በሀገራችን እግርኳስ በሰባዎቹ እና ሰማንያዎቹ ከታዩ ከዋክብት አንዱ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ የአስር ዓመት ቆይታው ወደ በርካታ ዋንጫዎች እና የግል ክብሮች አሳክቷል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ዘጠኝ ዓመታት ተጫውቶ ለሰባት ዓመታት ቡድኑን በአምበልነት በመምራት አይረሴው የ1980 የሴካፋ ዋንጫን አንስቷል።
ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ ድንቅ የሆነ ብቃቱን በማውጣት በከፍተኛ አንድ፣ ባህር ዳር ጨርቃጨርቅ እና መጨረሻም በቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ አንበሳ ለመታየት በቅቷል። የአየር ኳስ አጠቃቀም፣ አብዶ መስራት ፣ ግብ ማስቆጠር እና ዋንጫዎች መሳም ታዳሚዎችን የማስቦረቁን ያህን እሱም ፍፁም እርካታ እንደተጎናፀፈበት ሁሌም በልበ ሙሉነት ይገልፃል። በጊዜው ለእግር ኳሱ ቅርብ የነበሩ ተመልካቾች እና ጋዜጠኞች ይህ ሰው በሰማንያዎቹ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ እንደነበርም ይመሰክራሉ። ዘመነኞቹ :-
“የምን ማራዶና የምን ፔሌ ፔሌ
እኛም ሀገር አለ ገብረመድኅን ኃይሌ”
እያሉ ያሞካሹት የቀድሞው ታላቅ አጥቂ ገብረመድኅን ኃይሌ !
ከዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኘው እና በልጅነቱ ጥሩ የእግር ኳስ ክህሎት እንደነበረው የሚነገርለት ገብረመድኅን በለጋ ዕድሜው ባሎኒ በተባለው አንጋፋ የመቐለ ሜዳ በዕድሜ ከሚበልጡት ተጫዋቾች በመጫወት እንደጀመረ ይናገራል። በተጠቀሰው ሜዳ የእግር ኳስ ሕይወቱን ሀ ብሎ በመጀመር ቀጥሎም ለከፍተኛ አንድ መጫወት ቢችልም በከፍተኛ አንድ ቆይታው መሐል ግን ትግራይ ክፍለ ሀገርን ወክሎ በ1974 የቅርጫት ኳስ ውድድር ቻምፒዮን ሆኗል። በተጠቀሰው ዓመትም በድጋሚ ከትግራይ ጋር በእግርኳስ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
በለጋነቱ ከዕድሜው ጋር የማይመጣጠን ክህሎት እና ተክለሰውነት እንደነበረው በብዙዎች የሚነገርለት ገብሬ ምንም እንኳ ዕድሜው ገና ቢሆንም በ1975 በወቅቱ ጥሩ ስብስብ ለነበራቸው ባህርዳር ጨርቃጨርቅ ሳይጠበቅ ፌርማውን ሊያኖር ችሏል። ገብረመድኅን ወቅቱን ስያስታውስም እንዲህ ይላል። ” በመጀመርያው ክለቤ ጥሩ ብቃት ካሳየሁ በኃላ በአቶ ኃይሉ ገብረመስቀል ጠቋሚነት ወደ ባህርዳር አመራሁ ፤ መጀመርያ ልክ ከአውሮፕላን ስወርድ የተቀበሉኝ ሰዎችም ገርሟቸዋል። አቶ ኃይሉ ገብረመስቀል ‘ይሄንን ልጅ ነው ወደ ክለባችን እንዲፈርም ያመጡት?’ አሉ በግርምት፤ ምክንያቱም ቀጫጫ ነበርኩ። የለበስኩት ልብስ ራሱ ስፖርተኛ ስለማያስመስል በሁኔታዬ በጣም ተገርመው ነበር። ከክለቡ ጋር ልምምድ እስከጀመርኩባት ቀንም ‘ይሄ ልጅ ነው እግር ኳስ የሚጫወተው?’ ብለው ተገርመው ነበር። ክለቡ ከተቀላቀልኩ በኃላ ግን ነገሮች ተቀየሩ። በብቃቴም መቶ በመቶ እርግጠኞች ሆኑ። ” ይላል ወደ ባህር ዳር ያቀናበትን ጊዜ ሲያስታውስ።
