የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከግርማ ዲሳሳ ጋር…

የባህር ዳር ከተማው የመስመር ተጫዋች ግርማ ዲሳሳ በዛሬው ‘የዘመናችን ከዋክብት ገፅ’ ላይ እንግዳ አድርገነዋል።

በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 12 አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ የሚናገረው የዛሬው እንግዳችን ግርማ ከልጅነቱ ጀምሮ ከኳስ ውጪ የሚያዘወትረው ነገር እንደሌለ ያወሳል። በተለይ እንደ አርዓያ የሚያየው ታላቅ ወንድሙ እግርኳስ ተጫዋች ስለነበር እሱን ለመከተል ሲሞክር እና ሲጥር እንደነበር ያስታውሳል። ከምንም በላይ ደግሞ ትምህርት ቤት እያለ ወወክማ ለተባለ ቡድን ተመርጦ ጨዋታዎችን ማድረግ ሲጀምር የእግርኳስ ህይወቱን ከምንም ወደ አንድ የተሻለ ደረጃ አሸጋገረ። በዚህ ክለብ ውስጥ በባህር ዳር በሚደረግ የውስጥ ውድድር ላይ ሲሳተፍም በብሔራዊ ሊግ የሚሳተፈውን ዳሞት ከተማ ለማገልገል እድሉን አገኘ። በዳሞት ከተማም ለ1 ዓመት ከ6 ወር ከተጫወተ በኋላ ዳግም ወደ ትውልድ ከተማው በመመለስ ለአማራ ፖሊስ ፊርማውን አኑሮ ለግማሽ ዓመት ግልጋሎት ሰጠ። ዓመቱም እንደተገባደደ ጉዞውን ወደ ጣና ሞገዶቹ ቤት አድርጎ ውሃ ሰማያዊውን መለያ ለብሶ መጫወት ያዘ።

በሁለቱም መስመሮች ላይ በአጥቂ እና አማካይነት ቦታ መጫወት የሚችለው ግርማ በችግሮች ጊዜም ወደ ኋላ እየተመለሰ የመስመር ተከላካይ ሆኖ ሲጫወት ታይቷል። በተለይ ፍጥነት እና ቅልጥፍናውን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው የመስመር ላይ ሩጫዎች ብዙዎች ልብ ውስጥ በቀላሉ እንዲገባ አስችሎታል። ይህንን ብቃቱን ተከትሎ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ተጫዋቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ አካተውት ነበር።

ከቀናት በፊት ከ3 ዓመታት በላይ የተጫወተበትን ክለብ ለተጨማሪ 2 ዓመታት ለማገልገል የተስማማው ግርማ ዲሳሳ በዛሬው የ’ዘመናችን ከዋክብት ገፅ’ ላይ እንግዳ አድርገን አጫጭር ጥያቄዎችን አቅርበንለታል።

ኮቪድ-19 የእግርኳስ ውድድሮችን ካቋረጠ በኋላ ግርማ ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው?

ብዙ ጊዜ ቤት ነኝ። ቤት ስሆን ግን ዝም ብዬ አደለም የምቀመጠው። ስፖርተኛም ስለሆንኩ የተለያዩ ስራዎችን ቤት ሆኜ እሰራለሁ። ከዚህ ውጪ ምግብ ማብሰል ስለምወድ ምግብ እያበሰልኩ እና መጽሐፍ እያነበብኩ ቀኔን እገፋለሁ።

ምግብ ማብሰል ላይ ጎበዝ ነህ? ምን ምግብ ነው የሚጣፍጥልህ? የምታዘወትረውስ ምግብ ምንድን ነው?

ራሴን በደንብ ነው የምመግበው። እንደውም የሚያቁኝ ሰዎች ‘የምትበላው የት ነው የሚሄደው?’ ይሉኛል። የት እንደሚሄድ እንጃ እንጂ ስፖርተኛም ስለሆንኩ በደንብ እመገባለው። የምወደው ምግብ ዶሮ ነው። በተለይ በአሮስቶ መልክ። በተቃራኒው ፓስታ አልወድም። በሱ ምትክ ሩዝ እበላለሁ። የሚጣፍጥልኝ ምግብ ደግሞ ሽሮ ነው። እጮኛዬም ሽሮ እና ሳንዱች ስሰራላት ደስ ይላታል።

ኮቪድ-19 ከተከሰተ በኋላ የለመድከው ወይም ያዳበርከው አዲስ ልማድ አለ?

