“ኢትዮጵያ ቡናን ረጅም ዓመት በማገልገል ብዙ ዋንጫዎችን ማንሳት እፈልጋለው” ተስፈኛው አላዛር ሽመልስ

ያለፉትን አራት ዓመታት ከተለያዩ የታዳጊ ቡድኖች ጋር የእግርኳስ ጅማሬውን ካደረገ በኃላ በዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀል በተጫወተባቸው ጨዋታዎች መልካም እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ተስፈኛው ወጣት አላዛር ሽመልስ የዛሬው እንግዳችን ነው።

ወደፊት ክለቡን በሚገባ እንደሚጠቅም የተረዳው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ነበር በ2012 የሦስት ዓመት ኮንትራት እንዲፈርም ያደረገው። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተቀይሮ በመግባት ከመስመር ሰብሮ በመግባት ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ በብዙዎች ዓይን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በፕሪምየር ሊጉ በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት የተጫወተው አላዛር በተለይ ጎንደር ዐፄ ፋሲል ስታዲየም የአቡበከር ናስር በመጀመርያው ደቂቃ በጉዳት መውጣቱን ተከትሎ ወደ ሜዳ በመግባት መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል። ወደ ፊትም በቡናዎቹ መለያ ደምቆ ይወጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

አዲስ አበባ ኮልፌ ሠፈረ ሰላም የተወለደው አላዛር በአባቱ ጥረት የአሰልጣኝ ማትዮስ እገዛ ታክሎበት ፕሮጀክት ውስጥ ታቅፎ ከፍተኛ ሰባት ሜዳ እግርኳስን መጫወት ጀምሯል። ዕድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ የሚጫወትበት መንደር ድረስ በመምጣት ለብዙዎች ታዳጊዎች መነሻ በመሆን አሻራውን እያሳረፈ የሚገኘው አሰልጣኝ ይገዙ ተስፋ ለኢትዮጵያ በሚባል ታዳጊ ቡድኑ ውስጥ ተቀላቅሎ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በሚካሄዱ የታዳጊ ውድድሮች ላይ በአንድ የውድድር ዓመት ሃያ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በ2008 ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን የተካተተው አላዛር በዚሁ ዓመት ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ጥሪ ቀርቦለት በደርሶ መልስ ውጤት ግብፅን 5-2 ባሸነፈው ቡድን ውስጥ በመጀመርያው ጨዋታ ላይ ተካቶ የነበረ ቢሆንም ፓስፖርቱ ጠፍቶበት በቀጣይ ጨዋታ እንዳይገባ መደረጉ አሁንም ድረስ እንደሚቆጨው ይናገራል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከ17 ዓመት ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው የዛሬው የተስፈኞች አምዳችን እንግዳ አላዛር ከ2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና ዋናው ቡድን እያገለገለ ይገኛል። ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ተጠርቶ መጫወቱም ይታወሳል። ለታዳጊ ተጫዋቾች እድል በመስጠት የማይታማው ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ይህን ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች በብዙ መልኩ እንደሚጠቀሙበት ይታመናል። ባለ ግራ እግሩ ጥበበኛ ተጫዋችም ስለ አስተዳደጉ እና ወደ ፊት ስለሚያስበው እቅዱ እንዲህ ይናገራል።

” በጣም እድለኛ ነኝ የመጫወት እድል የሚሰጥ እና በታዳጊዎች የሚያምን ቡድን ውስጥ ነው ያለሁት። አሰልጣኝ ካሳዬ ብዙ ነገሬን ቀይሮልኛል። በተሰጠኝ የመጫወት እድል ለመጠቀም ጠንክሬ እየሰራው ነው። በኮሮና ውድድሩ ቢቋረጥም ያለ ማቋረጥ ልምምዴን እየሰራው እገኛለው። በቀጣይም እንደነ አቡበከር እና ሚኪያስ ቋሚ ተሰላፊ ሆኜ ኢትዮጵያ ቡናን ለረጅም ዓመት ማገልገል ብዙ ዋንጫዎችን ማንሳት እፈልጋለው። መሸነፍ አልወድም ልምምድ ይሁን ጨዋታ ላይ መሸነፍ አልፈልግም። ለዚህም ነው በጣም እልህኛ የሆንኩት። ይህ ደግሞ ከለጅነቴ ጀምሮ የመጣ ነው። የቅጣት ምት ጎሎችን ማስቆጠር የቻልኩት በልምምድ ያመጣሁት ነው። በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ግብፅ ጨዋታ ተሳትፌ አለው። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላቅም ለመልሱ ጨዋታ እያሰብኩ ፓስፖርትህ ጠፍቷል ተብዬ ከብሔራዊ ቡድን ውጭ መደረጌ ቢያስቆጨኝም በቀጣይ ሀገሬን ወክዬ በተለያዩ ውድድሮች መሳተፍ እፈልጋለው።

የአካባቢዬ ሰዎች የሚያደርጉልኝ ድጋፍ አለ ያበረታቱኛል። አሰልጣኞቼም ለኔ በጣም ጥሩ ናቸው። ብቻ ከጎኔ ብዙ ሰዎች አሉ ብዙም አልቆየሁም ወደ ክለቦች ለመግባት አሁንም ቡና ባለኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሠፈራችን ውስጥ እግርኳስን ጀምረው ከመንገድ የቀሩ አሉ ከእነርሱም የምማረው አለ። እራሴን እግርኳሱ ከማይፈልጋቸው ነገሮች ጠብቄ እየኖርኩኝ ነው። ጀማል ጣሳው ጎረቤቴ ነው እርሱ ምን ማድረግ እንዳለበኝ በጣም ይመክረኛል አመሰግነዋለው። አሰልጣኝ ማትያስ እና ይገዙንም አመሰግናለው። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አምኖብኝ እድል ስለሰጠኝ እርሱንም አመሰግናለው። የሠፈር ጓደኞቼንም በጣም አመሰግናለው። በተለይ ግን አባቴን በጣም ማመስገን እፈልጋለው። ብዙ ነገሮች እየገዛ ፣ እያበረታታ እዚህ ለመድረሴ የእርሱ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነው። ምንም ነገር አጉሎብኝ አያቅም። አንድ ገጠመኝ ልንገርህ በዘመን መለወጫ ነው። የሠፈር ልጆች ቤተሰቦቻቸው ልብስ ሲገዛላቸው አይቼ እኔም አባቴን ልብስ ግዛልኝ ስለው ምን ልግዛልህ ብሎ ጠየቀኝ። የዚዳንን ማልያ ግዛልኝ አልኩት፤ እርሱም በአዲስ ዓመት የሪያል ማድሪድ ማልያ ገዝቶልኝ በዓልን በማልያ ሳከብር ውያለው… (እየሳቀ)”

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!