“የሚያምንብህ አሰልጣኝ እና ክለብ ካገኘህ አቅምህን ማሳየቱ ቀላል ነው” ተስፈኛው አብዱልከሪም ወርቁ

ከከፍተኛ ሊግ አንስቶ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በሊጉ ካየናቸው ባለ ክህሎት እና ወደፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው የአጥቂ አማካይ ተጫዋቾች መካከል የወልቂጤ ከተማው አብዱልከሪም ወርቁ ይገኝበታል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን እንብዛም መመልከት አልያም ዕድል መስጠት አዳጋች በሆነበት ጊዜ ውስጥ ለብዙ ክለቦች ምሳሌ በሚሆን መልኩ ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል መስጠት ጠቀሜታው ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ከሚያሳዩ ተጫዋቾች መካከል በሰውነቱ አነስ ያለው አብዱልከሪም ወርቁ አንዱ ነው።

ጉልበት ሳይጠቀም በአዕምሮ ቀድሞ ይጫወታል፣ ባለ ክህሎት ነው፣ ኳሶቹን በትክክል ለቡድን አጋሮቹ ያቀብላል፣ ጎል ያስቆጥራል፣ ለጎል የሚሆኑ እድሎችን ይፈጥራል። ይህ ወጣት ኳሰኛ የተወለደው አዲስ አበባ ልደታ ሠፈር ልዩ ስሙ ቢሪሞ ሜዳ አካባቢ ነው። በዚህ ታሪካዊ ሜዳ እግርኳስን መጫወት የቻለው አብዱልከሪም በኒያላ ሲ ቡድን የልጅነት እግርኳስ ዘመኑን ጅማሬ በማድረግ ነበር በ2009 ወደ ኢትዮጵያ መድን ቢ ቡድን ገብቶ እስከ ዋናው ቡድን ደረስ መጫወት የቻለው። በ2011 ወደ ወልቂጤ በማምራት ለዓመታት ወደ ሊጉ ለመቀላቀል የነበራቸውን ህልም ካሳኩ በእድሜው ትንሹ ተጫዋቾች ከመሆኑም ባሻገር ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ወደ ስምንት የሚሆኑ ጨዋታዎችን መጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ መካተት ችሏል። በተቀሩትን ጨዋታዎች ደግሞ ተቀይሮ በመግባት አቅሙን አሳይቷል።

ምንም እንኳን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ለኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ምርጫቸው ባያደርጉትም በመጀመርያ ጥሪ ውስጥ በማካተት ጥሪ ማድረጋቸው በልጁ ውስጥ የሚያድግ፣ ተስፋ የሚጣልበት አቅም እንዳለው ማሳያ ነው። ይህም ቢሆን ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወቱ ይታወሳል። በአሰልጣኝ ደግአረግ በሚመራው ወልቂጤ ከተማ በቀጣይ ክለቡን በተሻለ እንዲያገለግል እምነት ተጥሎበት ለተጨማሪ ሁለት ዓመት እንዲቆይ በቅርቡ ውሉን ማራዘሙ ይታወቃል። አብዱልከሪም ወርቁ በዛሬው የተስፈኞች ገፅ አምዳችን እንግዳ በመሆን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” በስም አላውቃቸው እንጂ ለብዙዎች እግርኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ እንደሆነ በማውቀው በቢሪሞ ሜዳ ነው እንደማንኛውም ልጅ እግርኳስን ስጫወት ያደኩት። በኒያላ ሲ ቡድን ለአንድ ዓመት ስጫወት ቆይቼ በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መድን ከታዳጊ ቡድን አምርቼ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለሦስት ዓመት መጫወት ችያለው። ያው አብዛኛውን ሰው ተክለ ሰውነት ቁመናን የሚመለከት መሆኑ እድሜህ ካልገፋ በእኛ ሀገር ተመራጭ አያደርጉህም። በዚህም ምክንያት ቶሎ ለማደግ ተቸግሬ ነበር። ሆኖም ግን የሚያምንብህ አሰልጣኝ እና ክለብ ካገኘህ አቅምህን ማሳየቱ ቀላል ነው። አጋጣሚ ሆኖ አሪፍ አሰልጣኝ ደረጄ በላይን አግኝቼ ይዞኝ ወደ ወልቂጤ መሄዱ አቅሜን አውጥቼ እንድጫወት ረድቶኛል። በከፍተኛ ሊግ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፌለው። ስምንት ጎሎችንም በስሜ አስመዝግቤ ቡድኑንም ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር የምችለውን አድርጌአለው። ዓምናም ለፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዲስ በመሆኔ እየወጣው እየገባው ተጫውቻለው። ፕሪሚየር ሊጉ ከከፍተኛ ሊግ ብዙም የተለየ ነገር አላየሁበትም ዕድል ከተሰጠ እምነት ከተጣለብህ መጫወት ትችላለህ። በብሔራዊ ቡድን ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተመርጬ ተጫውቻለው። ዓምናም አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ለኦሊምፒክ ቡድን የመጀመርያ ጥሪ አድርገውልኝ በኃላ ቀንሰውኛል። ይህም በመሆኑ ደስተኛ ነኝ። መጠራቴ በራሱ ወደ ፊት ዕድሉን ላገኝ እደምችል አመላክቶኛል። ጠንክሬ በመስራት ሀገሬን በትልቅ ደረጃ ማገልገል እፈልጋለው።

መስዑድ መሐመድ በጣም የማደንቀው፣ የማከብረው ተጫዋች ነው። በአካል አግኝቼው፣ አወርቼውም ባላቅም ሁሌም በእግርኳስ ህይወቴ ምሳሌ የማደርገው እርሱን ነው። ፈጣሪ ብሎ ኮሮናም ጠፍቶ ውድድሩ ከተጀመረ የተሻለ ነገር አሳይቼ በትልቅ ደረጃ መጫወት እፈልጋለው። ከዚህም አልፎ ከኢትዮጵያ ውጭ የመጫወት ህልም አለኝ። ከሠራህ፣ ከጣርክ የምታስበውን የማታገኝበት ምንም ምክንያት የለም። ወልቂጤ ከበቂ በላይ የመጫወት እድል ስለሰጠኝ፣ በኔም እምነት በመጣሉ በጣም አድርጌ ክለቡን አመሰግናለው። በተለይ አቶ አበባው ሰለሞንን አመሰግናለው። ከዚህ በተረፈ እዚህ ለመድረሴ ትልቁን ድርሻ የምሰጠው የማመሰግነው አሰልጣኝ ደረጄ በላይን ነው። በመቀጠል ከሰፈር በልጅነቴ ጎትቶ እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን ያደረገኝ ዓለማየሁን አመሰግናለው። እነዚህ ሁለት ሰዎች በህይወቴ ትልቅ ቦታ አላቸው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!