አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡
ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው የትኛውም የሚያጠቃ ቡድን ዓላማ የተቃራኒ ቡድንን የመከላከል አቅም በመቋቋም ጎል ማስቆጠር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጫና የሚቋቋሙ ተጫዋቾች በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡
ጨዋታን መመስረት
አንዳንድ ቡድኖች ኳስን በረዥሙ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ከመላክ ይልቅ ጨዋታን ከኋላ መመስረት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ታዲያ እንደ እነዚህ አይነቶቹ ቡድኖች በተጋጣሚዎቻቸው አማካኝነት ብርቱ ጫና ስለሚበዛባቸው በከፍተኛ ደረጃ ጫናን የሚቋቋሙ ተጫዋቾች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ” ከተቃራኒ ቡድን ተሽሎ መጫወት ማለት የተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል ጋር ቶሎ-ቶሎ መድረስ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም በላቁ መንገዶች መድረስ ማለት እንጂ፡፡” ዣቪ አሎንሶ
ስፔናዊው አማካይ እንደገለጸው የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ጋር በተሻለ ሁኔታ ለመድረስ የተጋጣሚ ጫናን በጥሩ ሁኔታ ማለፍ ጠቃሚ ነው፡፡ ሰርጂዮ ቡስኬትስ፣ ጆርጊኒሆ እና ሙሳ ዴምቤሌን የመሳሰሉት አማካዮች ለቡድናቸው በመጀመሪያው የጨዋታ ምስረታ ወቅት በጣም አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያትም ጨዋታን ከኋላ በመመስረት ሒደት እጅግ አደገኛው እና ጥንቃቄ የሚሻው እንቅስቃሴ እዚህ ቦታ ስለሚደረግ ነው፡፡ በተጋጣሚ ቡድን ጫና ሳቢያ አልያም በራስ ቡድን ስህተት ኳስ የመነጠቅ አጋጣሚ ከተፈጠረ ከባድ ዋጋ ያስከትላል፡፡
ከታች የቀረበው ምስል በ2015/16 ባርሴሎና አትሌቲክ ቢልባኦን ባስተናገደበት ግጥሚያ ጨዋታን ከኋላ ስለመመስረት ሒደት ያሳያል፡፡
በመጀመሪያው ምስል ቡስኬትስ ከቴርስቴገን ኳስን ሲቀበል እና ከጀርባው የቢልባዎ ተጫዋች ጫና ሲያደርግበት እናያለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በባርሴሎና ተጫዋቾች አቅራቢያ የሚገኙ ሁሉም የመቀባባያ አማራጭ መስመሮች በማያስተማምኑ ሁኔታዎች በቢልባዎ ተጫዋቾች ሰውን-በ-ሰው በመጫን (Man-Oriented Press) የመከላከል አጨዋወት እንዴት ጫና እንደሚያደርጉባቸው እናስተውላለን፡፡ እዚህ ጋር ቡስኬትስ የያዘውን ኳስ ቢቀማ ባርሴሎናዎች ከእነርሱ ሳጥን አቅራቢያ ለሚጀመር የማጥቃት ሒደት በቂ የተጫዋች ቁጥር ስለማይኖራቸው ከባድ አደጋ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡
በሁለተኛው ምስል ቡስኬትስ ጫናን በከፍተኛ ደረጃ የሚቋቋም ተጫዋች በመሆኑ ባርሴሎናዎች የቢልባዎን “High-Press” ተቋቁመው ሲያልፉ እናያለን፡፡ ኢቫን ራኪቲች ኳስን ከቡስኬትስ ከተቀበለ በኋላ ሊሮጥበት የሚችለውን የቦታ ስፋት እንመልከት፡፡ በራሳቸው የሜዳ ክልል ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸው ከነበረበት ሁኔታ በመውጣት ባርሴሎናዎች አሁን 6-ለ-6 በሆነ ተመጣጣኝ የተጫዋቾች እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገኙ ችለዋል፡፡ (ዳኒ አልቬስ ማጥቃትን ለማገዝ በቀኝ በኩል ወደፊት መጠጋቱን ልብ ይሏል፡፡)
