መስፍን ታፈሰ በኢኳቶርያል ጊኒው ክለብ ልምምድ ጀምሯል

“በተቻለኝ መጠን ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችም ወደ ውጭ ለማዘዋወር ጥረት እያደረግኩ ነው” ሳምሶን ነስሮ (የተጫዋቾች ወኪል)

ለሙከራ ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ ያመራው ወጣቱ መስፍን ታፈሰ ከፉትሮ ኪንግስ ጋር ልምምድ ጀምሯል።

ከቀናት በፊት ወደ ኢኳቶርያል ጊኒው ፉትሮ ኪንግስ ለሙከራ ያመራው የሀዋሳ ከተማው መስፍን ታፈሰ በትናንትናው ዕለት በማላቦ ስታዲየም የመጀመርያው ልምምድ ሲያደርግ ዛሬ ረፋድም በሉባ ስቴድየም ሁለተኛ ልምምዱን ሰርቷል።

ከሳምንታት በፊት ኢኳቶርያል ጊንያዊው ግብ ጠባቂ ፍሊፖ ኦቮኖን ወደ ፉትሮ ኪንግስ በማዘዋወር ከክለቡ ጋር መልካም ግንኙነት የጀመረው የተጫወቾች ወኪሉ ሳምሶን ነስሮ የተጫዋቹ ማረፍያ በቅርቡ እንደሚታወቅም ገልፆልናል።

” የመስፍን ዝውውር ጨምሮ የስድስት ተጫዋቾች ዝውውር ለመጨረስ ነው የመጣሁት። ከዛ ቀጥሎ ወደ ካሜሩን አመራለሁ። በተቻለኝ መጠን ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችም ወደ ውጭ ለማዘዋወር ጥረት እያደረግኩ ነው። ከመስፍን ውጭ የተፈለጉ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ነበሩ። ግን ከክለቦቻቸው ጋር ውል ስላላቸው ትንሽ ነገሩ አክብዶታል። እንደዛም ሆኖ ግን ወጣት ተጫዋቾች ለማዘዋወት ጥረቶች እያደረግኩ ነው።

“መስፍን በመጀመርያው ቀን ቀለል ያለ የአካል ብቃት ልምምድ አድርጓል። ከፉትሮ ኪንግስ በተጨማሪም ወደ ሌላ የሚሄድበት ዕድል አለ። ከቀናት በኃላ በስፔን ክለቦች የተጫወተ የክለብ ባለቤት እዚ ማላቦ መጥቶ መስፍን ታፈሰን ጨምሮ ሌሎች አምስት ተጫዋቾች አይቶ ወደ ስፔን ይወስዳል እሱም እንደ ሁለተኛ ዕድል ይዘነዋል እስካሁን ባለው ሁኔታ።” ብሏል።

ከቀድሞ የመቐለ 70 እንደርታ ግብ ጠባቂ ፍሊፕ ኦቮኖ ጋር የሚገኘው መስፍን ታፈሰ እንደ ወኪሉ ገለፃ ከሆነ በኢኳቶርያል ጊኒው ፉትሮ ኪንግስ እና በአንድ የስፔን ክለብ የመቀላቀል ዕድል አለው።

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፉት እና ስብስባቸው በአዲስ መልክ እያደራጁ የሚገኙት ፉትሮ ኪንግሶች ከዚህ ቀደም የስሑል ሽረዎቹ አዳም ማሳላቺ እና ዓብዱለጢፍ መሐመድን በክለባቸው ስር እንደነበሩ ይታወሳል።

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!