“የውድድር ዓመቱ ልፋቴ በእውቅና በመገባደዱ ደስ ብሎኛል” ሎዛ አበራ

በሴቶች ዘርፍ የማልታ የ2019/20 ምርጥ ተጫዋች ተብላ የተመረጠችው ሎዛ አበራ ስለምርጫው እና ስለተሰማት ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ ሃሳቧን ሰጥታለች።

በዱራሜ ተወልዳ ያደገችው ሎዛ አበራ በክለብ ደረጃ ያላትን ህይወት ወደ ሀዋሳ ከተማ በመሄድ ‘ሀ’ ብላ ጀምራለች። በሀዋሳ ከተማ ራሷን ካበቃች በኋላም 2007 ላይ ወደ ደደቢት በመምጣት በይበለጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ተሸጋገረች። በዚህ ክለብ በቆየችባቸው አራት ዓመታትም የሊጉን ዋንጫ ለ3 ተከታታይ ጊዜያት በማግኘት፣ 4 ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና 1 ጊዜ የሊጉ ኮከብ ተጫዋች በመሆን የእግርኳስ ህይወቷን በጥሩ መንገድ አስቀጠለች። ተጫዋቿ በደደቢት በቆየችባቸው አራት ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የዓመቱ ግለሰብ ተብላ ተሸልማለች። በተጨማሪም 2008 ላይ 57 ጎሎችን ያስቆጠረችው ሎዛ ቡድኗ ደደቢት እቴጌን ገጥሞ ሲያሸንፍ ለብቻዋ 9 ጎሎችን አስቆጥራ በአንድ ጨዋታ ብዙ ኳሶችን ከመረብ ያገናኘች ብቸኛዋ ተጫዋች ሆናለች። በዚህ ምርጥ ብቃቷም ከሃገሯ ወጥታ መጫወት የምትችልበትን አጋጣሚ አገኝታ ጉዞዋን ወደ ሲውድን አደረገች። በሲውድኑ ክለብ ከንግስባካ ለግማሽ ዓመት ከቆየች በኋላ ዳግም ወደ ሃገሯ በመመለስ አዳማ ከተማን በግማሽ ዓመት ውል ተቀላቅላ የሊጉን ዋንጫ ለሦስተኛ ጊዜ ከፍ አደረገች።

የብቃቷን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልን ተከትሎም ዓምና የማልታውን ቢርኪርካራ ክለብ ተቀላቅሎ የመጫወት እድል አግኝታ ወደ አውሮፓ አመራች። በዚህ ክለብም 30 ግቦችን አስቆጥራ 2 ዋንጫዎችን አግኝታለች። በክለቡ ባሳየችው አቋምም የማልታ እግርኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የ2019/20 የዓመቱ ምርጥ ሴት እግርኳስ ተጫዋች ብሎ መርጧታል። ሶከር ኢትዮጰያም የፊታችን እሁድ የምትሞሸረውን ይህቺን ተጫዋች አግኝታ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

“ዓምና በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከክለቤ ቢርኪርካራ ጋር እንደ ቡድንም ሆነ እኔም በግሌ ውጤታማ ጊዜ ነበረኝ። በቅድሚያ ግን ውድድሩ ላይ እየተሳተፍኩ እንደዚህ አይነት ምርጫ እንዳለ አላቅም ነበር። እርግጥ ውድደድሩ ካለቀም በኋላ አላቅም ነበር። ከጥቂት ቀናት በፊት ግን ሽልማቶች እንዳሉ እና የምርጫው እጩዎች ውስጥ እንደገባሁ ተነገረኝ። ትናንት ምሽት ደግሞ ማልታ ላይ በነበረ ዝግጅት አሸናፊ መሆኔ ሲገለፅ ሰማሁ።

” ዓምና የነበረኝ አቋም፣ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆኔ እና ክለባችን ዋንጫዎችን እንዲያገኝ ማድረጌ ለምርጫው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። እርግጥ እኔ ብቻ ሳልሆን የቡድን አጋሮቼም ቢርኪርካራ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ረድተዋል። ግን እኔ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ብሆንም በሙሉ ልብ ምርጫውን አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም። በአጠቃላይ ግን የውድድር ዓመቱ ልፋቴ በእውቅና በመገባደዱ ደስ ብሎኛል።”

በምርጫው ደስታ እንደተሰማት እየነገረችን ያለችው ሎዛ በቀጣይ ማረፊያዋን በተመለከተ ያቀረብንላትን ጥያቄ በአጭሩ መልሳልናለች።

“አሁን ላይ ቀጣይ ማረፊያዬ ይህ ክለብ ነው ብዬ መናገር አልችልም። ግን ሁሌም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ ስለምፈልግ ጥሩ ደረጃ ላይ ያለን ክለብ ለመቀላቀል እሞክራለሁ። ከቢርኪርካራ ጋር ያለኝንም ነገር ወደፊት የምናየው ይሆናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!