ስለ ካሊድ መሐመድ ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

በግራ እግራቸው ከሚጫወቱ ባለ ብዙ ክህሎት ተጫዋቾች መካከል የሚመደበው እና አጭር በሆነው የእግርኳስ ሕይወቱ የማይረሱ ስኬታማ ዓመታትን ያሳለፈው የዘጠናዎቹ ኮከብ ካሊድ መሐመድ (ጩቤው) ማነው?

ነፍሱን ይማረውና ታላቁ የእግርኳስ ሰው ጋሽ ሥዩም አባት በሳምንቱ መጨረሻ ወደ አወልያ ትምህርት ቤት በመጓዝ የሚካሄደውን ጨዋታ ይከታተል ነበር። ጋሽ ሥዩም የሚሄድበት ምክንያቱ ደግሞ አንድ ቀልቡን የሳበው ፈጣን እና ባለክህሎት ልጅ በግራ እግሩ በሚያደርገው የተለየ እንቅስቃሴ ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች እንደሚሆን በማሰብ ነበር። በታዳጊ ተጫዋች እንቅስቃሴ ብቻ ያልተገደበው የጋሽ ሥዩም እክትትል በመጨረሻም በ1988 ቡና “ሲ” ቡድን እንዲገባ አድርጎታል። በዚህ መንገድ የጀመረው የዚህ ታዳጊ የእግርኳስ ጉዞ በ1990 በኢትዮጵያ ቡናን ዋና ዋናው ቡድን እንዲያድግ አስችሎታል።

ይህ ባለ ታሪክ ድንቁ አማካይ ካሊድ መሐመድ ነው። ተወልዶ ያደገው የበርካታ እግርኳሰኞች መፍለቂያ በሆነው ስሙ እንጂ ሜዳው በአሁን ሰዓት ደብዛው የጠፋው መሳለሚያ አካባቢ የሚገኘው ኳስ ሜዳ ሠፈር ነው። ዕድገቱ ፈጣን የሆነውና በፍጥነት የስፖርት ቤተሰቡ ዐይን ውስጥ የገባው ካሊድ ፋጣን፣ ፈጣሪ፣ የመስመር ተሻጋሪ ኳሶቹ ጥሩ የነበሩ፣ ለቡድን አጋሮቹ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ የሚያቀብል እና በርካታ ጎሎችን የማስቆጠርበት አቅሙ የእርሱ የተጫዋችነት ዘመኑ መገለጫዎቹ ነበሩ። በተለይ ባማረው ግራ እግሩ ከመስመር የሚያሻግራቸው ኳሶቹ እጅግ የተሳኩ ከመሆናቸው የተነሳ ” ካሊድ ከመስመር የሚጥላቸው ኳሶች ወይ ታገባዋለህ ወይም ካላገባኸው ያሰድብሀል” በማለት ሁሉም ተጫዋቾች ይነገሩለት ነበር።

ለስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና በቆየባቸው ጊዜያት የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ሦስት ጊዜ ከማንሳቱ በላይ ኢትዮጵያ ቡና የ1990 የግብፁ ኃያል ክለብ አል አህሊን ከውድድር ውጪ ባደረገበት ገድል ውስጥ የቡድኑ አባል ነበር። ነፃ ሆኖ የሚሰጠውን ሚና መተግበር የሚፈልገው ካሊድ በ1995 አሰልጣኝ ካሳዬ ኢትዮጵያ ቡናን ለማሰልጠን በተረከበበት ዓመት ካሊድ ከአሰልጣኙ የጨዋታ ፍልስፍና ውጪ አብዝቶ በራሱ መንገድ ከመስመር ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀሙ ያልተደሰተው ካሳዬ ተሻጋሪ ኳሶቹን ለማስቀረት ባልተለመደ ሁኔታ የቀኝ መስመር አጥቂው ደብሮም ሀጎስን ወደ ግራ ካሊድን ደግሞ ወደ ቀኝ ወስዶ ማጫወት በመጀመሩ ብዙም ባለመደው ቦታ መሰለፉ ያላስደሰተው ካሊድ በወቅቱ ለንባብ በሚቀርቡ የህትመት ሚዲያዎች በግልፅ የአሰልጣኝ ካሳዬ የሚና ለውጥ እንደማይቀበለው እና ተጫዋች ተገድቦ መጫወት የለበትም በሚል የተፈጠረው እሰጣ አገባ በወቅቱ በስፖርቱ ባለሙያዎች እና ደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል።

