☞ሀያ አራት ዓመታት የተሻገረ የድጋፍ ጉዞ …
☞ “የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ነው በሚል ከመጀመርያ አሰላለፍ የወጣሁበት አጋጣሚ አለ”
☞ “2002 ላይ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፊርማዬን አኑሬ ነበር”
☞ “እኔ እስከ አሁን ብዙ ደስታዎች አግኝቻለሁ፤ የ2003 ያህል ደስታን ግን አግኝቼ አላውቅም”
በኢትዮጵያ እግርኳስ ረጅም ዓመታት የዘለቀ የደጋፊነት ቆይታው ጉልህ ስም ካላቸው ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳል።፡ ተጫዋች የመሆን ህልሙን በትንሹ ማሳካት ቢችልም ጉዳት ግን ረጅም ጉዞን አላስኬደውም። ከጎላ ሚካኤል የጀመረው የክለብ ህይወቱ ኢትዮጵያ ባንኮች (ንግድ ባንክ) እና ኒያላ ድረስ ዘልቋል፡፡ 2002 ላይም ለኢትዮጵያ ቡና ለሁለት ዓመት ለመጫወት ፊርማውን አኑሮ የነበረ ቢሆንም ከዝግጅት ያለፈ ዕድሜ ግን አልነበረውም፤ ጉዳቱ በድጋሚ አገረሸበትና የሚወደውን ክለብ ኢትዮጵያ ቡና በመጫወት ማሳለፍ ባይችልበትም በድንገት መደገፍ ጀምሮ እነሆ ላለፉት ሀያ አራት ዓመታት የልብ ደጋፊ ሆኖ ዘልቋል። የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖም ሰርቷል፡፡ ከእግር ኳሱ ውጪ በበጎ ተግባራት ቀዳሚ እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን በኮሮና ወረርሽን ወቅት ከወዳጆቹ ጋር ያደረገው የገቢ ማሰባሰብ እና የአሸናፊ በጋሻውን የእውቅና ፕሮግራም ካሰናዱት መካከልም ስሙ አለ። የዛሬው የደጋፊዎች ገፅ እንግዳ የኢትዮጵያ ቡናው ደጋፊ አብዱራህማን መሐመድ (አቡሸት) ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል። ተከታተሉን፡፡
በቅድሚያ ለደጋፊዎች ገፅ እንግዳ ስለሆንክ ከልብ አመሰግናለሁ። እስቲ በቅድሚያ የት ተወለድክ ? ዕድገትህስ ምን ይመስላል ከሚለው እንጀምር ?
በመጀመሪያ ለዚህ በጣም ለምወደው እና ደስ በሚለኝ ደሞም ሁሌ በምከታተለው የሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገፅ እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ነው፡፡ በተለምዶ አሜሪካን ጊቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ትውልድ እና ዕድገቴ፡፡
እግርኳስ ተጫዋች እንደነበርክ እና ተስፋም ተጥሎብህ በጉዳት ከጨዋታ ዓለም እንደወጣህ ሰማሁ። እስቲ መለስ ብለህ ስለ ተጫዋቾችነት ጊዜህ ብናወራ ?
