖቹን መቅጠር ስለምትችሉ ይህ አያሳስባችሁም።”
አቶ ኢሳይያስ ጂራ ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ከሰጡ በኋላ ለሁለቱ ሊጎች የሚሆኑ የመወዳደሪያ ሜዳዎች መመረጥ ጀምረዋል። በዚህም በድምፅ ብልጫ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር በአዲስ አበባ (አንደኛ ዙር) እና በአዳማ አበበ ቢቂላ (ሁለተኛ ዙር) ስታዲየሞች በሁለት ዙር እንዲደረግ ተመርጠዋል። ነገርግን የዋናው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመወዳደሪያ ቦታዎች ሲመረጡ “እኛ ሜዳውን ከምንመርጥ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴው ያሉ ሜዳዎችን አጥንቶ ይንገረን” የሚል ሃሳብ ከተሳታፊያኑ ተነስቶ የተመረጡት ቦታዎች ሳይፀኑ ቀርተዋል። በዚህም የሴቶች ልማት እና ውድድር ኮሚቴ የሌሎች ሊግ ውድድሮች (የወንዶች) የሚመርጧቸውን ሜዳዎች ያማከለ እና ለሴቶች ውድድር አመቺ የሆነውን ሜዳ ለይቶ እንዲያቀርብ ትዛዝ ተላልፎ ስብሰባው ተቋጭቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!