የባህር ዳር እና ሶዶ ስታዲየሞች ዛሬ ተገምግመዋል

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ጤና ሚኒስቴር የተወጣጣው ልዑካን ቡድን የስታዲየሞች ግምገማ ማከናወኑን ቀጥሎ ዛሬም በባህር ዳር እና ሶዶ የሚገኙ የእግርኳስ መሠረተ ልማቶችን ሲመለከት ውሏል።

በኮቪድ-19 ምክንያት የተቋረጡት የሃገራችን የእግርኳስ እንቅስቃሴዎች ዳግም በ2013 እንዲመለሱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ የውድድር መመሪያ መነሻ ሰነድም አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቦ ነበር። ታድያ ውድድሮች ሲመለሱ የሚከወኑባቸው ስታዲየሞች ተለይተው ከረቡዕ ጀምሮ ግምገማ እየተደረገባቸው ይገኛል። ከፌዴሬሽኑ እና ጤና ሚኒስቴር ከተወጣጡት ሦስቱ ልዑኮች መካከለም አንደኛው ልዑክ በባህር ዳር ከተማ ሌላኛው ደግሞ በሶዶ በመገኘት ምልከታዎቸን አከናውኗል።

ከትላንት በስትያ የጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየምን ተመልክቶ የነበረው ልዑክ ከረፋድ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ 7 ሰዓት ድረስ በባህር ዳር ከተማዋ እየተዘዋወረ ለእግርኳስ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ሲመለከት ቆይቷል። በመጀመሪያም ልዑኩ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ተገኝቶ የሜዳውን ምቹነት ገምግሟል። ከሜዳው ምቹነት በተጨማሪ የተቀየሪ ተጫዋቾች መቀመጫ፣ የሚዲያ አካላት ቦታ፣ የተጫዋቾች ማረፊያ ክፍል፣ የተጋባዥ እንግዶች መቀመጫ ስፍራን እና የዳኞችን ክፍል ተመልክቷል። ከእነዚህ ውጪም በስታዲየሙ ውስጥ የሚገኙ እና ለጤና ምርመራ አመቺ የሆኑ ክፍሎችን አይቷል።

ከስታዲየም በመቀጠል በከተማዋ የሚገኙ የልምምድ ሜዳዎችን፣ የቡድኖች ማረፊያ ሆቴሎችን እና የባህር ዳር ከተማን የተጫዋቾች ካምፕ ተመልክቷል። ልዑካኑም በነገው ዕለት ወደ ደብረማርቆስ ጉዞውን በማድረግ የደብረማርቆስን የመጫወቻ ሜዳ እንደሚመለከት ተነግሯል።

በሀዋሳ ትናንት ምልከታ ያደረገው ልዑክ ቡድንም ሶዶ በመገኘት ልክ እንደ ባህር ዳር ሁሉ በከተማዋ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን ሲገመግም ውሏል

ግምገማው ቀጥሎ በስተደቡብ እና ምስራቅ የተጓዙት ሌሎቹ ልዑካኖች ከነገ ጀምሮ ባሉት ቀናትም ምልከታቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል። በአጠቃላይም በሃገራችን የሚገኙ እና ለውድድር ምቹ ናቸው ተብለው የተመረጡትን 17 ሜዳዎች እስከ ጿጉሜ 4 ድረስ ገምግሞ ለማገባደድ እቅድ መያዙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!