ያው እግር ኳስ እንደማንኛውም ሰው በሰፈር ተጫውቼ አልፌያለሁ። እኛ ሰፈር (ተክለሃይማኖት አካባቢ) የተመሠረተ ጎላ ሚካኤል የሚባል ቡድን ነበር፡፡ እዛ ነው እግርኳስን የጀመርኩት። በአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን በዚህ ቡድን ውስጥ ተጫውቻለሁ፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በካሳዬ አራጌ ለሚሰለጥነው ተስፋ ለኢትዮጵያ ወደሚባል ቡድን ነው አምርቼ ለሁለት ዓመት ያህል ተጫውቻለሁ። ተስፋ ለኢትዮጵያ በነበረ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ በብዙ ቡድኖች የመታየት ዕድሉን አግኝቼ ነበር። ቦሌ አካባቢ አንድ ሜዳ ላይ እነ ሸዋረጋ እነ አሰግድ ተስፋዬ ብዙ ተጫዋቾች በነበሩት ጨዋታ ላይ አሰልጣኝ ሮማሪዮ ነበር የወሰደኝ። እዛ ባደረኩትም ጨዋታ አይተውኝ ብዙ ክለቦች እንውሰድህ ብለውኝ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ እንደውም ቅዱስ ጊዮርጊስ እነ ኢትዮጵያ ቡና ነበሩበት ፤ ግን በቃ ለዕድገትህም ለማንኛውም ነገር የሚሻልህ ባንኮች ነው ተብዬ ወደ ባንክ ነበር ያመራሁት። ገብረመድህን ኃይሌ ነበር በጊዜው አሰልጣኙ። በባንክም ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ስጫወት ቆይቻለሁ፡፡ በወቅቱም ትንሽ ጉዳትም መጣና ወደ ማቆሙ ደረስኩ። ግን በዚህ መሀል በይልቃል አማካኝነት ወደ ኒያላ አንደገና ገባሁና ግማሽ ዓመት ተጫወትኩ። የተጫዋችነት ዘመኔ ይሄን ይመስላል፡፡
የተጫዋችነት ዘመንህን ብዙዎች አያውቁም። በደንብ የምትታወቀው እንደውም በኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊ ሆንህ ነው፡፡ የአቡሸት እና የኢትዮጵያ ቡና ቁርኝት መቼ ተጀመረ ? እንዴትስ ወደ ድጋፉ ዓለም ተቀላቀልክ ?
የሚገርምህ በጣም እኔ ህፃን ሆኜ አንድ ጓደኛዬ አለ፤ ወሊድ የሚባል አሁን የመን ነው የሚኖረው። እና ከእርሱ ጋር ከጊዮን እየተመለስን ስታድየም ውስጥ ሲጮህ ሰምተን እንግባ ተባብለን ገባን። በጣም ህፃን ልጆች ነበርን በሰዓቱ። ኤልፓ እና ቡና ነበር ለ1989 ጥሎ ማለፍ ዋንጫ የሚጫወቱት። በአጋጣሚ በኤልፓ በር ነበር የገባሁት። ከዚያ ጊዜ በኃላ ነው በቃ የኢትዮጵያ ቡና ፍቅር የሳበኝ። በመቀጠል ደግሞ እስከ ማስጨፈር ደረጃ ደረስኩ። ለክለቡ ትልቅ አስጨፋሪ ከሚባሉት ደረጃ ውስጥ ደርሼ ነበር። ጥላ ፎቅ በሙሉ የእኛ ሰፈር ሰው ስለሚገባ ሁሉም ያው ቀኝ ነበር። እናም በማስጨፈር ነው መጀመሪያ ወደ ክለቡ የተቀላቀልኩት። እንደውም ክለብ ገብቼ ሁሉ ደጋፊም ነበርኩ። በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልንገርህ። ባንክ እያለሁ ጨዋታው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነበር የሚደረገው። እኔም የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ገብቼ ሁሉ ለመጫወት ገብቼም የተሻለ ነገር ለማሳየት ጓጉቼ ነበር። መጨረሻ ላይ ሜዳ ገብተን አሰላለፍ ተነግሮን አሟሙቀን ወደ መልበሻ ከተመለስን በኃላ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ነው በሚል የወጣሁበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይኸው አሁንም ለረጅም ዓመት የክለቡ ደጋፊ ሆኜ አለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን እንደ ማንኛውም ደጋፊ ሆነህ ብትገባም እስከ ደጋፊ ማኅበር አመራርነት ደርሰሀል። ከዚያም ባለፈ ደግሞ ክለቡን በሚመለከቱ ማናቸውም ጉዳዮች ውስጥ አቡሸት ቀድሞ ይደርሳል ይባላል … እስቲ ስለ ደጋፊ ማኅበር ኃላፊነትህ ወደ ኃላ ተመልሰን እንጫወት ?