በዚህ መልኩ ወደ ባህር ዳር ካቀና በኃላ በጎጃም ክፍለ ሀገር ስመ ገናና ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም። እንደውም በ1976 በአስመራ በተካሄደው የክፍለ ሀገራት ውድድር ጎጃምን ወክሎ ምርጥ ብቃት በማሳየት የአካባቢውን እግርኳስ አፍቃርያን ቀልብ መግዛት ችሏል። ይህ ዓመት ከአስመራው የተሳካ የውድድር ቆይታ በኃላ ለመጀመርያ ግዜ የሃገሩን መለያ የለበሰበት ጊዜ ነበር። ዕድሜው ገና ስለነበርም ለወጣት እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን እየተመላለሰ ተጫውቷል።
ነገሮች በፍጥነት እየተጓዙለት የነበረው ገብረመድኅን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ሲገባ ግን ያተጠበቀ ነገር አጋጠመው። በጊዜው የተደረገው ነገርም በእግርኳስ ሕይወቱ ከማይዘነጋቸው ክስተቶች አንዱ መሆኑን በዚህ መልኩ ያስታውሰዋል። “ከወጣት ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በኃላ ወደ ባህር ዳር ስገባ ሰርፕራይዝ አድርገውኛል። ባህር ዳር ልትገባ ስትል ባለው የፍተሻ ቦታ ወታደሩ መጥቶ ‘እዚህ እናንተ መካከል ገብረመድኅን የሚባል አለ?’ አለን ድምፁ ከፍ አድርጎ። እኔም ከነበርኩበት ደንግጬ ተነሳሁና አቤት አልኩት። ‘ሰዉ አንተን እየጠበቀህ ነው፤ ውረድ’ አለኝና ወረድኩ። ከዛ በኃላ ያየሁት ግን ማመት አልቻልኩም። ደጋፊያችን፣ የክለብ አመራር እና የከተማው የእግር ኳስ አፍቃሪ እኔን ለመቀበል መጥቷል። አጅበውኝም ወደ ከተማ ሄዱ። የመጀመርያዬም ስለነበር ልዩ ደስታ ነበር የፈጠረልኝ።” ይላል ስለ ወቅቱ ያልተጠበቀ አቀባበል።
ገብረመድኅን በባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ሁለት የተሳኩ ዓመታት አሳልፎ ሁለት ዋንጫዎችም እንዲያነሳ ጉልህ ሚና ተጫወተ። በሕይወቱ አገኘዋለው ብሎ ያልጠበቀው ዝና እና ክብርንም አገኘ። የባህር ዳር ደጋፊ እና የከተማው ኑሮ ቢመቸውም ቅሉ በሀገሪቱ ትላልቅ ክለቦች ዓይን ውስጥ በመግባቱ ልቡ መሸፈቱ አልቀረም። በ1977ም ‘በሕይወቴ ከወሰንኳቸው ትላልቅ ውሳኔዎች አንዱ ነው’ ያለበትን ከባድ ውሳኔ ወሰነ። ከወጣት ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ ትልቅ ዝና ያስገኘለትን ባህር ዳር ጨርቃጨርቅን ለቆ ለታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን አኖረ።
በፈረሰኞቹ ቤት ብዙ ገድሎች ለመስራት ጊዜ ያልፈጀበት ገብሬ በመጀመርያ ዓመቱ ጥሩ ብቃት በማሳየት ከቡድኑ ጋር ዋንጫ አነሳ። ከ1977 እስከ 1986 በፈረሰኞቹ ቤት በቆየባቸው አስር የውድድር ዓመታት በ1979 እና በ1980 ሁለት ጊዜ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ሲሸለም በ1981 ደግሞ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን እንደተሸለመ ይናገራል። ” በግልም እንደ ቡድንም በጣም የተሳካ ግዜ ነበረን። በ1976 በወጣት ቡድን አብረውኝ ከነበሩት እነ ሙሉጌታ ከበደ ጋር ተነጋግረን ወደ ጊዮርጊስ ካመራን በኃላ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በወጣቶች የተገነባ ነበር። በዚህ ምክንያትም በዓመቱ መጀመርያ የልምድ እጥረት ይታይብን ነበር። እንደውም በመጀመርያው ጨዋታችን ሁለት ለባዶ ከመምራት አራት ለአራት አቻ ነው የወጣነው። ሆኖም ደጋፊውም አመራሩም በቡድኑ በጣም ደስተኞች ነበሩ። በዓመቱ መጨረሻ ግን ዋንጫው የኛ ነበር። እነ መቻልን ከመሳሰሉ ጠንካራ ቡድኖች ጋር ተፎካክረን ነበር ዋንጫውን ያነሳነው። በጊዮርጊስ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በቆየሁባቸው አስር ዓመታት ሙሉ ቡድኑን በቋሚነት ተጫውቻለው። በቁጥር ለመግለፅ የሚያዳግቱ ዋንጫዎች አንስቻለው። የአዲስ አበባ ሻምፒዮን ዋንጫ ከአስር ዓመቱ አንዴ ነው በመቻል የተነጠቅነው። ከዛ ውጭም በርካታ ዋንጫዎች ነበሩ። በግልም ቀላል የማይባሉ ስኬቶች አሉኝ። ሁለት ጊዜ ኮከብ ተጫዋች ሆኛለው። አንድ ጊዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኛለው።”
አጥቂው ከክለብ እግርኳስ በተጨማሪም ሀገሩን ለበርካታ ዓመታት በአምበልነት በማገልገል ይታወቃል። ከስልሳ በላይ ጨዋታዎች አድርጎ ወደ ሃያ አምስት የሚሆኑ ግቦች እንዳስቆጠረ የሚናገረው ገብረመድኅን የብሔራዊ ቡድን ቆይታው የተሳካ እንደነበር ይገልጻል። ” ገና ወጣት እያለሁ ነበር ሀገሬን ማገልገል የጀመርኩት። በሴካፋ፣ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ እና አፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድሮች ተሳትፌያለው። እንደውም ገና በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ ነበር አምበል መሆን የጀመርኩት። ዕድሜዬ ገና ቢሆንም በተፈጥሮ ያገኘሁት የመሪነት ባህሪ ነበረኝ፤ በብቃት ረገድም ጥሩ ነበርኩ። ለሃገሬ ከስልሳ አምስት በላይ ጨዋታዎች አድርጌ ሃያ አምስት የሚደርሱ ጎሎች አስቆጥሬያለው። ከዛ ውጭ ብዙ ጊዜ ወደ ቀድመሰዋ ሶቪየት ኅብረት አምርቻለው። በሁለቱ ሶሻሊስት ሃገራት መካከል የዲፕሎማስያዊ ስምምነት ስለነበር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ለማድረግ እንሄድ ነበር። እንደውም አንድ ጊዜ ከሩስያ ወጣት ቡድን ተጫውተን 4-1 ስናሸንፍ አራቱንም ግቦች አስቆጥሬያለው። በአጠቃላይ በብሄራዊ ቡድን እጅግ የተሳካ ጊዜ ነበረኝ።” ይላል።
አንድ ተጫዋች በጨዋታ ዘመኑ አንድ ታሪካዊ ግብ ለማስመዝገብ ያልማል። ነገር ግን ታሪካዊ ጎል ለማስቆጠር የተሻለ ዕድል ያላቸው የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ናቸው። ወደ አስር ዓመት ዓመት በሚጠጋው የእግር ኳስ ሕይወታቸው ከሚያስቆጥሯቸው ግቦች መካከል ዕድለኛ ከሆኑ አንድ ግባቸው በልዩ በታሪክ መዝገብ ሊካተትላቸው ይችላል። በዚህ ረገድም በገብረመድኅን ኃይሌ የእግርኳስ ሕይወት ውስጥ የምትጠቀሰው በ1980 የሴካፋ ውድድር ዚምባብዌ ላይ ያስቆጠራት ወሳኝ ግብ ነች። ግቧም ኢትዮጵያ ከሃያ ስድስት ዓመታት በኃላ ከዋንጫ ጋር እንድትገናኝ፤ የመጀመርያ የሴካፋ ድል እንድትሆን ያስቻለች የተጨማሪ ደቂቃ ወሳኝ ግብ ነች። በመለያ ምቶች በተጠናቀቀው ጨዋታ አንዷን ምት በማስቆጠር ኢትዮጵያ አሸናፊ ስትሆንም ዋንጫውን በአምበልነት አንስቷል። በተጫዋችነት ዘመኑ በአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ ዕድል ላላገኘው ገብረመድኅን የ1980ው ሴካፋ ድል በብሔራዊ ቡድን ቆይታው የሚጠቀስ ስኬት ነው።
