በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተዋቀሩ ኮሚቴዎች እያደረገ ያለው የሜዳዎች እና መሠረተ ልማቶች ግምገማ ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳስ ውድድሮች ለማስጀመር ቅድመ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ውድድሮች ከኮሮና ቫይረስ የፀዱ እንዲሆኑ ሦስት ኮሚቴዎችን አዋቅሮ የመጫወቻ እና መለማመጃ ሜዳዎችን፣ የስታዲየም መሠረተ ልማቶች፣ ከሥጋት የፀዱ የመልበሻ ክፍሎች፣ ማረፊያ ካምፕ እና ሆቴሎች እንዲሁም በቂ የጤና ተቋማት እና ባለሞያዎች መኖራቸውን ከሰሞኑ እያስገመገመ ይገኛል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ኮሚቴዎቹ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ቦታዎች በማምራት በተለይ በዋናነት ስታዲየሞችን እየገመገሙና ግብዓት እየሰበሰቡ ሲሆን የድሬዳዋ፣ ሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ፣ የባህርዳር፣ ሶዶ እና ባቱ ሜዳዎችን መመልከታቸው ይታወሳል፡፡
ኮሚቴዎቹ ቅዳሜ እና ዕሁድ በተመሳሳይ ጉብኝታቸውን ቀጥለው የነቀምት፣ ጅማ፣ ደብረማርቆስ እና አዳማ ስታዲየሞች የተገመገሙ ሲሆን በከተማ ውስጥ ያሉ አስፈላጊ የተባሉ ነገሮች ታይተዋል፡፡ ጳጉሜ 4 ፍፃሜውን የሚያገኘው ይህ ግምገማ በቀሪ ቀናት ተጨማሪ ቦታዎችን ተመልክቶ ውጤቱን ለፌዴሬሽኑ ካሳወቀ በኃላ መስከረም አጋማሽ ብቁሆኑ ሜዳዎች ይፋ እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡ እንደ መቐለ፣ ወልዲያ እና መሰል ሜዳዎችም ከዛሬ ጀምሮ የጉብኝት አካል የሚሆኑ ሲሆን ትናንት የወንጂን ስታዲየም ለመመልከት አንደኛው ኮሚቴ ለማምራት ወደ ስፍራው ያቀኑ ቢሆንም መንገዱ ምቹ ባለመሆኑ ሊመለሱ እንደቻሉ ሰምተናል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!