የግል አስተያየት | መሠረት የሌለው የታክቲክ ሥልጠናችን

የተወዳጁ ጨዋታ የሥልጠና ዘርፍ እጅጉን እየዘመነ ይገኛል፡፡ የሥልጠናው ዓይነት፣ ጥራት፣ ይዘት እና ደረጃ ከሚታሰበው በላይ እመርታ እያሳየ ነው፡፡ ከእግርኳስ መሰረታውያን ውስጥ ታክቲክ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሄዱ በግልጽ ይስተዋላል፡፡ ቡድኖች በየጊዜው ይዘው የሚመጡትን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ለመቋቋም አልያም ለማስከፈት አዳዲስ የማጥቃት መንገዶችን በመፍጠር ለአሸናፊነት ይተጋሉ፡፡ በተቃራኒው ሌሎች ደግሞ ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት የሚተገብሩ ቡድኖችን ለመቋቋም ዘመናዊና አዳዲስ የመከላከል ሥልቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ይህም በእግርኳስ ታክቲክ እድገት ላይ ተከታታይ ለውጦች፣ ማሻሻያዎች እና ፈጣን መፍትሄዎች እንዲመጡ በር ከፍቷል፡፡

እንደሚታወቀው ታክቲክ ሰፋ ያለ ጽንሰ-ሐሳብ ነው፡፡ ማዕቀፉ አንድ ተጫዋች በሜዳ ላይ ከኳስ ጋር እና ያለ ኳስ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአጠቃላይ አንድ ቡድን በጨዋታ ሊተገብር ያቀደውን የአጨዋወት እቅድ ያጠቃልላል፡፡ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚኖራቸው መስተጋብር፣ ቦታ አያያዝ፣ አካላዊ እና አዕምሯዊ ፍጥነት፣ ጨዋታ አረዳድ፣ እይታ፣ የቀጣይ ኹነቶች ግምት እና ሌሎችም በታክቲካዊ መነጽር ሊቃኙ የሚችሉ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ተጫዋቾች በከፍተኛ ደረጃ የላቁ ሆነው እንዲገኙ የሚጠበቀው ራሳቸው ባካበቱት የሚዳብር የታክቲክ ግንዛቤ አልያም ከአሰልጣኞች የሚቀስሙትን ታክቲካዊ ትምህርት በአግባቡ የሚረዱ እንዲሆኑ ነው፡፡

በሰለጠነው የእግርኳስ ዓለም አሰልጣኞች ታዳጊዎቻቸውን ስለ ታክቲካዊ ጉዳዮች የሚያሰለጥኑበት መንገድ ከፍተኛው ትኩረት ይቸረዋል፡፡ አሁን-አሁን ባደጉት ሃገራት በአስራ አምስት፣ አስራ ስድስት እና አስራ ሰባት ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ተጫዋቾችን በዋናው ቡድን ውስጥ የተሰላፊነት ዕድል መስጠት የተለመደ ሆኗል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች የመጫወት ዕድል ከማግኘታቸው በተጨማሪ ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ቡድናቸውን ሲጠቅሙ ይታያሉ፡፡ ለተጫዋቾቹ “ፕሮፌሽናል” እድገት- መሰረተ ልማቱ የተሟላለት፣ በዘመናዊ አስተደደር የሚመራ፣ በተደራጀ እና በተቀናጀ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፍ የእግርኳስ ከባቢ ወሳኙን ድርሻ ቢወስድም እኔ በግሌ የተጫዋቾችም ሆነ የአሰልጣኞቻቸው ታክቲካዊ ግንዛቤ ያስደንቀኛል፡፡ በተለያዩ ሃገራት የታክቲክ ስልጠና የሚሰጥበት ሒደት እና ሥልጠናው መሰጠት የሚጀምርበት የእድሜ ክልል ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ” የእግርኳስ ታክቲክ ስልጠና በየትኛው የእድሜ እርከን መጀመር ይኖርበታል?” የሚለው አከራካሪ ጥያቄ ሆኖ ዘልቋል፤ ብዙውን ጊዜ ጥያቄው የተለያዩ ምላሾች ይቀርቡበታል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ – በፌዴሬሸን ቴክኒካዊ ጉዳዮች ክፍል፣ በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በሚሰሩ  ባለሙያዎች፣ በስልጠናው ዘርፍ በተሰማሩ አሰልጣኞች ዘንድ ከላይ ለቀረበው ጥያቄ የሚቀርበው ምላሽ ተመሳሳይ ይዘት አለው፤ የታክቲክ ስልጠና መጀመር ያለበት ታዳጊዎቹ እድሜያቸው አስራ አምስት ዓመት ሲደርስ እንደሆነም ያሳያል፡፡ በእኔ እምነት ይህ እጅጉን የተሳሳተ አመለካካት ይመስለኛል፡፡ በአውሮፓና በሌሎች ክፍለ ዓለማት የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ በዋናው ቡድን መጫወት የሚጀምርበት እድሜ ሆኖ ሳለ እኛ ለታዳጊዎቻችን ታክቲካዊ ስልጠናውን በተጠቀሰው የእድሜ ደረጃ ላይ እንድንጀምር መፍረድ የኋላ-ቀርነት መንገዳችንን የሙጥኝ ብሎ የመያዝ አባዜ ነው፡፡ የማይመስል ነገር!