መጀመሪያ በ2002 ላይ አንድ የመረዳጃ ጨዋታ ነበር። ደጋፊው ከነአሰግድ ፣ ኩኩሻ እና አንዳርጋቸው ከመሳሰሉት ጋር የተደረገ ጨዋታ ነበር። እዛ ጨዋታ ላይ ባደረኩት እንቅስቃሴ ብዙዎች ይሄ ተጫዋች ነው ወይንስ ምንድነው ብለው ያወሩ ነበር። ያን ጨዋታ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኦኔራ ያይ ነበር መሰለኝ። የፌስቲቫል ጨዋታ ቢሆንም እኔንም እስከ መመረጥ ደረጃ ተደርሶ ነበር። በዚያ ጊዜ በነበረኝ ቆይታ ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት አለበት በሚል 2002 ላይ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፊርማዬን አኑሬ ነበር፡፡ ለሁለት ዓመት ፈርሜ ዝግጅት በደንብ ጀምሬ ጉዳት አጋጠመኝና ወደ ሳውዲ ለህክምና ሄድኩ። እዛ ጨርሼ መጣሁ በድጋፉም ቀጠልኩ። በዛኑ ዓመት መጨረሻ ላይ ሂልተን ሆቴል ስብሰባ ነበር። እዛም ላይ የደጋፊ አመራር ሆኜ ተመረጥኩ። ገደኛም ነበርን በሰዓቱ ከ2003 አዲስ አመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማኅበር ምክትል ሆንኩ። በዛን ወቅት ደስ በሚል ሁኔታ ሁላችንም ሙሉ ስራችንን በኢትዮጵያ ቡና ላይ አደረግን። ከተጫዋቾችም ፣ ከአሰልጣኝም፣ ከክለቡ ቦርድ አመራርም ጋር በጣም ደስ የሚል ፍቅር ነበረን። ያም ውጤት እንዲገኝ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የራሴን አስተዋጽኦ አበረከትኩ። ቢያንስ ለስድስት፣ ለሰባት ዓመታት የምወደውን ክለብ ደስ ብሎኝ አገልግያለሁ። በመጫወቱ ክለቡን ባላገለግልም በአመራርነት ሁሌም ከክለቡ ጎን በመሆን እስከ አሁንም አለው ማለት ነው።
ስለ 2003 ቅድም በንግግርህ ደስ የሚል ጊዜ እንደነበር ነካክተኸው ነበር። እንደ አንድ ረጅም ጊዜን እንዳስቆጠረ ደጋፊ በወቅቱ ቻምፒዮን ስትሆኑ ምን ተሰማህ?
እኔ ትንሽ የቆጨኝ እግር ኳስ ተጫዋች ሆነህ ይሄን ደጋፊ ስታየው በጣም ትገረማለህ። ባስደስተውስ ብለህ ትመኛለህ። ሁሌም የሚቆጨኝ በተጫዋችነት ዘመን ተጫዋች ሆኜ ባገኘሁ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሁሌም ሚፀፅተኝ ነገር በእግር ኳስ ህይወቴ ኢትዮጵያ ቡናን ተጫዋች ሆኜ አለማገልገሌ ነው፡፡ ግን በ2003 በነበረው የዋንጫ ድላችን እኔ እስከ አሁን ብዙ ደስታዎች አግኝቻለሁ። ያን ያህል ደስታን ግን አግኝቼም አይቼም አላውቅም። ሁለተኛም ውስጡ ስለነበርኩ የነበረው ፍቅር የነበረው መተሳሰብ አስገራሚ ነበር። እንደ ወጣትም እንደ ኳስ ተጫዋችም ዓይነት ባህሪም ስለነበረን ወደ ላይ የሚሄዱ ችግሮችን እዛው እየፈታን ለዚህ ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱም ጥሩ አመለካከት ስላለው እዛው እየቀጨን በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር የነበረው። እኔ እንደዛ ጊዜ ደስታ እስከ አሁንም አጋጥሞኝ አያውቅም። በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ግን ያን የመሰለ ደስታ ተፈጥሮ አይታወቅም። በመላ ሀገሪቱ ሥራ እስከማይኖር ድረስ የፈጠረ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ የፈጠረብኝ ደስታ የሚገለፅ አይደለም የእኔም የመጨረሻው ደስታ ያቺ ናት፡፡ ግን ደግሞ ያቺን ብቻ ዋንጫ እያሰብን እስከ አሁን አለማግኝታችንም ደግሞ የማዝንበት ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ቡና ከ2003 በኃላ ድጋሚ ዋንጫን ለማግኘት ሲቸገር ተመልክተነዋል። ሌላው ደግሞ የተለያዩ አሰልጣኞች ወደ ክለቡ በመምጣታቸው የክለቡ የአጨዋወት መንገድም የዛኑ ያህል ሲለዋወጥ እያስተዋልን ነበር። ከዓምና ጀምሮ ግን በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እየተመራ በዘጠናዎቹ የሚታወቅበትን የጨዋታ ፍልስፍና ይዞ ብቅ ብሏል። አንተ በክለቡ ውስጥ እንደቆየ ሰው ምን ተሰማህ ?
