Soccer Ethiopia

“የዘመኑ ከዋክብት ገፅ” ከወንድሜነህ ደረጄ ጋር …

Share

ወደ ኢትዮጵያ ቡና በመጣበት በመጀመርያ ዓመቱ ጥሩ ብቃት ያሳየው ወንድሜነህ ደረጄ የዛሬ የከዋክብት ገፅ እንግዳችን ነው።

በቅርቡ ወደ ሊጉ ብቅ ካሉት እና ለቀጣይ ብዙ ተስፋ ከሚጣልባቸው ተከላካዮች አንዱ ነው። በተለይም በባህር ዳር ከተማ ባሳለፋቸው ሁለት ስኬታማ ዓመታት እና ዘንድሮ በኢትዮጵያ ቡና ከፈቱዲን ጀማል ጋር በፈጠሩት የሰመረ ጥምረት ሙገሳ ተችሮታል።

እግርኳስን ባደገበት አከባቢ በሚገኝ መርካቶ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ጀምሮ በክለብ ደረጃ በልደታ ክፍለከተማ የእግርኳስ ሕይወቱን “ሀ” ብሎ የጀመረው ወንድሜነህ ምንም እንኳ ልደታ የመጀመርያ ክለቡ ቢሆንም በክለቡ ከስድስት ወር የዘለለ ቆይታ አልነበረውም። በመቀጠል ወደ የከፍተኛ ሊጉ ክለብ አራዳ ክፍለከተማ በማምራት የአንድ ዓመት ቆይታ አድርጓል። ከአራዳ ቆይታው በኃላ ወደ ሱሉልታ ከተማ ያመራው ይህ ተከላካይ በቡድኑ ባሳየው ብቃት በ2010 ወደ ባህርዳር ከተማ ተዘዋውሮ በመጀምርያ ዓመቱ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲገባ የውድድር ዓመቱን ሙሉ ጨዋታዎች በጥሩ ብቃት ተጫውቶ ከሌሎች የቡድኑ አጋሮች ክለቡ ወደ ዋናው ሊግ እንዲገባ አስችሏል።

በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሁሉም የሊግ እርከኖች ተጫውቶ ፈጣን እድገት በማሳየት በሊጉ አሉ ከተባሉ የመሐል ተከላካዮች አንዱ መሆን ከቻለው ወንድሜነህ ደረጄ ጋር ያደረግነው አዝናኝ ቆይታን እንደሚከተለው አቅርበንላችኃል።

ጊዜውን የሚያሳልፍበት..

አብዛኛው ጊዜዬ በቤት ውስጥ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት ከዛ ውጭ የግል ልምምዶች በመስራት በተቻለኝ ከእንቅስቃሴ አልራቅኩም። ጊዜውም ለብዙ እንቅስቃሴ ስለማይመች በጣም አስፈላጊ ካልሆነ ከቤት አልወጣም።

ኳስ ተጫዋች ባይሆን…

ኳስ ተጫዋች ባልሆን በንግድ ላይ የምሰማራ ይመስለኛል። ምክንያቱም ያደግኩት እህል በረንዳ አከባቢ ነው። የንግድ ሰፈር ላይ ስላደግኩ ኳስ ተጫዋች ባልሆን ወደዛ የምሳብ ይመስለኛል።

በተቃራኒ ሲገጥመው የሚያስቸግረው …

ያን ያህል ፈትኖኛል የምለው ተጫዋች የለም። የምወዳቸው የማደንቃቸው ብዙ ተጫዋቾች አሉ፤ ግን በፈተና ደረጃ የምጠቅሰው ተጫዋች የለም።

የማይረሳቸው ጎሎች …

ካስቆጠርኳቸው ጎሎች የማልረሳው በከፍተኛ ሊግ ላይ ባህር ዳር ከተማ እያለሁ በግንባር ያስቆጠርኳት ግብ አልረሳትም። እኛ ላይ ከተቆጠሩት በጣም የምቆጭበት ደግሞ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን በገጠመበት ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ የተቆጠረችብን የአቻነት ጎል አስቆጪ ነበረች።

በመሐል ተከላካይ ላይ አብሮት ሲጣመር ምቾት የሚሰጠው…

አብሮኝ ሲጫወት በጣም የሚመቸኝ ፈቱዲን ጀማል ነው። ከሱ ጋር ስትጫወት ምቾት ይሰማሀል። ብዙ ነገር ያሟላ ተከላካይ ነው።

ከእግርኳስ የቅርብ ጓደኛው ..

አሁን ተራርቀናል እንጂ የባህር ዳሩ ግብ ጠባቂ ሥነ-ጊዮርጊስ የቅርብ ጓደኛዬ ነው። ምንተስኖት አሎም ቅርብ ጓደኛዬ ነው።

የእግርኳስ ሕይወቱ ምርጥ ዓመት ..

በ2010 ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያሳለፍኩት ዓመት ምርጡ ጊዜዬ ነው። ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገበት ዓመት ነበር። በግልም የዓመቱን ሙሉ ጨዋታዎች የተጫወትኩበት እና ጥሩ ብቃት ያሳየሁበት ዓመት ነበር። በክለብ ደረጃም ጥሩ መንፈስ የነበረው ስብስብ ነበር። በአጠቃላይ ውጤታማ ዓመት ነበረን።

በእግር ኳስ ያዘነበት እና የተደሰተበት ወቅት ..

የተደሰትኩበት ወቅት ባህር ዳር ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ነው። ያዘንኩበት ግን እንዲ በልዩ የማስታውሰው የለም፤ ከሽንፈት በኃላ ከሚሰማኝ ስሜት ውጭ በልዩ የማስታውሰው የለም።

አርዓያው…

ብዙ አሉ በቅርብ ፕሮጀክት እየሰሩ የማውቃቸው አሉ። ከነሱ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ዓብዱልራህማን ሙባረክ አሉበት። በይበልጥ ግን ሳምሶን ጥላሁን አርዓያዬ ነው።

የጊዜው የእርሱ ምርጡ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች …

ብዙ ምርጥ ተጫዋች አሉ። አንድ ምረጥ ካልከኝ ግን የጊዜው ምርጥ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው ነው።

ከጨዋታ በፊት የሚያደርገው የተለየ ልምድ…

ብዙም የተለየ ልምድ የለኝም። ግን ሁሌ ከጨዋታ በፊት ፀሎት አደርጋለሁ።

ከኳስ ውጭ የሚያዝናናው..

ከኳስ ውጭ የሚያዝናኑኝ ፊልም ማየትና ሙዚቃ መስማት ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top