የቀድሞ ድንቅ አማካይ አሸናፊ ግርማ በተጫዋችነት ዘመኑ እንደ ካሊድ መሐመድ ልዩ ችሎታ ያለው ተጫዋች እንዳልተመለከተ በራሱ አንደበት ሲናገር “ካሊድ ምርጥ ከሚባሉት ግራኝ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ኳስ ሲጫወት ጎበዝ ነው። ከቆመ ኳስም ጎል ያገባል። እንዲሁም ከመስመር እየተነሳ የሚያስቆጥራቸው ጎሎች ብዙ ናቸው። አጨራረሱ የተለየ ነው። ለአጥቂዎችም ያለቀላቸው ኳሶችን ያቀብላል። አንድ ለአንድ አብዶ ሰርቶ ያልፋል ያለ ዕድሜው ከሜዳ በጉዳት የራቀ በጣም የማደንቀውተጫዋች ነው።” ይላል።

ከዚያ ጊዜ በኋላ ብዙም ያልቆየው ካሊድ በአጨዋወቱ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እንደተወደደ በ1996 ወደ ባንኮች (ኋላ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ሊያመራ ችሏል። በባንኮች እየተጫወተ ሳለ ለጨዋታ መቐለ ከተማ ላይ ሳይታሰብ በድንገት ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት በአሳዛኝ ሁኔታ ከእግርኳስ ዓለም ተሰናብቷል። በተደጋጋሚ በሀገር ውስጥ የተለያዩ ህክምናዎችን በማድረግ ወደ ሜዳ ለመመለስ ሞክሯል። ከጉዳቱ አገግሞ ቢመለስም በመጀመሪያው ልምምድ ላይ ህመሙ አገርሽቶ ያሰበው ሳይሆን ያላሰበው ነገር ተፈጥሮ ብዙም ሳይጠገብ በአሳዛኝ ሁኔታ ከእግርኳስ ዓለም በ1998 ተሰናብቷል። በንግድ ባንክ ቆይታው ግን የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቷል።

በብሔራዊ ቡድን አገልግሎቱም በሁሉም ዕርከኖች የወቅቱ አሰልጣኞች የመጀመርያ ተመራጭ በመሆን ያገለገለ ሲሆን በ1994 ከሀገር ውጪ በተገኘው የመጀመርያው የሴካፋ ዋንጫ ድል ውስጥ የቡድኑ አባል ነበር። ካሊድን በተጫዋችነት ዘመኑ በንግድ ባንክ እየተጫወተ፣ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ም/አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት አብሮት የነበረው ዕድሉ ደረጄ (በዴክሶ) ስለ ካሊድ እንዲህ ይናገራል። ” ካሊድ በጣም አዕምሮውን የሚጠቀም፣ የት ቦታ መሆን እንደሚገባው ጠንቅቆ የሚያውቅ በተለይ ጎል ለማስቆጠር የሚመርጠው አቋቋም ልዩ የነበረ ነው። የኳሷን ብልት የሚያውቅ፣ ጣጣቸው ያለቁ ኳሶችን በትክክል ከመስመር የሚያሻግር ተጫዋች ነበር። አሰልጣኝ ሆኖ ከጀርባ ሆኖ ፊት ለፊት ሳይታይ ቡድን የሚመራ በሳል ሰው ነው። ብዙዎች እርሱ ምክትላቸው እንዲሆን የሚፈልጉት ሰው ነው። ተጫዋቾችን የሚቆጣጠርበት መንገድ ደስ ይላል። በአጠቃላይ ከጀርባ ሆኖ ብዙ ነገር የሚረዳ እአሰልጣኝም ነው። አሰልጣኝ ውበቱ ቡና እንደመጣ እስኪላመድ ድረስ ብዙ ነገር አግዞት ነር። ቡና 2003 ላይ ቻምፒዮን የሆነው በካሊድ ከፍተኛ አስተዋፆኦም ነው ማለት ይቻላል።” ይላል።