በነገር ላይ በዚህ አጨዋወት ውስጥ እኔም አልፌያለሁ። ከአሰልጣኝ ካሳዬ ጋር በተስፋ ለኢትዮጵያ አይቼዋለሁ። በሚያሰለጥንበትም ጊዜም ሁሉንም ጨዋታ የመከታተሉን ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህም እንቅስቃሴው ትንሽም ቢሆን ይገባኛል ብዬ አስባለሁ። ደግሞም የማምንበት፤ ሊሆን ይገባልም ብዬ የማስበው ፍልስፍና ይሄ ነው፡፡ ይሄን ፍልስፍና ለማስረፅ መታገስ ይገባል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ቡና ዐምና በያዛቸው ልጆች ማንም ሰው አልጠበቀም ነበር። ሁሉም ሊወርድ ይችላል ብሎ ፍርሀት ይዞት ነበር። ግን ተጫዋቾቹ የነበረውን እንቅስቃሴ እና የጨዋታው መንገድ እስኪገባቸው ድረስ ጊዜ ይፈጅብሀል እንጂ ምንም ዓይነት ስጋት ሳይኖርብህ ደስ እያለህ እና ደጋፊውን እያስደሰትክ ውጤት የምታገኝበት እንቅስቃሴ ነው ብዬ አስባለሁ። ይሄም ነገር ደግሞ በደንብ ለመተግበር ክለቡ መታገስ መቻል አለበት። ካሳዬ እንደሌሎች አሰልጣኞች ረጅም ልምድ ላይኖረው ይችላል። ግን እሱ የሚያስባቸውን ነገሮች የሚፈልጋቸውን ነገሮች እያደረግን ከጎኑ ሆነን መታገስ አለብን። ማገዝም መቻል አለብን። አሁን ባለው ነገር እየታገዘም ነው ብዬ አላስብም። የሚፈልጋቸውን ተጫዋቾችም ሆነ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማመቻቸት ይኖርብናል። ይሄ እልህ የመጋባት ነገር መኖር ሳይሆን ያለውን ሙሉ ነገር አቅርበንለት ሙሉ ነገር አድርገንለት ከዛ በኃላ ውጤት ከጠፋ ለመጠየቅም ሆነ ለምንም የሚያመቸው አሰልጣኙ የሚፈለገውን ስናዘጋጅለት ብቻ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ያሉን ተጫዋቾች በሙሉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ክለባችንን ጠቅሞልናል፡፡ ከወጪ አንጻር እኛም ሀገሪቱም ብዙ ተጠቃሚዎች ነን። ሁለተኛ ከብዙ ዓመት በኃላ ነው ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት እና ከስድስት ተጫዋቾች በላይ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ሲችል። በፊት አንድ የማይመረጥበትም ወቅት ነበር። ሌላው ሸሽቶ የነበረውም ደጋፊ ቢያንስ ትንሽ ብልጭ ያለ ነገር አይቶ እየተመለሰ ነው። አንድ ያደረገንም የጨዋታ እንቅስቃሴ ነውና ለእርሱ እገዛ ማድረጋችንን መቀጠል አለብን። በደጋፊም በቦርድ አመራርም በእኛ ገለልተኛ ደጋፊዎችም ቢሆን ሁሌ ከጎኑ ሆኑን መርዳት መቻል አለብን። መጠየቅም ሆነ መፍረድ ያለብን ከውጤት በኃላ ነው። አራት ዓመት ተሰጥቶታል፤ በመጀመርያ ዓመቱም የተሻለ ነገር አይተንበታል። የሰራው ነገር እንዳይፈርስበት ያለንን ጠብቆ የሚፈለገውን አቅርበንለት የተሻለውን እንቅስቃሴ እናያለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ለዘንድሮ የውድድር ዓመት ቅድመ ዝግጅት ከተጫዋች ምርጫ ጋር በተያያዘ ሆነ እከሌ ካልመጣ… እከሌ ይምጣ… የሚሉ አላስፈላጊ ንትርኮች አሉ ሲባል በተደጋጋሚ እየሰማን ነው። እነኚህ ውንዥንብሮች እየሰፉ ሲመጡ በዘንድሮው የክለቡ ጉዞ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አይኖረውም ብለህ ታስባለህ ?
