በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ላይ በተለያዩ ክለቦች እና ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች ለረጅም ዓመታት ያሰለጠነው አሰልጣኝ አሥራት አባተ የዛሬው እንግዳችን ነው።
በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ዕድገት ላይ አበርክቶ ካላቸው ቀዳሚ ሙያተኞች መካከል አሥራት አባተ አንዱ ነው፡፡ የተወለደው ድሬዳዋ ቀፊራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ አባቱ አቶ አባተ ከፈኔ ከቀድሞ ተጫዋች ከአሁኑ አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ጋር ለድሬዳዋ ኮተን እና በቀደመው የሐረርጌ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተጫውተው አሳልፈዋል። የያኔው ታዳጊ አሥራት ምንም እንኳን በምስራቋ ፈርጥ ከተማ ቢወለድም ከወላጅ እናቱ ውዴ ካሣሁን ጋር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኃላ በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪነቱ በጥበብ ዕድገት እና በሁለተኛ ደረጃ የካቲት 12 (መነን) እግርኳስን ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር መጫወት ጀመረ። በትምህርት ቤት ውስጥ ከመጫወት ባሻገር ባደገበት ጉለሌ አካባቢ ላሉ የቀበሌ እና የወረዳ ቡድኖች እንዲሁም በመድን ታዳጊ ቡድን ውስጥ ገብቶ በመጫወት የቆየ ሲሆን በተጫዋችነቱ ይቀጥላል ተብሎ ሲጠበቅ እሱ ግን ገና በጊዜ ወደ ሥልጠናው ጎራ ተቀላቅሏል።
በመድን ታዳጊ ቡድን እያለ ቲ ሲ ኤፍ የሚባል የእርዳታ ድርጅት በሚያዘጋጀው ውድድር የድርጅቱን የጉለሌ ቡድን ይዞ ማሰልጠንን ጀምሯል። በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ለፒ ፒ አይ ኤፍ በቢሾፍቱ ደግሞ ሮሪንግ ለሚባሉ ቡድኖች እየተጫወተም ክረምቱን የጤና ቡድን ያሰለጥን ነበር። በመቀጠል በአለቤ ሾው ስር የነበሩ ተጫዋቾች በሁለት ቡድን ተከፍለው በዕድሜ አነስ ያሉትን እንዲያሰለጥን ኃላፊነት ተሰጠው። እነ ዙለይካ ፣ ሕይወት (የቀድሞዋ የመብራት ኃይል አሰልጣኝ) ፣ ከርክ (የአዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ) የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በመያዝ በ1996 በአለቤ ቡድን ወደ ማሰልጠኑ በመግባት ቡድኑ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን እንዲያድግ አድርጓል። ሆኖም በቀጣዩ ዓመት ለብዙዎቹ ሴት ተጫዋቾች መሠረት የጣለው አለባቸው ተካ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ የቡድኑ ህልውና ሲያበቃ አሰልጣኝ አሥራት በወቅቱ በአለቤ አማካኝነት ወደ ኮተቤ ኮሌጅ ገብቶ የመማር ዕድሉን በማግኘቱ ራሱን በዕውቀት እየገነባ ጎን ለጎንም የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች መውሰዱን ቀጠለ።