በጣም ቀልድ አዋቂ እንደሆነ የሚነገርለት ካሊድ ወደ ሜዳ ለመመለስ የነበረው ተስፋ ሳይሳካ ቢቀርም ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ምርጫ በ2002 ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ቡና ም/አሰልጣኝ በመሆን የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጀመረ። ለአንድ ዓመት ከገብረመድህን፣ ከ2003–04 ከውበቱ አባተ፣ በ2005 ግማሽ ድረስ ከፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር ከሰራ በኃላ ፀጋዬ ለትምህርት ወደ ሀንጋሪ በማቅናቱ ቀሪውን አጋማሽ የውድድር ዘመን በጊዚያዊ ዋና አሰልጣኝነት ተረክቦ ኢትዮጵያ ቡናን ከነበረበት ወራጅ ቀጠና አውጥቶ ደረጃውን አሻሽሎ እንዲጨርስ አስችሎታል።
በመቀጠል የአሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ እና ሳምሶን አየለ ምክትል በመሆን በዳሽን ቢራ እየሰራ በሁለት አጋጣሚ ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ አሰልጣኞቹ ሲሰናበቱ ሁለት ጊዜ ቡድኑን ተረክቦ ከነበረበት ወራጅ ቀጠና በማውጣት ለሦስተኛ ጊዜ ዋና አሰልጣኝ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሠፋን ሲያመጡ ተስፋ ቆርጦ ላለማሰልጠን ወስኖ ከዳሽን ቆይታው የማይረሳ የልደቱን አከባበር ትዝታ ብቻ ይዞ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል። በሰዎች ተደጋጋሚ ጉትጎታ በድጋሚ በ2010 የኢትዮጵያ መድን የታዳጊ ቡድን እየሰራ ከአንድ ዓመት በኋላ የቴክኒክ ዳይሬክተርነት ኃላፊነትን ተረክቦ መስራቱም ይታወቃል። 2011 ግማሽ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀላባ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ቆይታ አድርጎ በስምምነት ከተለያየ በኋላ በአሁን ሰዓት ክለብ አልባ ሆኖ ይገኛል።

በዛሬው የዘጠናዎቹ ከዋክብት አምዳችን ከዚህ ድንቅ ተጫዋች የአስር ዓመት የእግርኳስ ህይወት አስመልክቶ ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።

“ብዙ መጫወት እየቻልኩ በጊዜ እግርኳስን ማቆሜ ይቆጨኛል። እንዲያውም እግርኳስ በገባኝ ወቅት ነው ያቆምኩት፤ ይህ በጣም የሚቆጨኝ ነው። ሌላው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተጫዋችነት ዘመኔ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አለማንሳቴ በጣም የሚቆጨኝ ነው። እንደማንኛውም ተጫዋች ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ ብታሳካ ደስ ይልሀል። ያው በኃላ በ2003 በምክትል አሰልጣኝነት ዋንጫ በማንሳቴ ቢካካስልኝም።