እንደሚታወቀው የታክቲክ ስልጠና በሦስት መንገዶች ይሰጣል፡፡
1)በግል፦(የግል ታክቲክ)
2)በግሩፕ፦(የግሩፕ ታክቲክ)
3)በቡድን፦(የቡድን ታክቲክ) 

እነዚህ የታክቲክ ስልጠናዎች ተገቢው ጥናት ተሰርቶባቸው፣ በየቡድኖቹ ዋና ዋና አሰልጣኞች ቀጥተኛ ክትትል ተደርጎባቸው እና በየሰልጣኞቹ የእድሜ ደረጃ ተለክተው ወይም ተስማሚ እንዲሆኑ ተመጥነው ለታዳሚዎች ከለጋ የስልጠና  እድሜያቸው ጀምሮ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በእርግጥም ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት “ታክቲካዊ ሥልጠናውን አንድ ታዳጊ በስንት ዓመቱ ይጀምረው?” የሚለው ጥያቄ  በሃገራችን ያሉ ታዳጊ ተጫዋቾች አዳዲስ ሐሳብ፣ ትምህርት፣ ሥልጠና የመቀበል አዕምሯዊ አቅማቸውን በሰፊው ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን በታዳጊዎች ስልጠና የተለመደው ቴክኒክ ላይ ትኩረት የመስጠት ባህል ቢሆንም መሰረታዊ የማጥቃትና የመከላከል ታክቲካዊ ስልጠናዎችን በግል እና በግሩፕ (ተጫዋቾች በሚጫወቱባቸው ‘ዲፓርትመንቶች’) መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እያደጉ ሲሄዱም ከኋላ መስርቶ ስለመጫወት፣ በቡድን የሚወሰድ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት፣ “ፕረሲንግ”፣ መልሶ-ማጥቃት፣ ጥግግት፣ የማጥቃትና የመከላል ሽግግሮች እና የመሳሰሉትን የታክቲክ ስልጠናዎች እንደ እድሜ ደረጃቸውና እንደ መረዳት አቅማቸው ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የታዳጊና ወጣት ቡድኖች ባሏቸው ክለቦቻችንም ቢሆን የታክቲክ ስልጠና እምብዛም የብዙዎችን ትኩረት የሚያገኝ ጉዳይ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ “ታች” በፕሮጀክቶችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የሰፈነው ብልሹ የስልጠና “ትሬንድ” ሥር ሰዶ “ላይ” በክለቦቻችን ዋና-ዋና ቡድኖች እና በብሔራዊ ቡድኖች ለምናየው ደካማ የታክቲክ አተገባበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡አብዛኞቹ ክለቦች ውስጥ ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ሲቀላቀሉ ከላይ የጠቀስኳቸው ዘመናዊ የታክቲክ መሰረታውያን አዲስ ይሆኑባቸዋል፡፡  መስርቶ መጫወት፣ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት፣ “ፕረሲንግ”፣ መልሶ-ማጥቃት፣ ጥግግት፣ የማጥቃትና የመከላከል ሽግግሮችና ሌሎች ታክቲካዊ ሥልጠናዎችን ይቅርና መሰረታዊ የሆነውን የማጥቃትና የመከላከል መርህ በቅጡ አያውቋቸውም፡፡ ታክቲክን በጥሩ የማወቅ ልክ ላይ የደረሱ አልያም አመርቂ የአረዳድ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን የማናፈራው ለዚሁ ነው-ሌላ ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሰልጣኞችም ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚዘምን የማስተማሪያ ቴክኒኮች አንፈጥርም፤ ያወቅነውን ያህል ለማሳወቅ፣ ለማስተማር፣ ለማሰልጠን፣ ሌሎችንም ሆነ ራሳችንን ለመለወጥ አንጥርም፡፡ በተጫዋችነታችን ዘመን በምናውቀው-በለመድነው መንገድ እያሰለጠንን፣ ባለንበት እየረገጥን፣ ሰበብ እየደረደርን፣ በእውቀት ሳናምን፣ ….. ጊዜያችን ባከነ፤ ሳንለውጥ-ሳንለወጥ እድሜያችን ነጎደ፡፡ በታክቲክ ላይ ያለን ደካማ አረዳድ እና ውሉ የማይታወቅ የታክቲካዊ ሥልጠና ሒደት ይኸው ከታች አንስቶ ላይ ድረስ በመዝለቅ ብሔራዊ ቡድናችን ላይ በስፋት ሲንፀባረቅ ኖረ-የተሻሻለ ሁኔታ የለምና አሁንም መቀጠሉ አይቀርም፡፡በታዳጊዎች ስልጠና ታክቲክን የማሰልጠን ልማድ እና አተገባበር ደካማ ለመሆኑ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም ሁለት ዐበይት ጉዳዮችን ግን ሳላነሳ አላልፍም፡፡

