ከመዲናችን አዲስ አበባ 580 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው ባህር ዳር ከተማ ተወልዶ ያደገው የዛሬው የተስፈኞች ገፅ እንግዳች ከኳስ ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ የተለየ ነው። በተለይ በሰፈሩ የሚገኝ የመጫወቻ ሜዳ እና ኳስ የሚታዩባቸው አዳራሾች ላይ ውሎ እንደነበረ ያወሳል። የቀለም ትምህርቱን እየገፋ በሚገኝበት ወቅትም የሚማርበትን ግዮን ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤትን ወክሎ ለትምህርት ቤት ውድድሮች ሲጫወት አሠልጣኝ አምሳሉ እስመለዓለም ዕይታ ውስጥ ገብቶ ወደ ፕሮጀክት እንዲገባ ሆነ። በአሠልጣኝ አምሳሉ የሚመራው ተስፋ ኮከብ ፕሮጀክት ውስጥም ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች የእድሜ እርከን ስብስብ ውስጥ ተካቶ ራሱን አጎለበተ። ከዛም ይህ የተስፋ ኮከብ የፕሮጀክት ቡድን በባህር ዳር የውስጥ ውድድሮች ላይ ሲሳተፍ ተጫዋቹ ገና በለጋ እድሜው በስብስቡ ተካቶ ራሱን በተሻለ ደረጃ የሚያሳይበትን የመጫወቻ ጊዜ አገኘ። ነገርግን ገና አንድ ዓመት በውስጥ ውድድሩ ላይ እየተጫወተ ቡድኑ ተስፋ ኮከብ የመፍረስ አደጋ አጋጥሞት ከክለቡ እንዲወጣ ሆነ።
አንዳንድ ጊዜ መጥፎ አጋጣሚዎች ለበጎ ናቸው እና የዛሬው እንግዳችን ፕሮጀክቱ እንደፈረሰ የከተማውን ዋና ቡድን በተስፋ ደረጃ የሚቀላቀልበትን ያልታሰበ እድል አገኘ። በተለይ በፕሮጀክት ቡድን ያሰለጠነው አሠልጣኝ አምሳሉ የባህር ዳርን ቢ ቡድን እንዲመራ ስለተደረገ የተጫዋቹ ጉዞ የሰመረ ሆነ። ነገርግን ተጫዋቹ ወደ ባህር ዳር ቢመጣም የመጫወት እድል እንዳሰበው አላገኘም ነበር። በዋናው ቡድን በቢጫ ቴሴራ ትገባለህ ተብሎ ቢነገረውም የተገባለት ቃል ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ። በዚህ ሰዓት እዚሁ ቡድን ውስጥ እያለ ሌሎች አማራጮችን ማየት ጀመረ። በዚህም ተስፋ ሳይቆርጥ በዋናነት ከባህር ዳር ከተማ ቡድን ጋር ልምምድ እየሰራ ለመጫወት ደግሞ ወደ ግሽ አባይ ቡድን እየሄደ በሁለት ሳምንት አንዴ በአማራ ሊግ ተጫውቶ ይመለስ ጀመር። ይህንንም ያደረገው በጊዜው በግሽ ዓባይ አሠልጣኝ ሰለሞን አማካኝነት ጥሪ ቀርቦለት እና የጨዋታ ልምድ ለማካበት እንደሆነ ይናገራል።
ገና በለጋ እድሜው በተስፋ ቡድን ተይዞ የኮብልስቶን ሥራን ይሠራ የነበረው የባህር ዳር ከተማው ተስፈኛ ኃይለየሱስ ይታየው የዛሬው የተስፈኞች ገፅ እንግዳችን ነው።
“በባህር ዳር ከተማ ቡድን ውስጥ ተስፋ ተብዬ ብያዝም ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች በጊዜው ነበሩ። በተለይ በቢጫ ቴሴራ ዋናው ቡድን ትጫወታላችሁ ተብለን ለበርካታ ጊዜያት በትዕግስት ጠብቀናል። ግን ቶሎ አልተሰራልንም ነበር። እንደውም ከእኔ ጋር የነበሩ አንዳንድ ተጫዋቾች ተስፋ ቆርጠው ኳሱን አቁመውታል ። እኔ ግን ምንም ሳይበግረኝ እስከመጨረሻው የሚሆነውን ልይ ብዬ ታገስኩ። ከቡድኑ ጋር ከ2010 ጀምሮ ልምምድ ስሰራ ነበር። ግን ከዛ ጊዜ ጀምሮ ያለ ደሞዝ ነበር ከቡድኑ ጋር አብሬ የነበርኩት። ይህ ራሱ ትልቅ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነበር። ግን