ኮቪድ ብዙ ነገሮችን ቢያመሰቃቅልም በትንሹም ቢሆን ይዞት የመጣው በጎ ነገር አለ። በተለይ ራስን በመፈለግ ረገድ። ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ እኔ መጽሐፍ የማንበብ አዲስ ልማድ አዳብሬያለሁ።

ኮቪድ አሁን ጠፍቷል ቢባል መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው?

እየሮጥኩ ስታዲየም ነው የምገባው። ስታዲየም በጣም ናፍቆኛል። ያልከው ነገር በቶሎ ይሁን እንጂ ሙሉ ትጥቄን ለብሼ ቀጥ ብዬ ስታዲየም ነው የምገባው። በተለይ ደግሞ በደጋፊዎች ታጅቤ ኳስ መጫወት እጅግ ናፍቆኛል።

በእግርኳስ ካሳለፍክባቸው ዓመታት በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት የትኛው ነው?

ምርጥነት አንፃራዊ ነው። ለምሳሌ ዳሞት ከተማ ስሄድ በመጀመሪያ ዓመቴ ምርጥ ብቃቴን ያሳየሁበት ነበር። ግን ከእሱ የበለጠ 2010 ላይ ባህር ዳር ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊግ ስናሳልፍ የነበረኝ ብቃት ጥሩ ነበር።ግርማ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን ምን ይሆን ነበር?

እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን እግርኳስ ተጫዋች ነው የምሆነው(እየሳቀ)። ወደየትኛውም ሙያ አልሄድም ነበር። ሲጀምርም ኳስ ስለመረጠችኝ የትም አልሄድም።

አብሬው ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል የምትለው ተጫዋች አለ?

በብዛት አሉ። ግን ከሽመልስ በቀለ ጋር ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል። መልካሙ የተባለም አንድ ተጫዋች ነበር በልጅነቴ እያየሁት ያደኩት። በልጅነቴም እሱን ስላየሁት ብቃቱ ከልቤ አልወጣም። ከዚህ መነሻነት ከእርሱም ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል። በተለይ ደግሞ ከሽመልስ ጋር።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚፈትንህ ተጫዋችስ አለ?

ኧረ በጭራሽ። እስካሁን የሚከብደኝ ወይም የሚፈትነኝ ተጫዋች አላጋጠመኝም።

በዚህ ሰዓት በሃገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?

ራስ ወዳድ እንዳልባል እንጂ ነገሮች ወደ እኔ ያመዝኑብኛል። እርግጥ ሌሎች ምርጥ ተጫዋቾች ቢኖሩም ለእኔ ምርጡ ተጫዋች ራሴ ነኝ (እየሳቀ)።

የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ሜዳ ላይ ስምህን እያነሱ ይዘምሩልሃል። ደጋፊዎቹ ካንተ ምን የተለየ ነገር አግኝተው ነው?

እርግጥ የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ለእኔ ብቻ ሳይሆን ሜዳ ላይ ጥሩ ለሰራ ሁሉ ይጨፍራሉ። በብዙ ነገርም ከጎንህ እንደሆኑ ይገልፁልካል። ከምንም በላይ ታታሪ መሆንን ስለሚወዱ ነው የተጫዋች ስም እያነሱ የሚዘምሩት። ተጫዋች ደግሞ ከዓመት እስከ ዓመት ምርጥ ሆኖ አይቆይም። ስትወርድ እንድትበረታ ይተቹሃል፣ ስትጠነክር ደግሞ እያደገፉህ ይሄዳሉ። እኔም ስሜን እያነሱ ሲደግፉኝም ሆነ ስተቹኝ ሁሌ ለመነሳሳት እሞክራለው። በተለይ ሲደግፉኝ የተሻሉ ነገሮችን ለማምጣት እጥራለሁ።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበት አጋጣሚ ካለ አጋራን እስኪ?

ባህር ዳር ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ በጣም ተደስቼ ነበር። ከበፊት ጀምሮ ብዙ መስዋትነት የተከፈለበትን ነገር ስላሳካን በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። በተለይ የታሪኩ አንድ አካል በመሆኔ ሀሴት ተሰምቶኛል።

የተከፋህበትስ ጊዜ ይሆር ይሆን?

