በዛሬው የይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ኮከቦችን የተመለከተ ተከታይ ጥንቅር ይዘን ቀርበናል።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች ተብለው ጣምራ ሽልማት በአንድ የውድድር ዓመት ያገኙት ተጫዋቾች ሦስት ብቻ ናቸው። እነርሱም አዳነ ግርማ (2003)፣ ጌታነህ ከበደ (2005) እና ዑመድ ኡኩሪ (2006) ናቸው።
– የኮከብ ተጫዋችነት እና ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን ከአንድ ጊዜ በላይ በማሸነፍ ብቸኛ ባለታሪክ ጌታነህ ከበደ ነው። ጌታነህ የኮከብ ተጫዋችነት ክብርን በ2001 እና 2005 ሲወስድ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ደግሞ በ2003፣ 2005 እና 2009 አሸንፏል።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውጪ ዜጋ ሆነው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን ክብር ያገኙት ተጫዋቾች ሁለት ናቸው። እነርሱም ሳሙኤል ሳኑሚ (2007/ደደቢት/22) እና ኦኪኪ አፎላቢ (2011/ጅማ አባ ጅፋር/23) ናቸው።
– በ22 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ 13 ክለቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች አስገኝተዋል። ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎቹ የተገኘባቸው ክለቦችም ኢትዮጵያ መድን፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አርባምንጭ ጨጨ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መብራት ኃይል፣ ምድር ባቡር፣ ወንጂ ስኳር፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ናቸው።
– በአንድ የውድድር ዓመት ከሊጉ የጨዋታ ብዛት አንፃር በርካታ ኳሶችን ከመረብ አገናኝቶ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ተጫዋች ዮርዳኖስ ዓባይ ነው። ዮርዳኖስ በ1993 በተደረጉ 26 የሊጉ መርሐ-ግብሮች 24 ጎሎችን አስቆጥሮ ነው ይህንን ሪከርድ የያዘው።
– በተቃራኒው ከዓመቱ የጨዋታ ብዛት አንፃር ትንሽ ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው ያጠናቀቁ ተጫዋቾች የተገኙት በ1996 ነው። በዚህ የውድድር ዘመን 13 ግቦችን አስቆጥረው ያጠናቀቁት አህመድ ጁንዲ (ከሀዋሳ ከተማ)፣ ታፈሰ ተስፋዬ (መብራት ኃይል)፣ ቢኒያም አሰፋ (ወንጂ) እና መሳይ ተፈሪ (አርባምንጭ) ናቸው።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾችን ያስገኘው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። በእነዚህ 22 ዓመታት ከክለቡ ስድስት ተጫዋቾች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ተገኝተዋል። እነሱም አሸናፊ ሲሳይ (1991/በ11 ጎሎች)፣ ስንታየሁ ጌታቸው (1992/በ15 ጎሎች)፣ ሳልሃዲን ሰዒድ (2000/በ21 ግቦች)፣ አዳነ ግርማ (2003/በ20 እንዲሁም 2004/በ23 ጎሎች) እና ዑመድ ኡኩሪ (2006/በ15 ጎሎች) ናቸው።
– በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾችን ያስገኘው ክለብ መብራት ኃይል ነው። ይህ ክለብ በ1993፣ 1994፣ 1995 (ግማሽ ዓመት) ዮርዳኖስ ዓባይን እንዲሁም 1996 ላይ ታፈሰ ተስፋዬን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት አስመርጧል።
– በኢትዮያ ፕሪምየር ሊግ ላይ 16 (ሀሰን በሽር፣ በረከት ሃጎስ፣ አህመድ ጁንዲ፣ አሸናፊ ሲሳይ፣ ስንታየሁ ጌታቸው፣ ሳልሃዲን ሰዒድ፣ አዳነ ግርማ፣ ዑመድ ኡኩሪ፣ ዮርዳኖስ አባይ፣ መሳይ ተፈሪ፣ ቢኒያም አሰፋ፣ መድሃኔ ታደሰ፣ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ፣ ኢኪኪ አፎላቢ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል) ተጫዋቾች ከ13 ክለቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው አጠናቀዋል።
– በሊጉ በተለያዩ ጊዜያት የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እና የኮከብ ተጫዋችነትን ክብር ያገኙት ተጫዋቾች ስድስት ናቸው። እነሱም አህመድ ጁንዲ (1991 ኮከብ ተጫዋች፣ 1995 እና 1996 ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ)፣ ታፈሰ ተስፋዬ ( 2000 ኮከብ ተጫዋች ፣ 1996፣ 1998፣ 2001፣ 2002 እና 2008 ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ)፣ አዳነ ግርማ (2003 ኮከብ ተጫዋች፣ 2003 እና 2004 ከፍተኛ ግን አስቆጣሪ)፣ ጌታነህ ከበደ (2001 እና 2005 ኮከብ ተጫዋች፣ 2003፣ 2005፣ 2009 ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ)፣ ዑመድ ኡኩሪ (2006 ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ) እና ቢኒያም አሰፋ (1998 ኮከብ ተጫዋች፣ 1996 ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ) ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!