በ1980 በኢትዮጵያ አስተናጅነት የተካሄደው የሴካፋ ውድድር በብዙ ነገሮች ተወጥራ የነበረችውን ሀገር በአንድነት ያቆመ ነበር። ከአፍሪካ ዋንጫው ድል ሃያ ስድስት ዓመታት በኃላ የተገኘው ይህ ጣፍጭና የመጀመርያ የሴካፋ ዋንጫ ወግ አጥባቂ ሶሻሊስቶች ሳይቀሩ ሰዓት እላፊውን ረስተው በደስታ የዘለሉበት ነበር።
ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ ከኬንያ ፣ ታንዛንያ እና ዛንዚባር ጋር በምድብ አንድ ተደልድላ ጨዋታዎቿን በአዲስ አበባ አድርጋለች። በአመዛኙ አዲስ ትውልድ ይዛ የቀረበችው ኢትዮጵያ የመክፈቻ ጨዋታዋን ከታንዛንያ ጋር አድርጋ ባዶ ለባዶ አጠናቀቀች። በሁለተኛ ጨዋታም በተመሳሳይ ከዛንዚባር ጋር በተመሳሳይ ያለ ጎል ተለያይታ ከብዙዎች የዋንጫ ግምት ውጭ ሆነች። ሆኖም በሦስተኛው ጨዋታ ጠንካራዋ ኬንያን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ በአምስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ዛንዚባርን ተከትላ ወደ ቀጣይ ዙር አለፈች።
በመቀጠል በግማሽ ፍፃሜው የወቅቱ ስመ ገናና ቡድን ዛምቢያን አራት ለባዶ አሸንፋ የመጣችው የውድድሩ ቁንጮ ዩጋንዳን ሦስት ለባዶ በመርታት ወደ ፍፃሜ አለፈች። በፍፃሜው ጨዋታም ዚምባብዌን ገጥማ እስከ ተጨማሪ ደቂቃ ስትመራ ብትቆይም የወቅቱ ድንቅ አጥቂ ገብረመድኅን ኃይሌ በመጨረሻዎቹ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ባስቆጠራት ግብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ። ጨዋታው በተጨማሪ ደቂቃዎች ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ባለማስቆጠራቸው ወደ መለያ ምት አምርተው ጨዋታው በድራማዊ ትዕይንቶች ታጅቦ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።
በውድድሩ ድባብ እና ጨዋታውን በቴሌቪዥን ሲያስተላልፍ የነበረው ደምሴ ዳምጤ የሚታወሱ ገለፃዎች አሁንም ድረስ ከኢትዮጵያዊያን አዕምሮ ስላልወጣው ውድድር የወቅቱ የቡድኑ አምበል የነበረው እና ወሳኟን የፍፃሜ ግብ ያስቆጠረው እንዲሁም ውድድሩን በተጫዋችነት እና ኋላ ላይ ደግሞ በረዳት አሰልጣኝነት ያሸነፈው ገብረመድኅን ኃይሌ ትውስታውን በዚህ መልኩ አጋርቶናል።
” ወቅቱ ትልቅ ሀገራዊ አንድነት ያስገኘ ውድድር ነበር፤ ቡድናችን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ ነበር ውድድሩን የጀመረው። ሴካፋ ዋንጫ እንደ አሁኑ የምስራቃ አፍሪካ ሃገራትን ብቻ ሳይሆን የመካከለኛ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራትን ያካተተ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት ነበር። ቅድም እንዳልኩህ በውድድሩ ጅማሮ ነጥቦች ጥለን ነበር፤ ከዛ ግን ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፈን ወደ ጥሩ መንፈስ የመጣንበት ውድድር ነበር።
“የፍፃሜው ጨዋታ ብዙ ድራማዎች ነበሩት። አንዱ በጨዋታው የነበረው እንቅስቃሴ፣ የደጋፊያችን ጉጉት እና በጨዋታ መሐል የነበረው ተጫዋቾቻችን ጉዳት እና ድካም ነበር። ብዙ ተሰላፊዋቻችን ደክመው መጠነኛ ጉዳታቸውን ተቋቁመው ነበር ጨዋታውን ያካሄዱት። ሌላው የማልረሳው ደግሞ ጎሏ የገባችበት መንገድ እና ደቂቃው ነው። ከመስመር የተሻማችው ኳስ በግምባር ለማስቆጠር ከሚያዳግት ቦታ ነበር ገጭቼ ያስቆጠርኳት። ሌላው ደቂቃው ነው፤ መደበኛ ሰዓት ተጠናቆ የተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ሊያልቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩት ነበር ጎሉን አግብቼ አቻ የሆንነው። እንደውም ግቡ ካስቆጠርን በኃላ ደስታችን ገልፀን ልክ እንደገባን ነው የጨዋታው ማጠናቀቂያው ፊሽካ የተነፋው።
“በጣም የሚገርመው እና አጓጊ የነበረው ደግሞ የመለያ ምቱ ድራማ ነው። እኔ፣ ነጋሽ ተክሊት እና አማኑኤል ኢያሱ በተከታታይ መለያ ምቶቹን አስቆጠርንና እነሱ አንድ አስቆጥረው፤ ተካበ ሁለት መልሶ ሦስት ለአንድ መራን። ከዛ ቀጥሎ በቀለ ብርሀኑ ሳተ፤ በድጋሚ ዕድል ተሰጥቶትም ሳተውና እነሱ አገቡ። ከዛ በኃላ የነበረው አምስተኛ መቺው መንግሥቱ ሁሴን ቢያገባው እናሸንፍ ነበር፤ ሆኖም ሳተና ሦስት አቻ ሆን ውጥረት ውስጥ ገባን። ከዛ ግን ወደ ተጨማሪ ምት ተሸጋግረን የዚምባብዌ መቺ ሳተና እኛ በዳኛቸው ደምሴ አማካኝነት አስቆጥረን ጨዋታውን አሸነፍን።
“ከጨዋታው በኃላ የነበረው ደስታ ልዩ ነበር። የህዝቡ ስሜት በቃላት ለመግለፅ ይከብዳል። ጨዋታው ልክ እንደተጠናቀቀ ህዝቡ ደስታውን መቆጣጠር አቅቶት ሜዳ ውስጥም ገብቶ ነበር። በዛን ወቅት የሰዓት እላፊ ነበር። ዋንጫውን ካነሳን በኃላ ግን በደስታ ብዛት ለቀናት የሰዓት እላፊው ተነስቶ ነበር። ሀገራዊ አንድነት እና ጥሩ የእግርኳስ መነሳሳት የነበረበት ወቅት ነው። ”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!