አሁንም ለመቀጠል አልሰነፍኩም። ከዛ እኔ በጊዜው ቤተሰብም ስለማስተዳድር ኳሱን ሳልተወው ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር በመሆን የኮብልስቶን ስራ ጀመርን። እንዳልኩት በኳሱ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ ቆርጬ ሳይሆን ይህንን ስራ የጀመርኩት እናቴን ለማገዝ ነበር። እናቴ ብዙ ነገር ስላደረገችልኝ እሷን ለማስደሰት ነው በእግርኳሱ ደሞዝ ሳይከፈለኝ ሲቀር ይህንን የኮብልስቶን ሥራ የጀመርኩት።
በግሽ ዓባይ ዓምና የመጫወቱን እድል ካገኘ በኋላ ዘንድሮ ወደ ባህር ዳር በሙሉ ጊዜ ግልጋሎት ለመስጠት የተመለሰው ኃይለእየሱስ እንዴት ወደ ዋናው ቡድን ሰብሮ እንደገባ እና የመጫወት እድል በተሰረዘው የውድድር ዘመን እንዳገኘ ያጫውተናል።
“ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን እንድገባ የሆነው በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ አማካኝነት ነው። የሚገርመው የቢ ቡድን ተብሎ የተመሠረተው ቡድን በመበተኑ እኔ ብቻ ነበርኩ ተስፋ ሳልቆርጥ የቆየሁት። አሠልጣኙም ታዳጊዎች ላይ መስራት ስለሚፈልገም በቀላሉ ወደ ዋናው ቡድን እንድገባ አደረገኝ። ፋሲል ከመምጣቱ በፊት ደግሞ ግሽ አባይ ያሰለጠነኝ አሠልጣኝ ሰለሞን በክለቡ የቦርድ አባል ሆኖ ስለመጣ ስለ ብቃቴ ያሉትን ሰዎች አሳምኖልኛል።”
የእግርኳስ ሕይወቱን ሲጀምር በቀኝ መስመር ተከላካይነት የጀመረው ኃይሌ ወደ መሐል ገብቶም በተከላካይነት ተጫውቶ አሳልፏል። አንዳንድ ጨዋታዎች ላይም በመስመር ተጫዋችነት ግልጋሎት ሲሰጥ ታይቷል። እርግጥ እሱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ መጫወት ቢወድም ያለው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የመጫወት ብቃቱ ወደፊትም አዳብሮት መቀጠል እንደሚሻ ይናገራል።
ከወራት በፊትም ከቡድኑ ባህር ዳር ከተማ ጋር ለተጨማሪ 2 ዓመታት የሚያቆየውን ውል የተፈራረመው ተጫዋቹ ወደፊት ማሳካት ስለሚፈልገው ነገር በማንሳት ይቀጥላል።
“እኔ ከኳስ ውጪ ምንም የሚያዝናናኝ ነገር የለም። ወደፊት ደግሞ እየተዝናናው በተጫዋችነት ትልቅ ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በብሔራዊ ቡድን እና ክለቦች ደረጃ ብዙ ጊዜ ባህር ዳር ላይ ጨዋታዎች ተደርገዋል። እና በታዳጊነቴ ያየሁት ብሔራዊ ቡድን ላይ ወደፊት ተካትቼ ብጫወት እና ሃገሬን ባገለግል ደስተኛ ነኝ። ደግሞም ይህ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ። አሁንም ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። በቀጣይም የተሻሉ ነገሮችን አምጥቼ ህልሜን ለማሳካት እሞክራለሁ።”
በመጨረሻም ተጫዋቹ ወደ ትልቅ ደረጃ የሚያደርገውን ጉዞ ያስጀመረውን አሠልጣኝ አምሳሉን፣ የመጫወት እድል እንዲያገኝ ያደረገውን አሠልጣኝ ሰለሞን እና ብዙ ነገር ያበረከቱለትን የሰፈሩን ልጆች ከፈጣሪ በመቀጠል አመስግኖ ሃሳቡን አገባዷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!