“አስቂኝ ገጠመኞች ብዙ አሉ። በብሔራዊ ጨዋታ በአንድ ወቀት ኬንያ ሄደናል። ለጨዋታ ከሆቴል ወደ ስታዲየም በሰርቪስ መኪና እየሄድን ነው። አሁን ስሙን የማልነግርህ ተጫዋች ከኃላ ነው የተቀመጠው በመኪና ውስጥ የተከፈተውን ሙዚቃ ተመችቶት ድምፁ ከፍ እንዲል (ድምፁ እንዲጨመር) ይፈልጋል። በአጋጣሚ ሆኖ ሹፌሩ ኬንያዊ ስለነበር በምንም ቋንቋ ያውራው እንግሊዘኛ አያውቅም። ምን ቢል ጥሩ ነው ድምፅ ጨምርልኝ ለማለት ፈልጎ ” ኤ ድራይቨር” ይለዋል ሹፌሩም ጥሪውን ሰምቶ ዞር ሲል” ስፒድ ፣ ስፒድ አለ” ድምፅ ስጥልኝ ለማለት ፈልጎ ነው። በጣም እየሳቀ… ሹፌሩም በጣም ንዳ ያለው መስሎት መኪናውን ሲያፈጥነው ኧረ ሙዚቃውን ድምፅ ስጠው ለማለት ነው። “ቮሊዩም ፣ ቮሊዩም” ሲለው ሹፌሩ መኪናውን መንዳት አቁሞ የሳቀበትን ሁኔታ መቼም የማረሳው አጋጣሚ ነው። ሌላው አንድ ቅጣት ምት አገኘው እና ለመምታት ተዘጋጅቼ ስመታው ኳሱ ከጎሉ በላይ በጣም ከፍ ብሎ ወደ ውጪ ይወጣል። ታዲያ አንድ ተጫዋች ምን ቢለኝ ጥሩ ነው። ካሊዴ.. አቤት አልኩት ” ጎሉ ቢያዛጋ እንኳን አይገባም!” አለኝ። በጣም እየሳቀ… ይሄን ያለኝ ብሩክ እስጢፋኖስ ነው።

“በህይወቴ በሥልጠናው ላይ ተስፋ የቆረጥኩበት የዳሽን ቢራ አሰልጣኝ በሆንኩበት ዘመን ነው። ስሄድ ፕሪምየር ሊጉን በደንብ የሚያውቅ ጠንካራ አሰልጣኝ ያስፈልጋል ተብዬ ነው ከመኮንን ጋር አብሬ እንድሰራ የተቀጠርኩት። እሺ ብዬ እየሰራው መኮንንም ብዙም አልተሳካለትም። ወዲያውን ለኔ በዋና አሰልጣኝነት ቡድኑን እንዳሰለጥን ሠጡኝ እኔም ላለመውረድ የሚጫወተውን ቡድን እንዳይወርድ አድርጌ በቀጣይ ዓመት ቡድኑን እንዳሰለጥን ይሰጡኛል ብዬ ስጠብቅ ‘አንተ ወጣት አሰልጣኝ ስለሆንክ የዕድሜህም ገና ነው’ ብለው ከሳምሶን አየለ ጋር እንድሰራ ነገሩኝ። እሺ ብዬ አብሬ መስራት ጀመርኩ። ከሳምሶን ጋር እየሰራው እርሱም መዝለቅ አልቻለም ውጤት ሲጠፋ ከቡድኑ ተሰናበተ። አመራሮቹ ‘መጀመርያም ዕምነቱ ነበረን። ለአንተ መስጠት ነበረብን ግድ የለም አሁንም ቡድኑን እንደምታተርፍ ዕምነቱ ስላለን ቀጥል’ ብለው ይቅርታ ጠይቀውኝ ሰጡኝ። ዳሽን ከፍተኛ አደጋ ላይ ነበር። እንደገና እንዳይወርድ አድርኩት። እየሳቀ… ቀጣይ 2008 ላይ ለኔ ሙሉ ለሙሉ ይሰጡኛል ብዬ ስጠብቅ አሰልጣኝ ታረቀኝን (ዳኜ) አምጥተው ሾሙ። ‘አይ ከዚህ በኃላ አልሰራም’ ብዬ ጥዬ መጥቻለው። ሁሌም የምናገረው ነው። የሚፈለገው ገንዘብ የሚቀበል አሰልጣኝ ነው። አመራሩም በዚህ የሚነካካ እና ተጠቃሚ መሆን የሚፈልግ ነው። ለዚህም የሚመች ሰው ነበር የሚፈልጉት። በቃ እኔ በግልፅ አመራሮቹን ‘እናንተ የምትፈልጉት የሚመች ሰው ስለሆነ ተጠራጥሮ ሥራ እኔ አይመቸኝም። እኔ ቦርጭ ስሌለኝ ነው’ ብዬ ወጣው። በወቅቱም ዳኜ ከሀዋሳ የተባረረበት ምክንያት ከተጫዋቾች ጋር የገንዘብ ንክኪ በሚል ስለነበር። እኔም ይሄን እያወቅኩ ከእርሱ ጋር አልሰራም። ደግሞ እንደነገርኳቸው ታያላቹ ይህ ቡድን ይወርዳል ፣ ደግሞም ይፈርሳል ብዬ ነበር። በዚያኑ ዓመት ዳሽን ቢራ ላይመለስ ወርዶ እስከ መፍረስ ደርሷል። እንግዲህ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ነው እግርኳሱ እየሞተ የሚሄደው። እግርኳሱ በሥርዓት የሚመራ ቢሆን ኖሮ እንዲህ አይሆንም ነበር። እግርኳስን በእግርኳሳዊ መንገድ ብቻ የማትመራው ከሆነ ነገም ሌሎች ክለቦች ላለመፍረሳቸው ምንም ዋስትና የላቸውም።