ለዓመታት በምርጥ ብቃትና በወጥነት የተጫወተው አጥቂው በሰማንያዎቹ መጨረሻ ግን ጉዳት በተደጋጋሚ ይጎበኘው ጀመር። በዚህ ምክንያትም ከአስር ስኬታማ ዓመታት የፈረሰኞቹ ቆይታ በኃላ ከክለቡ ጋር ለመለያየት ተገደደ። ከፈረሰኞቹ ጋር ከተለያየ በኃላም ከእግር ኳስ ለመገለል ቢያስብም በቅርብ ጓደኞቹ ውትወታ እርሻ ሰብልን ለመቀላቀል ወሰነ። አጥቂው በአዲሱ ክለቡ መልካም አጀማመር ቢያደርግም በክለቡ በነበረው ያልተመቸ ሁኔታ ምክንያት ቆይታው በአጭሩ እንደተቀጨ ያስታውሳል። ” ከአስር የተሳኩ ዓመታት በኃላ ጊዮርጊስን ለቀቅኩ። ከዛ በቅርብ ጓደኞቼ ጥያቄ ወደ እርሻ ሰብል አመራሁ። አጀማመሬ ጥሩ ነበር። ሆኖም በክለቡ በነበሩ አንዳንድ ያልተመቹ ሁኔታዎች መቆየት አልፈለግኩም። ክለቡን ለቅቄም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመመለስ በተመረቅኩበት ሞያ መስራት ጀመርኩ። ” ይላል።
በበርካታ ደጋፊዎች ተከቦ በተመልካች በተሞሉ ስታድየሞች መጫወት የለመደው ይህ ተጫዋች አይረሴ የእግር ኳስ ሕይወቱን እርግፍ አድርጎ በመተው በጠባብ ፅህፈት ቤት ለሁለት ዓመታት ገደማ በሂሳብ ባለሞያነት መስራት ጀመረ። ቀስ በቀስ ከአዲሱ ሕይወቱ ጋር እየተላመደ ቢመጣም ድጋሚ ወደ እግ ኳስ የሚመልሰውን ዕድል ከወደ መቐለ መጣለት። በአቶ አሸናፊ ኃይሉ አማካኝነት በ1989 “ለቤት ምኽሪ ከተማ መቐለ” ( መቐለ ከነማ) ለማሰልጠን ተስማምቶ ዳግም ወደ ናፈቀው የእግር ኳስ ሜዳ ተመለሰ። “አሸናፊ ኃይሉ (አሁን የመቐለ 70 እንደርታ የቦርድ አባል) የአሰልጥንልን ጥያቄ ስያቀርብልኝ ደስ ነው ያለኝ ለቅዱስ ግዮርጊስ አስፈቅዱ እንጂ ፍቃደኛ ነኝ አልኩት። ክለቡም በህጋዊው መንገድ ጥያቄ አቅርቦ ለተወሰነ ጊዜ የዓመት እረፍት አውጥቼ በነፃ አገልግሎት ክለቡን በጊዝያዊነት ተረክቤ ለውድድር ወደ ድሬዳዋ ሄድኩ። በውድድሩም ጥሩ ውጤት አምጥተን ሙሉ ለሙሉ ወደ አሰልጣኝነት ገባሁ። ከዛ በኃላም በርካታ ስልጠናዎች ወስጄ አሁን ላለሁበት ደረጃ ደርሻለው። ”
ከሰማንያዎቹ መጨረሻ የጀመረው የገብረመድኅን የአሰልጣኝነት ሕይወት አሁንም ድረስ የዘለቀ ሲሆን በዚህ ወቅት በሀገሪቱ ውጤታማ ከሆኑ አሰልጣኞች መካከል ይመደባል። በትራንስ ኢትዮጵያ፣ ባንኮች፣ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ አል-ቲላል መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ ፸ እንደርታ ክለቦች አሰልጥኖ በተከታታይ ዓመታት የፕሪምየርሊግ ዋንጫን ያነሳ ብቸኛ አሰልጣኝ ሆኗል። ብሔራዊ ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት አገልግሎ በተጫዋችነት ያነሳው የሴካፋ ዋንጫን በ1997 ሲያሳካ በ2008 ለአጭር ጊዜያት ዋናው ብሔራዊ ቡድንን መርቷል። በአሁኑ ወቅትም በመቐለ ፸ እንደርታ አሰልጣኝነት እየሰራ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!