ምስር ተከታታይ ድሉን ባስመዘገበበት ጨዋታ ሽመልስ በቀለ ጎል አስቆጥሯል

ከኮሮና ቫይረስ መቋረጥ በኃላ በተጀመረው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ብቃቱን በማሳየት ለቡድኑ መሻሻል ጥሩ አስተዋፅኦ እያደርገ የሚገኘው ሽመልስ በቀለ ተቀይሮ በመግባት ግብ አስቆጥሯል።

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ምስር ለል ማቃሳ ካይሮ ላይ ማስርን አስተናግዶ 3-0 ማሸነፍ ችሏል። ምስሮች በ16ኛው ደቂቃ በአሚር ማሬ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው እስከ ዘጠናኛው ደቂቃ አንድ ለባዶ ሲመሩ የቆዩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ በቀለ በ74ኛው ደቂቃ ፖል ቮአቪን ቀይሮ ወደ ሜዳ መግባት ችሏል። መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጨረማሪ ደቂቃ ላይም ከመሐመድ ኢብራሂም የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ይህች ጎል ለሽመልስ ከኮሮናው ዕረፍት መልስ ውድድሮች ከተጀመሩ በኋላ ሁለተኛው ሆና ተመዝግባለች። ባለሜዳዎቹ ከሽመልስ በቀለ ጎል ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ቆይታ በኋላ በሪኮ አማካኝነት አንድ ግብ አስቆጥረዋል።

በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ድል ያስመዘገበው ምስር ከአስቸጋሪ የውድድር ዘመን ጉዞ በኋላ እያገገመ ሲሆን ካለፉት ዘጠኝ ድሎች እና አንድ ድል በማስመዝገብ ነጥቡን 36 በማድረስ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። በቀጣይ ሳምንትም የሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ ከተቃረበው ታላቁ አል አህሊ ጋር ይጫወታሉ።

በተያያዘ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አጥቂ ዑመድ ኡኩሪ ከጉዳት ከተመለሰ ወዲህ ጨዋታዎች እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ቡድኑ አስዋን ትናንት ታንታን 4-0 ባሸነፈበት ጨዋታ በ68ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!