አይጠፈም። ሁሌ ደስታ የለም። ምናልባት ግን ዳሞት ከተማ እያለሁ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ፍፁም ቅጣት የሳትኩበት ቅፅበት ከሁሉም የከፋው ሊሆን ይችላል። ብድናችን ብሔራዊ ሊግ ነበር ግን ያንን ጨዋታ ቢያሸንፍ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚመጣበት እድል የሰፋ ነበር። ግን አልሆነም። በዚህም በጊዜው ተከፍቼ ነበር።

በሊጉ ላይ ከሚገኙ 15 ክለቦች ጋር ከሚደረጉ ጨዋታዎች የትኛውን እና ከማን ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ነው በጉጉት የምትጠብቀው? ለምን?

ከፋሲል ከነማ ጋር ያለው ደርቢም በጉጉት የምጠብቀው ጨዋታ ነው። ግን ከደርቢው በላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው መርሐ-ግብር በጣም ደስ ይለኛል። በጉጉትም የምጠብቀው እሱን ጨዋታ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ አንጋፋ እና ባለታሪክ ክለብ ስለሆነ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ተጫዋች ከቡድኑ ጋር በተቃራኒ መጫወት ይፈልጋሉ።

አንድ የቡድን አጋርህ ሜዳ ላይ ኳስ መፈለግ ትቶ ጥርስ ሲፈልግ የነበረበትን አጋጣሚ ሰምቻለሁ። እስኪ ስለዚህ አስገራሚ ገጠመኝ አውጋን?

(እየሳቀ) ልክ ነው። የተጫዋቹን ስም አልነግርህም ግን ሜዳ ላይ እኛ ኳስ እየተጫወትን ይህ የቡድን አጋሬ የተተከለለት ሰው ሰራሽ ጥርስ ተነቅሎበት ጠፋ። እኛ እየተጫወትን እሱ ኳሱን ትቶ ጥርሱን ይፈልጋል። ኳስ እግሩ ስር ሲደርስ እራሱ አይኑ ሳሩ ላይ ነበር። እርግጥ እኔ ጨዋታው አልቆ ከሜዳ እየወጣሁ እያለ ነው ምን ሆኖ ነው ዛሬ ስንል ጥርሱ ጠፍቶበት ሲፈልግ እንደነበረ የሰማነው። ‘እዛ ሳር ላይ አንድ ጥርስ የሚፈልገው የዝሆን ጥርስ ነው እንዴ ያስተከለው’ እየተባለ ሲሾፍበት ሁሉ ነበር። በሰዓቱም በጣም አስቆኝ ነበር። አሁን እራሱ ይህንን ቃለ መጠይቅ አይቶ እንደሚደውልልኝ እርግጠኛ ነኝ።

በእግርኳስ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛህ ማነው?

እንደ ወንድም የማየው ተጫዋች ዳግማዊ ሙሉጌታ ነው። ዳግም ባህር ዳር ስቀላቀል ጀምሮ አብሮኝ የነበረ እና ያበረታታኝ የነበረ ተጫዋች ነው። ካምፕ ውስጥ እራሱ አንድ ክፍል ነው አብረን የምንጋራው።

ቅድም ከእግርኳስ ውጪ በየትኛውም ሙያ አታገኙኝም በለህ ነበር። እግርኳሱን ካቆምክ በኋላ በምንድን ሙያ ነው ህይወትህን የምትቀጥለው? በስልጠናው ዓለም እንጠብቅህ?

(በምሬት) አሰልጣኝማ መቼም አልሆንም። ግን ከስፖርቱ አልርቅም። እጮኛዬም የስፖርት ትጥቆችን ስለምትሸጥ ከእሷ ጋር በጋራ በመሆን ከስፖርቱ ሳልርቅ ወደ ንግዱ ዓለም የምገባ ይመስለኛል።

በመልሶችህ መካከል እጮኛዬ የሚል ሃረግ በተደጋጋሚ እየተጠቀምክ ነው። የግል ህይወትህ ምን ይመስላል?

በቅርቡ መሞሸሬ አይቀርም። ድግስም እንዳልደግስ ኮሮናው ጥሩ አጋጣሚ ነው የሆነኝ (እየሳቀ)። ፈጣሪ ከፈቀደ ከእጮኛዬ ጋር ለመጠቃለል አስበናል።

ግርማ ምን የተለየ ባህሪ አለው?

የተለየ ባህሪዬ ለሙዚቃ ያለኝ ልዩ ፍቅር ነው። ከኳስ እኩል ለሙዚቃ ጥሩ ስሜት አለኝ። በተለይ የበፊት ሙዚቃዎቸን አደምጣለሁ። ከዛም ባገኘሁት ቦታ አዜማለሁ። ድምፄም አሪፍ ነው መሰለኝ ብዙ ጓደኞቼ ዝፈንልን ይሉኛል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