ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር የመጨረሻ ክፍል ዛሬ ይቀርባል።
በ1966 የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ሄሌኒዮ ሄሬራ ከወሳኝ ተጫዋቹ አሎዲ ጋር ተቃቅሮ ሰንብቷል፡፡ ሪያል ማድሪድም ያባብለውና ያማልለው ይዟል፡፡ ሱአሬዝ ደግሞ ዳግም ወደ ፍቅረኛው ሃገር ስፔይን ለመመለስ እንደሚፈልግ ብዙኃን መገናኛዎች መዘገባቸውን ቀጥለዋል፡፡ በወቅቱ ክለቡን በበላይነት ሲመሩ የነበሩት አንጄሎ ሞራቲ የኢንተር ፕሬዘዳንት ሆነው ለመዝለቅ ፍላጎት አጥተው ታይተዋል፤ ሰውየው ለንግድ ተቋሞቻቸው የበለጠ ጊዜ መስጠት እንዳለባቸው አምነው ራሳቸውን ከኃላፊነት ለማንሳት ተዘጋጅው ነበር፡፡ ከሁሉ የከፋው ግን የአጥቂው የሱአሬዝ ብሽሽት ጉዳት ይመስላል፡፡ ጨዋታው ሊከናወን ቀናት ሲቀሩት ደግሞ የሳንድሮ ማዞላ በኃይለኛ ጉንፋን መያዝም “በእንቅርት ላይ …” እንዲሉ ሆነ፡፡
ሴልቲኮች ከሜዳቸው ውጪ ከደክላ ፕራግ ጋር ባካሄዱት የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ በደካማ የመከላከል አደረጃጀት እጅጉን ተዳክመው መቅረባቸው አነጋግሯል፡፡ በእርግጥ በጨዋታው ጎል ሳይቆጠርባቸው 0-0 መለያየት ቢችሉም
ከመከላከል ይልቅ ማጥቃቱ ላይ እንደሚጠነክሩ ተረጋግጧል፡፡ በጊዜው የስኮትላንዱ ቡድን ከ1958ቱ የዓለም ዋንጫ በኋላ ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት የቻለውን 4-2-4 ፎርሜሽን ያወትር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ የመሃል አጥቂዎቻቸው ማለትም ስቲቪ ቻልመርስ እና ዊሊ ዋላስ ወደኋላ በማፈግፈግ የመጫወት ዝንባሌ ነበራቸው፡፡ ይህን ታክቲካዊ ተልዕኮ የሚወጡትም የተጋጣሚዎቻቸውን እግር-በ-እግር ተከታታይ ተከላካዮች (Defensive Markers) ከቦታቸው ለማስለቀቅ ነበር፡፡ በዚህም ሴልቲኮች ተጫዋች-በ-ተጫዋች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ የኢንተሮችን የመሐል ተከላካዮች (Central Defensive Markers) ለማቆም ችሏል፡፡ ለወትሮ መስመራቸውን ታከው ሲጫወቱ የሚታወቁት ሁለቱ የመስመር አማካዮች ጂሚ ጆንስቶን እና ቦቢ ሌኖክስ ወደ መሃል እየገቡ እንዲጫወቱ ይበረታቱ ነበር፡፡ እነዚህ አማካዮች በእንቅስቃሴ ወደ መሃል ሲገቡ ከጀርባቸው የሚሰለፉት የመስመር ተከላካዮች ጂም ክሬይግ እና ቶሚ ገሜል የሚያጠቁበት ነጻ ቦታ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ኢንተሮች በፍጻሜው ለመከላከል ከወጠኑ ሴልቲኮች ያላቸውን አቅም አሟጠው ለማጥቃት ዝግጁ እንደነበሩ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናል፡፡
ጨዋታው ሲጀምር ቀድሞ የተፈራው ነገር ደረሰ፡፡
