በክፍል 11 የ’ይህን ያውቁ ኖሯል?’ ጥንቅራችን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ኮከቦችን የተመለከተ ተከታይ ዕውነታዎችን አዘጋጅተን ቀርበናል።
– የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ እና አካሄድ የተጀመረው በ1990 እንደሆነ ይታወቃል። በዚህኛው ዓመት በተደረገው የውድድር ዘመንም ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው የተመረጡት አሠልጣኝ ሐጎስ ደስታ ናቸው። በጊዜው መብራት ኃይልን እየመሩ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ ያነሱት አሠልጣኝ ሐጎስ የመጀመሪያው የሊጉ ኮከብ አሠልጣኝ ተብለው የታሪክ መዝገብ ላይ ተመዝግበዋል።
– በ22 ዓመት የሊጉ ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት ኮከብ ተብለው የተመረጡት አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ናቸው። አሠልጣኙ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባሰለፏቸው አጠቃላይ አምስት ዓመታት (1997፣ 1998፣ 2000፣ 2001 እና 2002) ሁሉ ኮከብ ተብለው በመመረጣቸው ነው ቀዳሚ የሆኑት።
– በርካታ አሠልጣኞቸን በኮከብነት ያስመረጠው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ጊዮርጊስ በ1991 ወደ ሊጉ ከመጣ በኋላ እስካሁን ለ14 ጊዜያት ኮከብ አሰልጣኞቸን በማስመረጥ ቀዳሚው ክለብ ሆኗል።
– የኮከብ አሠልጣኝነት ምርጫ ዋንጫ ካነሱ ክለቦች ሲመረጥ ይስተዋላል። አልፎ አልፎ ከኮከብ አሠልጣኝነት በተጨማሪም የታታሪ አሠልጣኝ ሽልማት በሊጉ ጥሩ ጉዞ ላደረጉ አሠልጣኞች ሲበረከት ይታይ ነበር።
– ከታችኛው የሊግ እርከን ክለቡን ባሳደገበት ዓመት ኮከብ ተብሎ በሊጉ የተመረጡ ብቸኛ አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ናቸው። አስራት በ1991 ዓ/ም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከታችኛው የሊግ እርከን አሳድገው በመጀመሪያ ዓመታቸው የሊጉን ዋንጫ አግኝተዋል። በዚህም አሥራት የሊጉ ኮከብ አሠልጣኝ ተብሎ ተመርጠዋል።
– እስካሁን አራት የውጪ ሃገር ዜጎች በሊጉ ኮከብ አሠልጣኝ ተብለው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። እነሱም ሚቾ (አምስት ጊዜ)፣ ማርት ኑይ (ሁለት ጊዜ) ፔርሉጂ ዳንኤሎ እና ሬኔ ፌለር ናቸው። በተቃራኒው 9 የሃገራችን አሠልጣኞች ደግሞ በሊጉ ኮከብ ተብለዋል። እነሱም ሐጎስ ደስታ፣ አሥራት ኃይሌ (2)፣ ጉልላት ፍርዴ፣ ሥዩም ከበደ (2)፣ ከማል አሕመድ (2)፣ ውበቱ አባተ፣ ፋሲል ተካልኝ፣ ንጉሤ ደስታ እና ገብረመድህን ኃይሌ (2) ናቸው።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ግብ ጠባቂነት ሽልማት መሰጠት የተጀመረው በ2003 ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የግብ ጠባቂዎች ዘርፍንም ኮከብ ተብሎ ያገኘው የሲዳማ ቡናው የግብ ዘብ ሲሳይ ባንጫ ነበር።
– ከ2003 ጀምሮ መሰጠት የተጀመረውን የኮከብ ግብ ጠባቂዎች ሽልማትን 2 ኢትዮጵያዊ የግብ ዘቦች ብቻ ናቸው ማግኘት የቻሉት። እነሱም ሲሳይ ባንጫ እና አቤል ማሞ ናቸው።
– ለበርካታ ጊዜያት የኮከብ ግብ ጠባቂነትን ክብር ያገኘው ተጫዋች ሮበርት ኦዶንካራ ነው። ሮበርት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እየተጫወተ ለ5 ተከታታይ የውድድር ዓመታት (2004፣ 2005፣ 2006፣ 2007፣ 2008፣ 2009) ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ ተመርጧል። በዚህም ለበርካታ ጊዜያት በኮከብነት በመመረጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።
– በ9 ዓመታት የግብ ጠባቂዎች ሽልማት ታሪክ 5 ግብ ጠባቂዎች ይህንን ክብር አግኝተዋል። እነሱም ሮበርት ኦዶንካራ (5 ጊዜ)፣ ሲሳይ ባንጫ፣ አቤል ማሞ፣ ዳንኤል አጃይ እና ፍሊፕ ኦቮኖ ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!