አቡበከር ናስር እና ሚኪያስ መኮንን ስለ ውል ማራዘማቸው ይናገራሉ

በኢትዮጵያ እግርኳስ አንድን ተጫዋች ረዘም ላለ ሁኔታ ማስፈረም በማይቻልበት ሊግ የኢትዮጵያ ቡና ወጣት ተጫዋች የሆኑት አቡበከር ናስር እና ሚኪያስ መኮንን እስከ 2017 ድረስ ለአምስት የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ቡና የሚያቆያቸውን ኮንትራት ከሰዓታት በፊት መፈረማቸው ይታወቃል። ይህን አስመልክቶ አቡበከር እና ሚኪያስ ረዘም ላለ ጊዜ በኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት የተስማሙበትን ምክንያት ሶከር ኢትዮጵያ በተመለከተ አጭር ቆይታ አድርገዋል።

አቡበከር ናስር

“የአሸናፊ በጋሻውን ታሪክ ለመድገም ኮንትራታችንን ለረጅም ዓመት አራዝመናል። ይህ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል። በኢትዮጵያ ቡና እስካሁን በቆየንበት ዓመታት ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በቀጣይም አቋማችንን ጠብቀን ለመዝለቅ እና የምንወደውን ኢትዮጵያ ቡናን እስከ መጨረሻው ለማገልገል ውላችንን የረዥም ዓመት ልናደርገው ችለናል።”

ሚኪያስ መኮንን

” ለኢትዮጵያ ቡና ካለን ከፍተኛ ፍቅር ኮንትራታችንን ለአምስት ዓመት ለማራዘም ወደናል። እኛን ለዚህ ያበቃን ክለባችንን ለቀን ላለመሄድ በማሰብ እና አንዳንድ በደሞዝ ጉዳይ ማሻሻያ ተደርጎልን ለመጫወት ችለናል። ባሳለፍነው እሁድ አንተም እንዳየኸው በአሸናፊ በጋሻው የዕውቅና ፕሮግራም ላይ ቃል ገብተን የነበረ በመሆኑ ያንን ቃላችንን ለማክበር በዛሬው ዕለት ስምምነታችንን ፈፅመናል።”

በአዲስ አበባ ሾላ ጉቶ ሜዳ አብረው ያደጉት ሁለቱ ወጣቶች ተስፋ ፍሬ ከሚባል ቡድን የእግርኳስ መነሻቸውን በማድረግ በሐረር ሲቲ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ባሳዩት ድንቅ አቋም ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በ2008 በጥምረት መጫወት ችለዋል። ያለፉትን አራት የውድድር ዓመታት በቡናማዎቹ ማልያ በመጫወት ያሳለፉ ሲሆን አሁን ደግሞ አንድ እና ሁለት ዓመት ውል መፈራረም ብቻ በተለመደበት የኢትዮጵያ እግርኳስ ባህል በተለየ ሁኔታ ለአምስት ተጨማሪ ዓመታት (እስከ 2017) በክለቡ ለመቆየት ተስማምተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!