“በጣም ተስፋ ከመቁረጤ የተነሳ ወደ አሰልጣኝነቱ ዳግመኛ ላለመመለስ ወስኜ በሚዲያ ‘በቃኝ ከዚህ በኃላ በእግርኳሱ እንዲህ ያሉ ነገሮች የማይስተካከሉ ከሆነ ዳግመኛ አሰልጣኝ አልሆንም። በቃኝ ታዳጊ ላይ እሰራለው’ ብዬ ወስኜ ወደ ንግዱ ዓለም ገብቼ ነበር። ሆኖም ብዙ ሰዎች ‘ሙያውን እየወደድከው ለምን ? ‘ እያሉ ሲገፋፉኝ በድጋሚ ወደ ማሰልጠኑ መጥቼ የኢትዮጵያ መድን የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ ሆንኩ። በኋላም ያለኝን አቅም ተረድተው እኔን ወደ ቡድን የማስጠጋት ፍላጎት ስለነበራቸው የክለቡ ቴክኒክ ዳሬክተር በመሆን እያገለገልኩ ያው ብዙም በዚህ ኃላፊነት መቀጠል ስላልፈለኩ ከመድን ጋር በስምምነት ተለያይቼ በመሐል ሀላባ ከተማ ጥሪ ሲያደርጉልኝ ዋና አሰልጣኝ መሆን ስለምፈልግ ወደዛ ሄጄ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሳገለግል ቆይቻለው። ስረከበው ቡድኑ በጣም ዝቅተኛ ነጥብ ነበረው። ቡድኑን ከመውረድ ስጋት አውጥቼ በአንዳንድ ነገሮች ምክንያት በስምምነት ተለያይተን አሁን ምንም ስራ ላይ አይደለሁም። በመሐል ኮሮናም መጣ በቅርቡ ወደ አሰልጣኝነቴ መመለሴ አይቀርም።