ሳንድሮ ማዞላ በሰባተኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ካደረገ በኋላ ኢንተሮች በጥብቁ መከላከል ጀመሩ፡፡ በ1965 ከቤኔፊካ ጋርም ይህንኑ አድርገው ነበር፡፡ አሁንም ተመሳሳዩን መከወን መረጡ፡፡ ነገርግን ክለቡ የቀድሞው አቋሙ አብሮት አልነበረም፡፡ ብዙዎች የጣልያኑ ክለብ ብቃት ላይ ጥርጣሬ አደረባቸው፡፡ ሴልቲኮች ሲወሯቸው ደግሞ ይበልጡን ኢንተሮች ተጨነቁ፡፡ ” በተለይ ከአስራ አምስተኛው ደቂቃ በኋላ ልንቆጣጠራቸው እንደሚሳነን እናውቅ ነበር። እያንዳንዱን የመጀመሪያ ኳስ የሚይዙት እነርሱ ነበሩ፤ ስለዚህም በሜዳው ሁሉም ክፍል ቀጠቀጡን፡፡ እንዲህም ሆኖ በጨዋታው እስከ እረፍት ድረስ እነርሱን 1-0 እየመራናቸው የነበረ መሆኑ ለእኔ ተዓምር ሆኖብኛል፡፡ በእነዚያ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነንም አልፎአልፎ የራስ መተማመናችን ከፍ እያለ ሲሄድ ይሰማን ነበር፡፡ በሂደት በራሳችን ዕምነት እየኖረን መጣ፡፡ ይሁን እንጂ የዚያን ዕለት ይህኛው ወኔ አልነበረንም፡፡ በዕረፍት ሰዓት በመልበሻ ቤት ሆነን እንኳ ሁላችንም እርስ በእርስ እየተያየን የምናስበው የመጨረሻችን ውድድር እንደነበረ ነው፡፡” ይላል በርኚች፡፡
በርኚች እና መሰሎቹ ያኔ የ”ሪትሮ” አጨዋወት ሥልት እንዳበቃለት አስበዋል፤ ፋይዳውም እምብዛም እየሆነ መሄዱንም ተገንዝበዋል፡፡ ምናልባትም ጥርጣሬ ከማጫር እና አሉታዊ ገጽታን ከመፍጠር በቀር ሌላ ጥቅም የማይሰጥና ረብ የለሽ ተደርጎም መወሰድ ጀምሯል፡፡ “በውድድሩ የመጨረሻ ወር አካባቢ ቤተሰቦቼን ያየኋቸው ሶስቴ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ለዚያም ነው ‘የመኝታ ቤት ተጋሪዬ ጂያንሺንቶ ፋኬቲ እና እኔ ትዳር የመሰረቱ ጥንዶች ያህል ሆነናል፡፡’ እያልኩ እቀልድ የነበው፡፡ በእርግጠኝነት የምናገረው ከባለቤቴ ይልቅ ከእርሱ ጋር ብዙ ጊዜያት እንዳሳለፍኩ ነው፡፡ ጫናው እየናረ ስለሄደ ዘወር የምንልበት መፈናፈኛ ወይም ማምለጫ አማራጭ አልነበረንም፡፡ ይህ ሁኔታ ኋላ ላይ ለውድቀታችን ዋነኛ መንስኤ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ጉዳቱ በሁለቱም ውድድሮች ጉልህ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፎብናል፥ በሊግም-በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜም፡፡” በማለት በርኚች ይናገራል፡፡
ኢንተሮች ፖርቹጋል ሲደርሱ ሄሬራ የቡድኑን አባላት ይዞ ከሊዝበን ግማሽ ሰዓት በሚፈጅ የመኪና ጉዞ የሚደረስ ባህር ዳርቻ አጠገብ በሚገኝ ሆቴል አሳረፋቸው፡፡ እንደተለመደው ክለቡ የሆቴሉን ሙሉ ክፍል ያዘ፡፡ ” እዚያ ከተጫዋቾች እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ውጪ ማንም አልነበረም፡፡ የሆቴሉ ሠራተኞች እንኳ ያረፉት ሌላ ቦታ ነበር፡፡ እየቀለድኩ አይደለም- አውቶቡሳችን ጭኖን ወደ ሆቴሉ በር ከደረስንበት ደቂቃ አንስቶ ለጨዋታው ወደ ስታዲየም እስከወጣንበት ቅጽበት ድረስ በነበሩት ሦስት ቀናት ከተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ወሳኝ የሆቴሉ ሰራተኞች በስተቀር ማንንም አካል አላየንም፡፡ አንድ መደበኛ የአኗኗር ሒደት የለመደ ሰው እነዚህ ሁኔታዎች ሊያሳብዱት ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳ ከብዙ ጊዜያት በኋላ ነገሩን እየተላመድነው ብንሄድም መጨረሻ ላይ ጭንቀቱ ናላችንን አዙሮት ነበር፡፡ የዓለምን