እነዚህ ነገሮች በጣም መቀረፍ ያለባቸው ነገሮች ናቸው። ጥፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥፋቶችን ተመካክሮ ሊፈቱ የሚችሉበትንም መንገድ ከአሰልጣኙም ጋር ከቦርድ አመራርም ጋር ከደጋፊ ማህበርም ጋር ሆኖ በጋራ መፍታቱ ነው የሚሻለው። አንዳንድ ደጋፊዎች ከእከሌ ጋር ተጣልተናል እንዲህ ማድረግ አለብን በሚሉት ወሬ ክለብ መጨነቅ የለበትም። አሰልጣኙ የሚፈልጋቸውን ተጫዋቾችም ሆነ ሌሎች ነገሮች መሟላት ነው ያለበት። ለመጠየቅም የሚያመችህ አሰልጣኙ ያቀረባቸውን ነገሮች ካሟላህለት በኃላ ነው። እኔ በግሌ የማስበው ያሉባቸውን ችግሮች ተመካክረው ሊፈቱ ይገባል ብዬ ነው። ያው ከውጪ ሆነህ የምትሰማው ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ነው። እኔ በበኩሌ የማምነው እንዲሆንም የማስበው አሰልጣኙ ኃላፊነት እስከተሰጠው ድረስ ባመነባቸውና ይሆኑኛል ባላቸው ነገሮች እንዲቀጥል በማድረግ ነው። ከክለቡ ጋር ችግር ያለባቸው ሰዎችም ካሉ ተነጋግረው የሚፈቱበት መንገድ ተፈጥሮ ቢፈታ ይሻላል ባይ ነኝ። በዚህ ሁኔታ ነገ ውጤት ቢጠፋ ለመተቸት አይመችም። ቆጥረህ የሰጠህውን ድጋሚ ለመቀበል ምንም አይቸግርህም። ባልሰጠህው ነገር ግን ለመቀበል ከባድ ይመስለኛል። እንደዚህ ዓይነት ወሬዎች በዚህ ትልቅ ክለብ ውስጥ መሰማትም አልነበረበትም። ያሉትን ችግሮች ግን ከአሁን በኃላ መፍታት ይሻላል፡፡ እኛ እንደ ደጋፊ መደገፍ ነው ስራችን። አሁንም ለመደገፍ እኔ ዝግጁ ነኝ፡፡
ክለቡ አቡበከር እና ሚኪያስን አምስት ዓመት፣ አማኑኤል ዮሀንስን አራት ዓመት እና አዲስ ፈራሚው ዘካሪያስ ቱጂን ሦስት ዓመት ኮንትራት በመስጠት ዳግማዊ አሸናፊ በጋሻውን ለመፍጠር ያለመ ተግባር ሲፈፅም እንደ አንድ ደጋፊ ምን ተሰማህ ?