★ የመጀመሪያው- በሃገራችን ተዘወትሮ የሚሰጠው የአሰልጣኞች ስልጠና በተለይ የታክቲክ ጉዳይን በተመለከተ ያለው ተመክሮ እጅግ ደካማ መሆኑ ነው፡፡ መሰረታዊ በሆነው የታዳጊዎች ስልጠና ላይ የሚሳተፉ አሰልጣኞች የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን ይወስዳሉ፡፡ እኔም በእነዚህ ስልጠኛዎች ላይ ተሳትፌአለሁ፡፡ በስልጠናዎቹ ላይ የሚሰጠው የታክቲክ ትምህርት ከተግባር ይልቅ በአብዛኛው ንድፈ-ሃሳብ ላይ ያተኩራል፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም ምናልባት ከላይ እንደጠቀስኩት የታክቲክ ስልጠና የሚሰጠው እድሜያቸው አስራ አምስት ሲደርስ ነው ብለን ስለምናስብ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ታክቲክ ትኩረት ተሰጥቶት ስንማር ትዝ አይዩኝም፡፡ ታክቲካዊ ኅልዮቶችን ወደ ተግባር በመቀየር መሬት ላይ አውርዶ ለማስተማር ብርቱ ቸልተኝነት ይታያል፡፡ ለምሳሌ፦ ከመከላከል የታክቲክ መርህ አንዱ የሆነውን እና ማገዝ ወይም መደጋገፍ (Support) የሚል ግርድፍ ትርጉም የምንሰጠውን ሐሳብ ብናነሳ በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ምን ማለት እንደሆነ ትንታኔ ከመስጠት ባሻገር በተግባር ሁለተኛው ተከላካይ የመጀመሪያውን ተከላካይ እንዴት፣ መቼ እና ለምን እንደሚያግዝ፣ ተጫዋቹ የቡድን አጋሩን ሲያግዝ ከመጀመሪው ተከላካይ ሊኖረው ስለሚገባው ርቀትና እየተጠባበቁ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ማዕዘን ምን መምሰል እንዳለበት ደጋግሞ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ታክቲክ ለተጫዋቾች ለማለማመድ የትኛውን ዓይነት የልምምድ መርኃግብር መንደፍ እንደሚቻል ማሳየት ግድ ይላል፡፡ የታክቲክ ስልጠና በጣም ውስብስብ እና ጊዜ የሚጠይቅ እንዲሁም በጣም አስፈላጊ እንደመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል በሃገራችን የታዳጊዎች እግርኳስ  ሒደት መስመሩን የሳተ ልማድ ተጸናውቶታል፡፡ ስልጠናው የሚገመገመው በማሸነፍ ቁጥር ወይም ዋንጫ በማስገኘት በመሆኑ በታክቲክ ስልጠና ደካማ ለመሆናችን የበኩሉን አሉታዊ ተጽዕና ፈጥሯል፡፡ እንደ’ኔ-እንደ’ኔ በታዳጊዎች ስልጠና የውጤት መለኪያ ተደርጎ መቀመጥ ያለበት ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን በማፍራት ረገድ የተመዘገበው ስኬት ነው፡፡ በታዳጊዎች ስልጠና አሰልጥኞች በዚህ ዘርፍ የምንመዘን ከሆነ ተጫዋቾችን በረጅም ጊዜና በአስፈላጊ የእግርኳስ ስልጠናዎች ብቁ ከማድረግ ይልቅ ባልተገባ መንገድ ዋንጫ ለማግኘት እንዲጫወቱ እናደርጋቸዋለን፡፡ ስልጠናቸውም በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት የሚችሉበት ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ይህም ጊዜ የሚፈልጉ የታክቲክ ስልጠናዎች እንዲዘነጉ ያደርጋል፡፡

በመጨረሻም በፕሪምየር ሊጋችን በታክቲክ መረዳት ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችን፣ ጠንካራና የበሰለ ታክቲካዊ አተገባበር ያላቸውን ቡድኖች ለማየት ሥራውን ከታች መጀመርና በየደረጃው ተገቢውን ስልጠና እየሰጡ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ መታወቅ ይኖርበታል፡፡   


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