ሸክም ሁሉ በጫንቃችን የተሸከምን ያህል ይሰማናል፡፡ ቅሬታ ለማቅረብ መተንፈሻም አልነበረንም፡፡ ማናችንም እንቅልፍ እምቢ አለን፤ መተኛት አቃተን፡፡ ለሊት ላይ ለሦስት ሰዓት ያህል ሸለብ ካደረገኝ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥር ነበር፡፡ ሁላችንም ስናከናውን የጨረምነው ተግባር ስለ ሴልቲክ ተጫዋቾች አብዝቶ ማሰላሰል እና ስለ ፍጻሜው ማሰብ ብቻ ነበር፡፡ እኩለ ለሊት ላይ ፋኬቲ እና እኔ የሆነ ድምጽ ቀሰቀሰንና ነቃን፤ ማጓራት የሚመስል ድምጽ ወደ ሰማንበት ክፍል ጆሯችንን ስንተክል አምበላችን አርማንዶ ፒቺ ከከፍተኛ ጭንቀት የተነሳ እያስመለሰው እንደሆነ ተረዳን፡፡ ለነገሩ አራት ተጫዋቾች ጨዋታው በሚካሄድበት ቀን ጠዋቱን ጣታቸውን ወደ አፋቸው በማስገባት ሽቅብ እንዲላቸው አድርገዋል፡፡ አራቱ ደግሞ ለጨዋታው ወደ ሜዳ ከመውጣታቸው በፊት ተመሳሳዩን ሲፈጽሙ አስተውለናል፡፡ አዕምሯችንን ከጭንቀት ለመታደግ ችግሩን ወደራሳችን የጠራነው እኛው ራሳችን ነበርን፡፡” ሲል በርኚች ያሳለፉትን ስቃይ ይዘረዝራል፡፡
በአንጻሩ ሴልቲኮች ዘና የማለት መንፈስ አሳዩ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ይበልጡን ኢንተሮችን ውጥረት ውስጥ ከተታቸው፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ የካቴናቺዮ ታክቲክ ያከተመለት ጉዳይ እንደሚሆን የሚያረጋግጥ የአመለካከት አውድ ተፈጠረ፡፡ በዚህ የመከላከል እግርኳሳዊ አቀራረብ ላይ አሉታዊ ገጽታ የማላበስ ከፍተኛው ደረጃ ተደረሰ፡፡ ራሳቸው ኢንተሮች የፈጠሩት ጭራቅ መልሶ ራሳቸውን ዋጠ፡፡ ይህ ሁሉ ተብሎም በጨዋታው እንደተጠበቀው ሴልቲኮች ታክቲካዊ በሆኑ ውስብስብ እንቅስቃሴዎች አልተቸገሩም፤ የተጋጣሚያቸው መከላከያ ወረዳም እንደተፈራው አልከረቸመም፡፡ ተከታታይ ግብ የማስቆጠር አጋጣሚዎች ፈጥረው ነበር፡፡ በርቲ ኡልድ የጎሉ አግዳሚ መልሶበታል፤ የጌሜልንም ሙከራ የኢንተሩ በረኛ ጁሊያኖ ሳርቲ በአስደናቂ ሁኔታ አድኖታል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ አስራ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ሴልቲኮች የአቻነት ግብ አስቆጠሩ፡፡ ጃክ ስቴይን ላመነባቸው ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ምስጋና ይግባና የኢንተሮችን መስመር በተደጋጋሚ ማጥቃት ቻሉ፡፡ በቀኝ መስመር ቦቢ ሙርዶክ በቀኝ መስመር ክሬይግን ደጋግሞ ያገኘው ነበር፡፡ በዚህም ሒደት ለቀኝ መስመር አጥቂው ጌሜል ተሻጋሪ ኳስ ከመላኩ በፊት እርሱ ራሱ ወደ ፊት ተጠጋ፡፡ ይህን ያደረገውም ሆን ብሎ ነበር፡፡ በኢንተር ተከላካዮች ጥብቅ ቁጥጥር ሥር ለሚገኙ ተጫዋቾች ቅብብሎችን መከወን እርባና ቢስ ሆኖበት አገኘው፤ ስለዚህም ኳሱን ይዞ ወደ መሃል ካፈገፈጉ አማካዮች የተወሰኑት ቀደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል እስኪደርሱ ጠበቀ፡፡ የቡድን አጋሮቹ አመቺ ቦታ ላይ ሲደርሱ ቅብብሎቹን ፈጸመ፡፡ በዚህ መንገድ ሴልቲኮች ጎል አግብተው አቻ ሆኑ፡፡
