የሴቶች ገፅ | ኳስ ለመጫወት ብላ ለበዓል የተገዛን በግ የሰዋችሁ ብዙሃን እንዳለ

ጊንጪ በምትባል የኦሮሚያ ከተማ ተወልዳ ነገር ግን ገና አንድ ዓመት ሳይሞላት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ቶታል 3 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ እድገቷን የቀጠለችው ብዙሃን በክለብ እና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብዙ ስኬቶችን አግኝታለች። በተለይ ለ13 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ድንቅ ግልጋሎት በመስጠት እና በ4 የተለያዩ ክለቦች 26 ዋንጫዎችን በማምጣት በሴቶች እግርኳስ ላይ ያላትን ስም በጥሩ ደረጃ ላይ አፅፋለች። ይህቺ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና፣ የሴንትራል የጤና ኮሌጅ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም አሁን ላይ በድሬዳዋ የምትገኘው ተጫዋች በልጅነቷ የተፈጠረን የበዓል ሰሞን አስገራሚ ገጠመኝ በትዝታ መለስ ብላ ታጫውተናለች።

“ህፃን እያለሁ አባቴ ከቤት እንድወጣ አይፈልግም ነበር። በተለይ ደግሞ በሰፈሬ ሌሎች ሴቶች ኳስ ስለማይጫወቱ ከወንዶች ጋር ነበር የምጫወተው። ከዚህ መነሻነት አባቴ በሴትነቴ ጥቃት እንዳይደርስብኝ ስለሚሰጋ ፈፅሞ ከቤት አያሶጣኝም ነበር። እኔ ግን እየተደበኩም ቢሆን እየወጣሁ እጫወት ነበር። አንድ ጊዜ አባቴ ለበዓል ብሎ በግ ገዛ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በጉ ከበዓሉ ቀን ቀደም ብሎ ነበር የተገዛው። ይህ ግን ለእኔ በጣም ነበር የጠቀመኝ። ምክንያቱም በጉን ሳር ላብላ እያልኩ ከቤት የምወጣበትን እድል ስለሰጠኝ። በዓሉ እንደ ነገ ሆኖ እኔ ቀድሜ እንዳልኩህ በጉን ሳር ላብላ ብዬ ይዤው ወጣሁ። ከቤት የወጣሁት ግን በዋናነት በጉን ሳር ለማብላት ሳይሆን የሚጠበቅ የሰፈራችን ግጥሚያ ላይ ለመሳተፍ ነበር። ጨዋታው የሰፈር ግጥሚያ ቢሆንም እኔን ጨማሮ በርካታ የሰፈራችን ልጆች ስንጠብቀው የነበርነው ግጥሚያ ነበር። በቡድናችን ውስጥ ደግሞ እኔ እና አንድ ልጅ ነበር በጣም የምንጠበቀው። ሁለታችን ከሌለን ደግሞ ጨዋታውን መሸነፋችን ሆነ። ብቻ በጉን ሳር ላብላ ብዬ ከቤት ወጥቼ ወደ ሜዳ ሄድኩ። የምንጋጠምበት ሜዳ ተራራማ ስለነበረ በጉ ቅጠል እንዲበላ ለቅቄው እኔ ወደ ጨዋታዬ አመራሁ። ከዛ ኳሱን ተጫውተን ጨርሰን ወደ ቤት ልናመራ ስንል በግ ይዤ መውጣቴ ትዝ አለኝ። በጉን የለቀኩበት ቦታ ስሄድም በጉ የለም። ብፈልገው፣ ብፈልገው ላገኘው አልቻልኩም። ቀኑም መሽቶ 2 ሰዓት ሆነ። ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ ባዶ እጄን ወደ ቤት ገባሁ። እቤት ስገባ አባቴ የለም ነበር። እሱ በጣም ሃይለኛ ስለነበረ ‘ለአባትሽ በጉ ደንብሮ ነው ከቤት የጠፋው እንለዋለን። አንቺ ግን ከዚህ በኋላ ኳስ የሚባል ነገር አትጫወቺም’ አሉኝ እናቴን ጨምሮ እቤት ያሉት ቤተሰቦቼ። እኔም በጊዜው ላለመቀጣት እሺ አልኩ። አባቴም ሲመጣ በጉ ከቤት አምልጦ እንደጠፋ ተነግሮት ሌላ በግ በማግስቱ ገዛ።”

ኳስ ለመጫወት ብላ አባቷ የገዛውን በግ የሰዋችው ብዙሃን በግጥሚያው እለት በጣለ ከባድ ዝናብ ጨዋታው እንደተቋረጠ እና ከበጉም ከጨዋታውም ሳትሆን መቅረቷን ትናገራለች።

“ደግሞ የሚገርመው ጨዋታው በዝናብ መቋረጡ ነው። ወንዝ ተሻግረን ስለሆነ ወደ ሜዳው የመጣነው ደራሽ እንዳይዘን ቶሎ እንሂድ ተባብለን ነው ጨዋታውን ያቋረጥነው። በጊዜው ግን ወይ ከበጌ አልያም ከኳሴ ሳልሆን ቀረሁ። ጨዋታውን አሸንፈን እንኳን ቢሆን በሱ እካስ ነበር። ግን ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ የተያዘለት ጨዋታም አላመለጠኝም ነበር። እርግጥ ከቤት ለኳስ ብለሽ እንዳትወጪ ብባልም እኔ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠርኩ እወጣ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ጨዋታው የተላለፈበት ቀን ላይ ቤተሰቦቼ ቤተክርስትያን ብለው በለሊት ወጡ። እኔም እነሱን ተከትዬ ለ4 ሰዓት ጨዋታ 12 ሰዓት ላይ ከቤት ወጣሁ። የጨዋታ ሰዓት እስኪደርስም ከሌሎች ቡድኖች ጋር ሩጫ እና ሰርከስ እየሰራሁ ጠበኩ። በመጨረሻም በግን ጨምሮ ብዙ መስዋትነት የተከፈለበትን ጨዋታ 2-1 አሸነፍን።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!