“አቡበከር እና ሚኪያስ የኢትዮጵያ እግርኳስን አንድ ምዕራፍ አሻግረውታል” አቶ ገዛኸኝ ወልዴ

ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የሁለቱን ወጣት ተጫዋቾች አቡበከር እና ሚኪያስን ኮንትራት ረዘም ላለ ጊዜ ማራዘሙ ይታወቃል። ይህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ያልተለመደን አካሄድ እንዲሳካ በማድረግ ጥረት ያደረጉት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የዝውውሩ ሂደት ምን እንደሚመስል እና በቀጣይ ሁሉም ክለቦች ይህን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ያስተላለፉት መልዕክትን እንዲህ አቅርበነዋል።

“ከተጫዋቾቹ ጋር ተማምነን ነው ለቀጣይ አምስት ዓመት ለመጫወት የተስማሙት። ስምምነቱ አንደኛ በየዓመቱ በሚያሳዩት ወቅታዊ ብቃት መሠረት ባደረገ መልኩ ደሞዝ ስኬላቸው ከፍ እያለ ጥቅማጥቅማቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ተስማምተናል። በክለብ ውስጥ ለበርካታ ዓመት መቆየት የሚገኘውን ጥቅም በግልፅ አቅርበልናቸዋል። አቋማቸውን ጠብቀው የመሔዳቸው እድል ሰፊ በመሆኑ፣ በርካታ እና ብዙ ደጋፊ ባለው ክለብ ውስጥ ረዥም ዓመት መጫወት በራስ መተማመናቸውን እያዳበሩ የሚሄዱ መሆኑን፣ ለብሔራዊ ቡድንም ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀልናቸዋል ነው የአምስት ዓመት ኮንትራት የፈረሙት። ይህ ደግሞ ለአንድ ክለብ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ ክለቦች መለመድ እና መበረታታት ያለበት ጉዳይ ነው። አሁን የኢትዮጵያ እግርኳስ ውድቀት የሚመነጨው ተጫዋቾች በአንድ ላይ ሆነው ለበርካታ ጊዜ በአንድ ክለብ መቆየት አለመቻላቸው ነው። ይህን ተከትሎ ዘላቂነት ያለው ቡድን ለመገንባት ራሱን የቻለ ችግር ፈጥሯል። ይህ ደግሞ ብሔራዊ ቡድን ሲኬድ ተመሳሳይ ችግር ነው እየፈጠረ ያለው። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ እንዳይሄድ የሚያደርገው ስለሆነ ሁሉም አካል በዚህ መንገድ ለመሄድ ጥረት ማድረግ አለበት።

“አቡበከር እና ሚኪያስ ይህን ፕሮፌሽናል መንገድ አምነው ከክለቡ ጋር ለመሄድ ተደራድረው ለአምስት ዓመት በፈረማቸው ሊመሰገኑ ፣ ክብርም ሊሰጣቸው ይገባል። የኢትዮጵያ እግርኳስን አንድ ደረጃ ከፍ አድርገዋል ብዬ ነው የማምነው። ወጣቶች ናቸው፤ የነገ ብሩህ ተስፋቸውን አይተው በአንድ ክለብ ለበርካታ ዓመት መቆየት የሚሰጠውን ጥቅም ነው የተረዱት። ሌሎችም ተጫዋቾች በዚህ መንገድ ነው ማየት ያለባቸው። ቀጣይም የክለቡ አካሄድ መሆን ያለበት በዚህ መንገድ ነው። ረዣዥም ውል በመስጠት ተከታታይነት ያለው ቡድን መገንባት አለበት። ለዚህ ደግሞ መላው ደጋፊ ክለቡን ለማገዝ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለበት። ተጫዋቾች ማቆየት የምትችለው ገንዘብ ሲኖር ነው። ስለዚህ ክለቡ ገንዘብ ለማግኘት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ድጋፊ ሊያግዝ ይገባል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!