በመቀጠል አሰልጣኝ አሥራት አባተ ከ1999-2002 ድረስ ከአሰልጣኝ ዓለማየሁ ጌታቸው ጋር በጋራ በመሆን ኢንጅነር ሰለሞን በሚባል ግለሰብ የሚረዳ አራዳ ጊዮርጊስ የተባለ ቡድንን በ200 ብር ይዞ ማሰልጠን ጀመረ። ያም ቢሆን ቡድኑን ማስቀጠል ቀላል መሆን አልቻሉም። “አሁንም በጋዜጠኝነት እየሰራ ካለው አብርሀም ተክለማሪያም ጋር ሆኜ ቡድኑን እንደምንም ለረጅም ጊዜ ለመግፋት ሞከርን። እሱ በትርፍ ሰዓቱ ሚኒባስ ይሰራል ፤ እኔም ትምህርት ቤት አስተምራለሁ። ከዛም ከመምህራን ሁለት ሁለት ብር እየቆረጥን ከደመወዝ 50 ብር የትራንስፖርት በወር እየከፈልን ተጫዋቾችን ደግሞ በትምህርት እና በተለያዩ ቦታዎች እየሰበሰብን ነበር የምናሰለጥነው። እንደዛም እያደረግን ትላልቅ ተጫዋቾች ይወስዱብን ነበር። አስታውሳለሀ ምህረት መለሰ የምትባል ተጫዋች ወደ ምርት ገበያ ስትሄድ ሦስት መቶ ብር ኳስ መግዣ ብላ ሰጥታን ነበር። እንደምንም እስከ 2002 ቆየን። ቡድኑ እየተመናመነ 12 ተጫዋች ቀሩን። 11 ተጫዋች ሜዳ ገብቶ እንደምንም ሰባት ሆነው እንዲጨርሱ ተደርጎ በዛው ክለቡም ፈረሰ እኔም በ2003 ወደ ደደቢት ሄድኩ።” ሲል የአራዳ ጊዮርጊስ አስቸጋሪ ቆይታውን ያስታውሳል።
“ክለቦች በአስገዳጅ መልኩ የሴቶች ቡድን እንዲይዙ የተባለበት ወቅት ነበር። ይሄ ከመሆኑ አንድ ዓመት ቀድሞ ደደቢት በኮሎኔል ዐወል አማካኝነት ቡድን አቋቁሞ ነበር። በወቅቱ ከእነመሸሻ ወልዴ ፣ ኑራ ኢማም እና ዳግም ዝናቡ በቀር ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ ሚዲያዎችም ብዙም አልነበሩም። ነገር ግን ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የነበረበት እና በሀገር ዓቀፍ ደረጃም ትኩረትም እየተሰጠው ነበር። በወቅቱ ደደቢት የቀድሞው ኢትዮጵያ ቡናን ነበር የሚመስለው ፤ ቆንጆ ኳስ የሚጫወት በድን ነበር። ቡድኑን በ23 ተጫዋቾች ነበር ያቋቋምነው። አራዳ ጊዮርጊስ አብረውኝ ከነበሩ 11 ተጫዋቾች መካከል እንደነቅድስት ቦጋለ ፣ ሀድራ ፣ ኬኒያ ፣ ኤደን እና ኦሌምቤን አድርገን የሠራነው ቡድን ነው። ጥሩ እግርኳስን በመጫወት ውጤታማ የሆነ ቡድን መስራት የቻልኩበት እና በግሌም እውቅና ያገኘሁበት ነበር።” የሚለው አሥራት ደደቢትን ከ2003 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ሲያሰለጥን ክለቡ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ያየለ ተፅዕኖ እንዲኖረው በማድረጉ ረገድ የጎላ ድርሻ ነበረው፡፡ በቆይታውም ደደቢት 2003 ላይ በአዲስ አበባ ዲቪዚዮን ከሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ሲያደርግ በ2004 ፕሪምየር ሊጉ በአምስት ክለቦች ሲቋቋም የመጀመሪያውን ዋንጫ እንዲያነሳ ረድቷል ፤ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝም መሆን ችሏል። በ2005 እና 2006 ደግሞ ቡድኑን በመለያ ምት በተከታታይ በንግድ ባንክ ዋንጫውን ሲነጠቅ በሁለተኝነት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በ2007 የሰማያዊ ቤት ቆይታው በሊጉ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቅ የፀባይ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎች ክብርን አግኝቷል።
አሰልጣኝ አሥራት ከደደቢት በመቀጠል የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የማሰልጠን ዕድል ገጥሞታል። አሰልጣኙ ይህን ቡድን ይዞ በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ብዙ ርቀት መጓዝ ችሏል። ብሔራዊ ቡድኑ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ አልተቆጠረበትም። ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎችም በአንዱ ብቻ ነበር ሽንፈት የገጠመው። አውሮፕላን በማጣት ብዙ ችግር በደረሰበት የካሜሮን ጨዋታ 0-0 ተለያይቶ ሲመለስ ባህርዳር ላይ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ የነበረችውን ቡርኪናፋሶን ከሌላ የጉዞ እንግልት በኋላ በዝግ ስታድየም በጥይት ድምፅ በታጀበ ጨዋታ አሸንፎ በሜዳው ያለግብ ተለያይቷል። በመጨረሻው ጨዋታ በጋና እስኪሸነፍ ድረስም ማጣሪያውን ለማለፍ ከጫፍ ደርሶ ነበር።
