በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው አይቮሪ ኮስት የወዳጅነት ጨዋታ ልታደርግ ነው

በምድብ 11 ከኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር እና ኒጀር ጋር የተደለደለችው አይቮሪ ኮስት በመስከረም ወር መጨረሻ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዛለች።

የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ 2022 ለተሸጋገረው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ የወዳጅነት ጨዋታዎቸን ለማድረግ መርሐ-ግብር እያወጡ ነው። በምድብ 11 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደለደሉት ዝሆኖቹም ከጥቅምት መጨረሻ ቀናት ጀምሮ እስከ ህዳር 8 ድረስ ለሚደረጉ የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎች ለመዘጋጀት ይረዳቸው ዘንድ ከጠንካራዋ ናይጄሪያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ አስበዋል።

አይቮሪኮስቶች ከሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለድሏ ናይጄሪያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ መስከረም 28 በአውስትራሊያ እንደሚደረግ ተነግሯል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአይቮሪኮስት ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርጉት ናይጄሪያዎች ከዝሆኖቹ ጋር ከተጫወቱ ከ4 ቀናት በኋላ ከቱኒዚያ ጋር እዛው አውስትራሊያ ላይ ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።

ከሁለት ጨዋታ ሦስት ነጥቦች ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ በምድቡ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች ከኒጀር ጋር በጥቅምት ወር እንደምትጫወት ቢታወቅም እስካሁን ከአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሮ ምንም እንቅስቃሴ እየታየ አይገኝም። ፌዴሬሽኑም ለጨዋታዎቹ ለመዘጋጀት የመንግሥትን ፍቃድ እየጠበቀ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!