የስኮትላንዱ ክለብ ተጫዋቾች በድንገት የሚከውኗቸው ከባባድ የማጥቃት ሒደቶች ቀጠሉ፡፡ ” አስታውሳለሁ-የሆነ ሰዓት ላይ ፒቺ ወደ ግብ ጠባቂያችን ዞሮ ‘ ጁሊያኖ በቃ-ተወው! ተወው! መውተርተሩ ትርጉም የለሽ ነው፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ተጨማሪ ግብ ያስቆጥሩብናል፤ በመጨረሻም አሸናፊ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው፡፡’ አለው፡፡” ይለናል በርኚች፡፡ ” እንደ እነዚህ አይነት ቃላት እሰማለሁ ብዬ ፈጽሞ ጠብቄ አላውቅም ፡፡ አምበላችን ለግብ ጠባቂያችን ፎጣውን እንዲወረውር ሲነግረው አዳምጣለሁ ብዬ በጭራሽ አስቤ አላውቅም፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በዚያች ቅጽበት ምን ያህል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደተዘፈቅን ማሳያ ይሆናል፡፡ ሁላችንም በወቅቱ ስቃያችንን ላለማራዘም የተመኘን እንመስል ነበር፡፡” በማለት በርኚች የነበሩበትን ውጥንቅጥ ይዘረዝራል፡፡
እጅጉን የተዳከሙት ኢንተሮች አላማ ቢስ ረጃጅም ቅብብሎችን ወደ ተጋጣሚ ክልል ከመላክ ውጪ ሌላ የሚከውኑት ተግባር አልነበራቸውም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ኢንተሮች ተረቱ፡፡ አሁንም የሴልቲኮቹ የመስመር ተከላካዮች ወሳኝ ሚና ተጫወቱ- ጌሜል ለሙርዶክ ኳስ አቀበለው፤ የሙርዶክ አቅጣጫዋን የሳተች ጠንካራ ምት ቻልመርስ እግር ሥር ደረሰች፡፡ ቻልመርስ ኳሷን በቀላሉ የሳርቲ ግብ ውስጥ መሰጋት፡፡ በዚህም ድል የስኮትላንዱ ቡድን የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ አሸናፊ በመሆን ላቲናዊ ከሆኑት ክለቦች ውጪ ቀዳሚው ሆነ፡፡ የኢንተር የመፍረክረክ ዘመንም በዚሁ ጀመረ፡፡
እጅግ የከፋው እና አሳዛኙ ሁኔታ ደግሞ በማንቶቫ ተከሰተ፡፡ ጁቬንቱሶች በሴሪኤው ላዚዮን አሸነፉ፡፡ በሌላ በኩል ጁሊያኖ የቀድሞውን የኢንተር አጥቂ ዲ ጂያኮሞን ጠንካራ ምት ማዳን ተስኖት ኳሷ ሳርቲን በተኛበት አልፋ ግብ ሆነች፡፡ ኢንተሮች በከባዱ የውድድር ዘመን ስኩዴቶውንም አጡ፡፡ ” አዕምሯችን ሥራውን ያቆመ መሰለን፤ በስነ ልቦና፣ በአካል ብቃት፣ በስነ አዕምሮ እጅጉን ተዳክመን ነበር፡፡ የሄሬራ የወቀሳ ውርጅብኝ በተከላካዮቹ ላይ ተከተለ፡፡ ከዚያም ጉዋርኔሪ ለቦሎኛ ተሸጠ፤ ፒቺም ወደ ቫራዝ አመራ፡፡” ይላል በርኚች፡፡ ” ገድ ፊቷን ስታዞርልን እና ሁኔታዎች ሲሰምሩልን የምናስመዘግበው ድል በሄሬራ ታላቅ ዕቅድ የተገኘ ስለመሆኑ ይለፈፋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ነገሮች በተጠበቀው መንገድ አልጓዝ ሲሉን እና ሳይሳካልን ሲቀር ተጫዋቾች ላይ የትችት ናዳ ይወርዳል፡፡” በማለት ግብ ጠባቂው ሳትሪ ያማርራል፡፡