አሰልጣኙ ከ20 ዓመት ቡድኑ ባለፈ ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ይዞ በድጋሚ እስከ መጨረሻው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ድረስ እልህ አስጨራሽ ጉዞን በማድረግ ከጫፍ ደርሶ አሁንም ከልምድ እጦት ሳይሳካለት ቀርቷል። አሰልጣኝ አሥራት አባተ ካመጣው የወጣት ቡድኖቹ ውጤት አንፃር ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት ሲጠበቅ ዕድሉን አለማግኘቱ ከሴቶች እግርኳስ ዘወር ብሎ ፊቱን ወደ ወንዶቹ ለመመለሱ እንደ ምክንያት ይነሳል፡፡ የአሰልጣኙ ቀጣይ አሰተያየትም ይህን ሀሳብ ያንፀባርቃል። “በሁለቱም ቡድኖች ካመጣውን ውጤት አንፃር አንድ ነገር ይሰጠኛል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። በዚህ እኔ ብቸኛ ነኝ ማለት ይቻላል። ከ14 ዓመታት በላይ በሴቶች እግርኳስ ከሰራው ከብርሀኑ በመቀጠል በረዳትነት ከመሥራት ውጪ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ያላሰለጠንኩት እኔ ብቻ ነኝ። ብርሀኑ ፣ ሰላም ፣ መሠረት እና በኃይሏም ያገኙትን ዕድል እኔም እጠብቅ ነበር። ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር። እና በወቅቱ ወንዶችን የማግለል ሁኔታዎች ሁሉ ተጀምረው ነበር። ለማስታወስ ያህል ለኦሊምፒክ ማጣሪያ የአብርሀም ተክለሃይማኖት ረዳት ሆነን እኔና ብርሀኑ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ነበርን። እስከ መጨረሻው ሄደን በደቡብ አፍሪካ ነው የወደቅነው። ያው ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ልናደርግ ስንል ሴት አሰልጣኝ መግባት አለባት በሚል በአንድ ሰው ገፋፊነት እኔና ብርሀኑ ውጤት እያለን እንድንቀስ ተፈለገ። በወቅቱ ቡድኑ መጎዳት ስለሌለበት እኔና ብርሀኑ ራሳችንን ልናገል ነበር። እኔ ግን ቡድኑ ለምን ይጎዳ የለፋንበት ስለነበር ብርሀኑ እንዲሳተፍ አድርጌ እኔ ወጥቻለሁ። ያውም በክለብ 1500 ነበር የሚከፈለኝ በአፍሪካ ቡድን በመግባት ውስጥ መቶ ምናምን ሺህ ብር ተሸልሟል። ያኔ ካለ ውድድር በኃይሏ ገብታለች። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ደግሞ እንድትሸሽ የሚያደርጉህ ነበሩ። ዋናውን ብሔራዊ ቡድን አለማሰልጠኔ ጥሩ ትውልድ ነበረበት። ሁለቱን ወጣት ቡድኖች ጨምቄ አንድ ነገር ለመስራት አስብ ነበር። ያንን ለማድረግ ሁኔታዎች ሊመቻቹልኝ አልቻሉም። ይሄ ደግሞ ከዓለም ዋንጫውም በላይ ቁጭት ይፈጥራል።”
በ2009 አሰልጣኙ የብሔራዊ ቡድን ቆይታውን ካጠናቀቀ በኃላ የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ቡድንን መረከብ ቻለ። ቡድኑን ከማቋቋም እንዲሁም በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በማድረጉ ረገድ በወቅቱ አሰልጣኙ ጥሩ ሚናም ነበረው። በተለይ ልምድ ያላቸውን ልምድ ከሌላቸው ጋር በማቀናጀት የፈጠረው ስብጥር መልካም ነበር፡፡ በዓመቱ አጋማሽ ግን የፕሪምየር ሊጉ አዲስ አዳጊ የነበረው የወንዶቹ ቡድን አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን በማሰናበት አሥራትን የወንዶች ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ ሾመው፡፡ በሴቶች እግር ኳስ ትልቅ ድርሻ የነበረው አሥራትም በእርሱ አገላለፅ ‘ከማይጥሙ ከባባቢዎች ለመራቅ’ ሲል ወደ ወንዶች በቀጥታ ገብቶ አዲስ አበባ ከተማን በከፍተኛ ሊግም እስከ 2010 ድረስ መርቷል፡፡ 2011 መግቢያ ላይ በርካታ ክለቦች የአሰልጥንልን ጥያቄ ቢያቀርቡለትም እሱ ቢሾፍቱ ከተማን ተረክቦ ማሰልጠን ጀመረ። “ቢሾፍቱ ከተማ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩበት ወቅት ነበር። ጥሩ ኳስ ጠንካራ ስብስብ ያለው ቡድን ነበር። ጥሩ ነገርም ሠርተን ቶርናመንት ማስገባትም ችያለሁ። በዛም ውጤት ከከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ሌሎች ክለቦች ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ግን አሜሪካ ሀገር ለኮርስ ሄጄ እያለ የቡታጅራ ከተማ ፕሬዝዳንት አቶ ነስረላ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየቱ እና ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ቢሆንም ለማሻሻል መፈተኑን ስለፈለኩት ወደዛ ሄጃለው።” በማለት
ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ስለነበረው የአሰልጣኝነት ጊዜ ይናገራል።
አሰልጣኙ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሐ’ ቡታጅራ ለረጅም ጊዜያት ምድቡን እንዲመራ ያስቻለ ቢሆንም በኮቪድ ምክንያት ውድድሩ በመቋረጡ የፕሪምየር ሊግ ግስጋሴውን ዳር ማድረስ ሳይችል ቀርቷል። ከክለቡ ጋር ነሀሴ 30 ውሉ የሚጠናቀቀው አሥራት አባተ የሊደርሺፕ እና ማኔጅመንት ምርቅ ሲሆን ከአሰልጣኝነቱ ጎን ለጎንም በመምህርነት ሙያም ሲሰራ ቆይቷል። በአመዛኙ በራሱ ጥረት (አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ ካደረገለት የአውሮፕላን ቲኬት ድጋፍ ውጪ) በአሜሪካ እና በስፔን የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡ 2003 ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ረዳት ሆኖ ሲሰራ የመኪና አደጋ አስተናግዶ በህክምና ካገገመ በኋላ ዳግም ወደ ሙያው ተመልሶ እስካሁን የዘለቀው አሰልጣኝ አሥራት አባተ ከጎኑ ለነበሩ ሁሉ በዚህ መልኩ ምስጋናውን በማቅረብ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ቆይታ አጠናቋል። “በመጀመሪያ ጤናዬን አግኝቼ ሥራዬን እየሠራሁ እንድኖር ለረዳኝ ፈጣሪ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በመቀጠል ቤተሰቦቼን በትለይ እናቴ ውዴ ካሣሁን እና ልጄ ሄርሜላ አሥራትን አመሰግናለሁ። በተለይ እናቴ ‘አንድ ነገር ማሳካት ይችላል’ ብላ ስለምታምን ከእኔ ጋር ትለፋ ስለነበር በምክርም አይዞህ በማለትም አስተዋጽኦ ነበራት። ከድሬዳዋ ከመጣሁ በኃላ ያለአባትም ስላሳደገችኝ ማመስገን እፈልጋለሁ። በሠራሁባቸው ክለቦች ሁሉ ሁሉም ተጫዋቾች እና አመራሮች በምሰራው ስራ ደስተኛ ስለሆኑ ለስራዬ ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር። ሁሉንም ድጋፍ ላደረጉልኝ ማመስገን እፈልጋለሁ። በትምህርት ቢሆን ወደ ሥልጠናው ዓለም እንድገባ ለረዳኝ በህይወት ባይኖርም ለእኔ ብቻም ሳይሆን ለብዙዎቻችን ክለብ አሰልጣኞች ፈር የቀደደውን አለቤን ነብሱን አሁንም በገነት ያኑራት እላለሁ። ኮሎኔል ዐወልን ጨምሮ በየትኛውም ክለብ አብረውኝ ለነበሩ ለሁሉም ማመስገን ፈልጋለሁ። ታምሜ ላሳከሙኝ ፋልከን አካዳሚ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አመሰግናለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!