“ጩቤ የሚለውን ቅፅል ስም የወጣልኝ ምክንያት እንደሚታወቀው እኔ ኳስ ተጋፍቼ አልቀማም ፤ ያው ቀጭን ስለሆንኩ እና ጉልበት ስሌሌለኝ። የማደርገው ኳሱን ከኃላህ እመጣና ወጋ አደርግና እቀማሀለው ወይም አጨናግፍብሀለው። በዚህ መልኩ ኳስ ወጋ አድርጌ በመንጠቄ እና ለቡድን አጋሮቼ ወጋ አድርጌ በማቀበሌ ‘ይሄ ጩቤ ነገር ነው ከኃላ ኳስ ወጋ እያደረገ ይነጥቀናል’ በማለት ጩቤ አሉኝ በዚህ ምክንያት እጠራበታለው።

“በኢትዮጵያ እግርኳስ ልደቱ የተከበረለት በእኛ ዘመን ብቸኛው አሰልጣኝ እኔ ሳልሆን አልቀርም። ዳሽን እያለው ተጫዋቾቹ ይመካከራሉ። ክፍሌ ተኝቼ እየሮጡ ይመጡና በሩን በጣም ይደበድቡታል። ደንግጬ ‘ምንድን ነው ? ምን ሆናችሁ ‘ ብዬ ስጠይቃቸው። ‘ኧረ ዓይናለም ኃይሌ እና አስራት መገርሳ እየተጣሉ ነው’ ሲሉኝ በጣም ደንግጬ ወደ ተጫዋቾቹ ካምፕ ስሄድ መብራቱን አጥፍተውት ስገባ አብርተው ‘ሰርፕራይዝ !’ ብለው ልደቴን አከበሩልኝ ። ይህ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኝ ከተጫዋቾቹ ጋር በመሆን ቡቹ የሚባል የአንባ ራስ ሆቴል ባለቤት ጋራ በመሆን አስተባብረው አከበሩልኝ።

“ከተጫዋቾች ጋር ያለኝ ግኑኝነት በተመለከተ እኔ በነገራችን ላይ በጣም ዲሞክራት ነኝ። ተጫዋች ላይ መስራት የምፈልገው አዕምሮ ላይ ነው። ተጫዋች እንዲፈራኝ ሳይሆን እንዲያከብረኝ ነው የምፈልገው። ተጫዋች ከፈራህ ነገሮችን የሚያደርገው ፈርቶህ ነው። ሲያከብርህ ግን ነገሮችን የሚያደርገው ፈልጎ ነው። ፈልጎ የሚያደርገው እና ፈርቶ የሚያደርገው ነገር በጣም ነው የሚለያየው። ይህ የኔ ፍልስፍና ነው። ተጫዋቾች ጋር ጥሩ የስራ ግኑኝነት ነው ያለኝ። ስራ ላይ ስራ ነው። መስመር አለው ልክ ወደ ሜዳ ስገባ የአሰልጣኝ አክት ነው የማደርገው። ከሜዳ ውጪ ግን ሰውኛ ነገሬን ማጣት አልፈልግም። ለምሳሌ እነ ጋርዲዮላ ስታያቸው ያው የነርሱ አዕምሮ ፣ (መሠረታቸው) ከፍ ያለ ቢሆንም ጋርዲዮላ ከተጫዋቾቹ ጋር ያለው ቅርርብ ደስ ይላል። እኛ ሀገር ይህ የማይሆነው ለምድን ነው? ስለዚህ ከተጫዋቾች ጋር ደስ የሚል ግንኝነት አለኝ። በዚህ ምክንያት እስከ ዛሬ ክፉ ነገር ያደረገኝ አልገጠመኝም። ተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆነ ከጨዋታ ውጪ ያሉ ተጫዋቾች የሚወዱኝ አስልጣኝ ነኝ። ሁሉንም በዕኩል ዓይን አያለው ፣ ተጫዋችን ከመቅጣት ይልቅ ማስተማር እወዳለው። የቅርቡ እንኳን የሀላባ ተጫዋቾችን እይዝ የነበረበትን መንገድ ከደጋፊዎችም መጠየቅ ትችላለህ።

“በ3–5–2 አጨዋወት ሂደት ውስጥ በመስመር ትሄዳለህ ተሻጋሪ ኳስ ትጥላለህ። እኔ የምጥላቸው ኳሶች ደግሞ የተሳኩ መሆናቸው አብረውኝ የተጫወቱ ይመሰክራሉ። እኔ ብዙ ጊዜ የለመድኩት ይህን አጨዋወት ነው። ካሳዬ ደግሞ በእርሱ ፍልሰረፍና ከማሻማት ይልቅ ተቀባብለህ ወደ ጎል እንድትገባ ነው የሚፈልገው። እኔ ደግሞ ከለመድኩት ነገር መውጣት አልቻልኩም። ይህ ተገቢ አይደለም በማለት እከራከር ነበር። ለምን ተጫዋች መገደብ የለበትም ብዬ ስለማምን ጭምር ነው። ለምን ትገድቡኛላችሁ ክሮስ ማድረግ ካለብኝ ላድርግ ፣ ተቀባብሎ መግባት ካለብኝ ላድርግ ለምን አንድ ሀሳብ ብቻ ይዤ ወደ ሜዳ አልገባም። እኔ ከመስመር እንደማላሻገር ካወቀ ያኛው ተከላካይ የትኛውን ነው ቀድሞ የሚዘጋብኝ ? የማቀብለበትን ቦታ ይዘጋብኛል። ስለዚህ እኔ ይህን ለመቀበል እቸገራለው። ለምንድን ነው የምትገድቡኝ ? አይገደብ ብዬ እከራከር ነበር። አሁን ዓለም ራሱ ሁለቱን አማራጭ እየተጠቀመ ነው። ካሳዬ ክሮስ ኳስ እያደረኩ ስላበዛሁበት ይሄን ለመቀነስ የቦታ ለውጥ አድርጎ ደብሮም ሀጎስን በግራ እኔን በቀኝ ወስዶ እንድጫወተ አደረገ። ይህ እኔን አልተመቸኝም እግርኳስን አዕምሮህ ነው የሚጫወተው። አዕምሮህ ተገድቦ ከገባህ ምቾት አይሰማህም። በጥሩ ሁኔታ ወደ ሜዳ ካልከባህ ደግሞ ሜዳ ውስጥ ችግር ይፈጠራል።

“በእኔ ዕምነት ውበት ያለው እግርኳስ እፈልጋለው። ውበት ባለው አጨዋወት ፈጣን በሆነ እቅንቅስቃሴ መጫወት እፈልጋለው። አሁን ክሎፕን ውሰደው የሊቨርፑል አጨዋወት ስትመለከተው ውበት ባለው ኳስ ተቀባብለህ በሚያምር ሁኔታ ግን በፈጣን የአጨዋወት እንቅስቃሴ ወደ ጎል መድረስ ነው። ዓለም ቀስ እያለ የምትጫወተውን አጨዋወት አይፈልገውም። ምክንያቱ ይህ አጨዋወት ለተቃራኒ ቡድን ይመቻል። ኳሶች መፍጠን አለባቸው በዛኑ ልክ አዕምሮህም መፍጠን አለበት። አንድ ኳስ ንኪኪ በጣም ይመቸኛል። ኳሶች ቶሎ ቶሎ እየተጫወትክ ማጥቃትን መሠረት ያደረገ አጨዋወት የኔ ፍልስፍና ነው።

“በኢትዮጵያ እግርኳስ በጣም መታሰብ ያለበት ጉዳይ የዳኝነት ነገር ነው። ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም የሚታወቅ ነገር ነው። በጣም ሥነ ምግባር ያላቸው ጥሩ ዳኞች ሊኖሩ ይችላሉ። በዛው ልክ ደግሞ ቡድን እየሸጡ የሚሄዱ ዳኞች አሉ። ሆን ተብሎ ይሄን የሚያደርጉ አሉ መታሰብ አለበት። በየክልሎች ያሉ የፀጥታ ችግሮችም መቀረፍ አለባቸው። ቡድን እና ቡድን ብቻ ነው ሊደገፍ የሚገባው። አንዳንድ ቦታዎች የኃይማኖት ያህል ፀቦች ታያለህ። እንዲሁም የዘር ችግሮች ትመለከታለህ ስለዚህ በደንብ ሊሰራበት ይገባል።