ዳኒ አልቬስ በመስመር በኩል የማጥቃት ሒደቱን ይቀላቀላል፡፡ ፔድሮም በሌላኛው መስመር እንዲሁ ያጠቃል፡፡ ኤኒየሽታ ደግሞ የኳስ ቅብብል ቢደረግለት ሰፋ ያለ ክፍት ቦታ ይዞ ሲጠብቅ እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪም በቀኝ በኩል በፊት ለፊት መስመሩን ታክኮ ሜሲና አልቬስ የተጋጣሚያቸውን ተጫዋች ባሌንዚያጋን ለብቻው በመነጠል የ2-ለ-1 ብልጫ ይወስዱበታል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ እውን የሆነው በሰርጂዮ ቡስኬትስ ከፍተኛ ጫናን የመቋቋም ክህሎት ነው፡፡
የማጥቃት አደረጃጀት
በከፍተኛ ደረጃ ጫናን የሚቋቋሙ ተጫዋቾች ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክልል ለመድረስ የራሳቸውን ብቃት ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች አብዛኛውን ጊዜ ለተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ቀርበው ሲጫወቱ የሚገባቸውን አድናቆት ያገኛሉ፡፡ ተጫዋቾቹ ኳስ የመያዝ ብቃታቸው እንዲሁም የባላጋራ ቡድን ተጫዋቾች የመከላከል አደረጃጀታቸውን አላልተው ወደ እነርሱ እንዲቀርቡ ያደርጓቸዋል፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው እንቅስቃሴ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንደ ሜሲ፣ ሃዛርድ እና ኔይማር ያሉ ተጫዋቾች ወደ አዕምሮአችን ይመጣሉ፡፡
ከላይ በምስሉ ሜሲ ከቢልባዎ ተከላካይ ፊት ኳስን በመቀበል ወደ ፊት ሲገፋ ይታያል፡፡
በዚህኛው ምስል ሙሉ የቢልባዎ ተከላካዮች ሊዮኔል ሜሲ ላይ እንዴት ትኩረት እንደሚያደርጉ እና እርሱን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ለመክተት ወደ እርሱ እየተጠጉ እንደሆነ እናያለን፡፡
የሜሲ ኳስን ይዞ ወደፊት መግፋት የቢልባዎን የመከላከል መዋቅር ሚዛን እንዲያጣ እያደረገው ይገኛል፡፡ ይህም ካፈገፈገ ቦታ ወደ ፊት ለሚመጡ ተጫዋቾች መሃለኛው ክፍል ክፍት እየሆነ ይሄዳል፡፡
የመጨረሻዎቹ ሁለት ምስሎች ደግሞ ሜሲ ኳስን እስከ መጨረሻው በመያዙ የቢልባዎ አጠቃላይ የሜዳ ውስጥ ተከላካዮች ትኩረት ማግኘቱን ያሳያል፡፡ ይህም ቡስኬትስ በተፈጠረው ክፍተት በመጠቀም ፔድሮ ለሚያስቆጥረው ግብ ጥሩ ቅብብል እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ሽግግር
የመልሶ-መጫን ታክቲክ በትልልቅ ቡድኖች ጥቅም ላይ መዋሉ እየጨመረ በመምጣቱ ቡድኖች ኳስን ከተጋጣሚያው እግር ሥር እንደነጠቁ የሚመጣውን የ”ፕረሲንግ” ሒደት የሚያበርዱ ተጫዋቾችን መያዝ አስፈላጊነቱ ከፍ እያለ ነው፡፡ ያለ እነዚህ ተጫዋቾች ቡድኖች በራሳቸው ሜዳ ብቻ ተገድበው በመቅረት አስከፍተው ለመውጣትና ጥራት ያለው የማጥቃት ሒደት በቋሚነት ለማድረግ ይቸገራሉ፡፡
የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