ቅዱስ ጊዮርጊስ የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ለመቅጠር ወሰነ

አሰልጣኝ አልባ ቢሆንም ተጫዋች ለማስፈረም እና ውል ለማራዘም እየተስማማ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የውጭ አሰልጣኝ ለመቅጠር እንደወሰነ ለማወቅ ተችሏል።

ያለፉትን አስራ ስድስት ዓመታት ከውጭ ሀገር በሚመጡ የተለያየ ዜግነት ባላቸው አሰልጣኞች ሲመሩ የቆዩት ፈረሰኞቹ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭን ካሰናበቱ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ አሰልጣኝ በማዞር ይቀጥራሉ ተብሎ የነበረ ሲሆን ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ውበቱ አባተ ጋር ሥማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱም ይታወሳል። ሆኖም የክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ ባደረገው ስብሰባ የውጭ ሀገር አሰልጣኝን በድጋሚ ለመቅጠር ወስኗል።

የአሰልጣኙ ማንነት ክለቡ እስካሁን ይፋ ባያደርገውም ከውጭ ሀገር ይመጣሉ ከተባሉት አሰልጣኝ ጋር በሁሉም የመደራደርያ መስፈርቶች ከስምምነት ደርሰዋል። ሆኖም አሰልጣኙን ወደ ሀገሩ ውስጥ እንዲመጡ እና ክለቡን እንዲረከቡ ለማድረግ ቢታሰብም ሊጉ የሚጀመርበት ቀን ቁርጡ አለመታወቅ እንዳዘገየው ታውቋል። ሊጉ የሚጀመርበት ቀን ሳይታወቅ አሰልጣኙን እዚህ አምጥቶ ማስቀመጡ ክለቡን አላስፈላጊ ወጪ መዳረግ በመሆኑም ለጊዜው አሰልጣኙ የሚመጡበት ቀን እንዲዘገይ ሆኗል።

በቀጣይ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ክለቡን የሚያሰለጥኑት እነማን ናቸው? የሚለውን በተመለከተ አዲሱ አሰልጣኝ የሚወስኑት ጉዳይ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1996 ሆላንዳዊው ሀንስ ቫንደር ፕሊዩምን ካመጣ ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ፊቱንወደ ውጪ ሀገራት አሰልጣኞች ያዞረ ሲሆን ያለፉትን አስራ ስድስት ዓመታት የሆላንድ፣ ሰርቢያ፣ ቦስኒያ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ፖርቱጋል እና እንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኞችን ሲቀጥር መቆየቱ ይታወቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!