“ያሳደገን ኳስ ሜዳ እንዲህ መሆኑ በጣም ነው የሚያሳዝነነው። ያ ሜዳ እንዲህ ሆኖ መቅረቱ እና መጥፋቱ በዚህ መልኩ ትምህርት ቤት ተሰርቶበት ማየቱ ያሳምማል። ባለፈው ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር የሩጫ ቀኑን በማስመልከት ኳስ ሜዳ አከባቢ ተሰባስበን ነበር። ያንንም ያደረግንበት ምክንያት ኳስ ሜዳ እንዳይረሳ ለማስታወስ ጭምር ነው። ድሮ ኳስ ለመጫወት የምትሄድበት ቦታ አሁን ለህዝብ ትራንስፖርት ታክሲ ሰው መጫኛ እና ማውረጃ መጠርያ ስም ብቻ ሆኗል። ይህ ሊታሰብበት ይገባል። አንድ ጤናማ ዜጋ ለማፍራት የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ወሳኝነት አላቸው። አሁን ኳስ ሜዳ አካባቢ አንድም ሜዳ የለም። ይሄንን ሳስብ በጣም ነው የሚሰማኝ። ወደእዛ አካባቢ ወጣቱ ቁጭ ብሎ ጫት ሲቅም እና ሱሰኛ ሆኖ ነው የምታየው። ድሮ ደግሞ ሁሉም ቁምጣ እና ማልያ ለብሶ ነበር የምታየው ፤ አሁን ግን ይህ የለም። ይህ ችግር ኳስ ሜዳ ብቻ አይደለም በመላው አዲስ አበባ ያለ ችግር ነው። እንግዲህ ኳስ ሜዳ ስሙ አለ ስሙም እንዳይረሳ እንኳን እንጥራለን። ከከተማ አስተዳደር ጋር ተነጋግረናል። ትምህርት ቤቱ አጠገብ የሆነች አነስ ያለች ቦታ ተሰጥቷል። እስካሁን የለማ ነገር የለውም። በቀጣይ ተከታትለን ምን ደረሰ? ብለን እናያዋለን።

“በመጨረሻም ሁላችንም ተባብረን የኢትዮጵያ እግርኳስን ወደ ተሻለ ደረጃ እናድርስ የሚል ነገር አለኝ። ሁሌም ሌሎች ሌሎች ነገሮችን ከማሰብ እግርኳሱን ማሰብ ያስፈልጋል። ዓለም ላይ እግርኳስን ብራዚላዊያን ይወዳሉ እላለው። ቀጥሎ የኢትዮጵያ ህዝብ እግርኳስን ይወዳል ብዬ አምናለው። ግን በሚወደደው ልክ አይደለም ያለው። ብዙ ነገሮች ማድረግ እየቻልን በተለያዩ ነገሮች ነው ተጠምደን ያለነው። ደጋፊዎችም የዘጠና ደቂቃ ጨዋታውን ብቻ ሜዳ ውስጥ እናስብ። የአንድ ሀገር የአዳምና የሔዋን ልጆች ነን እና ሁላችንም አንድ እንሁን። ሌላው ይህን ኮሮና በሽታ ያርቅልን ፤ ራሳችንን እየጠበቅን። የሀላባ ከተማ ደጋፊዎች በፍቅር ተቀብላችሁ በፍቅር ስለሸኛችሁኝ አጠቃላይ ላደረጉልኝ ነገሮች ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!