ብዙ ቡድኖች ካቴናቺዮን እየተገበሩ በሄዱ ቁጥር የአጨዋወት ዘይቤው ደካማ ጎኖች ይበልጡን ግልጽ ይሆኑ ጀመር፡፡ ካርል ራፕን ከገና ከጅምሩ ያስተዋለውና በሲስተሙ ቅርጽ ሳቢያ አማካዮች በተጋጣሚዎቻቸው ብልጫ ተወስዶባቸው የሚፈጠረው ችግር ሳይፈታ የካቴናቺዮ ህልውና ለብዙ ዘመናት ዘለቀ፡፡ <ቶርናንቴ> በመባል የሚታወቀው የአማካዮች አዲስ ሚና ችግሩን በጊዜያዊነት ሊያቀለው ቢችልም ሌላ መዘዝ ማስከተሉ አልቀረም- ከፊት መስመሩ ተጫዋች እንዲቀንስ ማድረጉ፡፡ ” ኢንተሮች ካቴናቺዮን ከእነ እንከኑ ተላምደውት ታይተዋል፡፡ የዚህም ምክንያት በግራና ቀኝ መስመሮች ባለ ተሰጥኦዎቹን ጃየር እና ኮርሶን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ስለነበሯቸው ነው፡፡” ማራዴይ ያብራራል፡፡ ” ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የወቅቱን ታላቅ አጥቂ ሱአሬዝን አካቷል፡፡ እርሱ እኮ እነዚያን ረጃጅም ኳሶች በሙሉ ወደ ግብነት ለመቀየር የማይቸገር ተዓምረኛ ተጫዋች ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የካቴናቺዮ ሲስተም ለሌሎች ቡድኖች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የተወሰደው እርማት ደግሞ ሲስተሙ ተግባሪዎች ላይ ሌላ ያልታሰበ ውስብስብ ተግዳሮት አስከተለ፡፡ በወቅቱ የካቴናቺዮን ጉድለት ለማስተካከል የመስመር ተከላካዮችን (Full-Backs) ወደ ጠራጊ- ተከላካዮች (Liberis) የተሻለው መፍትሄ እንደሆነ ይታመን ነበር፡፡ ነገር ግን ቡድኖች ይህን ከማድረግ ይልቅ ከመሃል አጥቂ ግራና ቀኝ የሚጫወቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎችን (Inside-Forwards) የጠራጊ ተከላካዮችን ኃላፊነት እንዲወጡ አደረጓቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ሽግሽግ በራሱ የሚሰጠው ጥቅም አለ፡፡ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲገኝ ከፊት መስመር ተሰላፊነት ወደ ጠራጊ ተከላካይነት የተለወጠው ተጫዋች ኳሷን ይዞ በመግፋት ወደ አማካይ ክፍሉ ይጠጋል፡፡ ስለዚህም በሜዳው አጋማሽ ላይ ኳሱን ወደፊት የሚያሻግሩ የአቀባዮች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ይህም ከካቴናቺዮ (Catenaccio)በቀጥታ ኤል ጂዬኮ ኦል ኢታሊያኖ(il giocco all’ italiano) ወደተሰኘው የጣልያኖች አጨዋወት (The Italian Game) የተደረገውን ዝግመታዊ የእግርኳስ ታክቲካዊ ሽግግር አመላካች ሆነ፡፡” ይለናል ማራዴይ፡፡
ምስል፦ ኢንተርናዚዮናሌ 1-2 ሴልቲክ፣ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ፡ ኢስታዲዮ ናሲዮናል-ሊዝበን-ግንቦት 25-1967
በ1967-68 የውድድር ዘመን የቡድኑ ወኔ እና በራስ የመተማመን ስሜት ተንኮታኮተ፡፡ ኢንተሮች ሴሪአውን አምስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ፡፡ ከሻምፒዮኑ ሚላን አስራ ሦስት ነጥቦች አንሰው ተገኙ፡፡ ሄሬራም ወደ ሮማ ተጓዘ፡፡ ካቴናቺዮ ከታላቁ ኢንተር ጋር ግብዓተ መሬቱ አልተፈጸመም፤ ይሁን እንጂ ያለመበገር ምልክትነቱ ከቡድኑ አቋም ጋር አብሮ ወርዷል፡፡ በፍጻሜው ሴልቲኮች የወደፊቱ እግርኳስ በማጥቃት አቀራረብ የተቃኘ ሊሆን ስለመቻሉ ፍንጭ ሰጡ፡፡ ለቀጣዩ እግርኳሳዊ የታክቲክ አብዮት ተጠባቂው እና ተመስጋኙ አሰልጣኝ ቢል ሻንክሌይ ብቻ እንደማይሆኑም ምልክት ታየ፡፡
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