ወላይታ ድቻ የሦስት ተጫዋቾችን ውል አራዘመ

በቀድሞው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት መምህር የሚመሩት ወላይታ ድቻዎች እስከ አሁን ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረሙ ሲሆን የወሳኝ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝንም ውል ማራዘማቸው ይታወሳል፡፡ ዛሬ አመሻሽ ደግሞ የሦስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም ተስማምተዋል፡፡

ውል ካራዘሙት ተጫዋቾች መካከል አንተነህ ጉግሳ አንዱ ነው፡፡ በመሀል እና በመስመር ተከላካይነት የከፍተኛ ሊጉን ክለብ ሶዶ ከተማን ለቆ ወላይታ ድቻን በ2011 የውድድር ዓመት አጋማሽ ከተቀላቀለ በኃላ በክለቡ ያለፉትን አንድ ዓመት ከግማሽ ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ በመቻሉ በዛሬው ዕለት ለሁለት ተጨማሪ ዓመት በክለቡ ለመቆየት ተስማምቷል፡፡

ሁለገቡ ተጫዋች ያሬድ ዳዊት ለሁለት ዓመት በአሳዳጊ ክለቡ መለያ ለመቆየት የተስማማ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡ በወላይታ ድቻ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አማካኝነት በ2008 ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኃላ ለክለቡ በአጥቂ አማካይ፣ በመስመር አጥቂነት እና በቀኝ መስመር ተከላካይነት መልካም እንቅስቃሴን በማድረግ ለክለቡ ጥሩ ግልጋሎት ሰጥቷል። ተጫዋቹ በበኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሀዋሳ ስታዲየም ላይ ወላይታ ድቻ ዛማሌክን 2ለ1 ሲረታ ሁለተኛዋን የማሸነፊያ ጎል ከመረብ ማሳረፉም አይዘነጋም፡፡

ፀጋዬ ብርሀኑ ሦስተኛው ማምሻውን ውል ያራዘመው ሌላኛው ተጫዋች ነው፡፡ በ2009 ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን ካደገ በኃላ ላለፉት አራት ዓመታት በዋናው ቡድን እየተጫወተ የሚገኘው ይህ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በተለይ ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ጥሩ አበርክቶ የነበረው ሲሆን ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለመቆየት ከስምምነት ደርሷል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!