ብዙውን ጊዜ አዳዲስ ነገሮች የሚጀመሩት በኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ ይሄ ነገር ደግሞ በእኛ ክለብ አሁንም ሆኖ በማየቴ እኔ በራሴ ደስተኛ ነኝ። እንዲሆኑም ከምፈልጋቸው ነገሮች መሀል አንዱ ይህ የዝውውር አካሄድ አንዱ ነው። በእኛ የአሸናፊ በጋሻው ፕሮግራም ላይ አቡኪ እና ሚኪ ተገኝተው ነበር። እንደ አሸናፊ መሆን አለባችሁ ረጅም ጊዜም በክለቡ መቆየት ይኖርባችዋል ብለን ተነጋግረን ነበረና ቃል እንዲገቡም የተደረገበት ሁኔታ ነበር። እና ያን ነገር ክለቡ አመቻችቶ በማየቴ ኮርቻለሁ። ልጆቹም በጣም ደስተኛ ሆነዋል ከሚገባው በላይ። እና እኔ የምደግፈውም ሊሆን ይገባልም የምለው ይሄንን ነው። አሁን የውጪ ዕድል እንኳን ቢመጣ ቡና ከእነ አቡኪ፣ ሚኪ፣ አማኑኤል ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ አለ። ሌላ የተሻለ የኢትዮጵያ ክለቦች ደግሞ ከእኛ በልጠው የተሻለ ገንዘብ ካቀረቡ ክለባችን ትርፋማ ይሆናል። የዝውውር ሂደቱም ማስጀመሪያ ይሆነናል የሚልም እምነት አለኝ። ይሄ ነገር አንድ በኢትዮጵያ ቡና እንደዚህ ዓይነት ውል በመጀመሩ በጣም ደስ ብሎኛል። ሁለት ደግሞ በጣም የምደግፈው የኮንትራት አማራጭ ነው፤ ልጆቹን ተጠቃሚ የሚያደርግም ነው። ሌላው ደግሞ ክለቡንም ተጠቃሚ የሚያደርግም ስለሆነ በዚህ አካሄድ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ደምቀው ከሚታዩ ደጋፊዎች መካከል የቡና ደጋፊዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የቡና ደጋፊዎችን እንዴት ትገልፃቸዋለህ ?
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ለእኔ ቤተሰብ ነው አሁንም ድረስ ለእኔ ቤተሰቦቼ ሆነዋል። ከወንድም እና እህቶቼ በላይ በዙሪያዬ ብታየኝ 90 ፐርሰንት የቡና ሰው ነው ያለው። በጓደኝነትም በሁሉም ነገሬ ዙሪያዬ ያለው የኢትዮጵያ ቡና ሰው ነው፡፡ በየሄድክበት በየሰፈሩ በመስሪያ ቤት ከትልልቅ ሰውም ጋር ያገናኘኝ ኢትዮጵያ ቡና ነው። በቃ ለእኔ የኢትዮጵያ ቡና የሆነ ሁሉ ቤተሰቤ ነው፤ የቤተሰቤ አካል ሆኗል። በክፉ ብትል፣ በደግ ጊዜ፣ በደስታም ጊዜ ቅድም በነገርኩህ ቁጥር ልክ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ነው፡፡
በመጨረሻም ያው ሊጉ መጀመሩ አይቀርም። እንዲጀመርም የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ ከክለብህ ጋር የተያያዘም ሆነ የቀረኝ ነገረም አለ የምትለው አለ ?
በመጨረሻ መናገር የምፈልገው የመጣብንን መቅሰፍት አላህ እንዲያነሳልን እመኛለሁ። ሁለተኛ ዘንድሮ እኛ እንኳን ሜዳ ገብቶ መመልከት ባንችልም እንዴት እንደናፈቀን። የኳስ አለመኖር በጣም መጥፎ የሆነ ስሜት ውስጥ ነው የከተተን። ይሄ ኳስ ተመልሶ ደስታችንን የምናይበት እንዲያደርገን እመኛለሁ፡፡ ሌላው ያው ውድድሩ ተጀምሮ ያው በባዶ ስታድየም ነው የሚደረገው እየተባለ ነው። ይሄ ደግሞ ለክለባችን ጥቅምም አለው የተወሰነ ጉዳትም ይደርስብናል። ቡና አብዛኛው ህልውና ያለው በደጋፊው ስር ነው። የደጋፊ አለመኖር ትልቅ ጉዳት ይኖረዋል እና ትንሽ ፐርሰንት ደግሞ ተጫዋቾች እንቅስቃሴውን በደንብ ለመተግበር እንዲችሉና በነፃነት እንዲጫወቱ ያግዛቸዋል፡፡ በብዛት ወጣቶች ስለሆኑ የህዝብ የጩኸት ድምፅ ሲሰሙ ትንሽ ከእንቅስቃሴ የሚወጡ አሉ እና በዚህች ትንሽ ፐርሰንትም ቢሆንም እንጠቀማለን ባይ ነኝ። የእኛ ህልውና ደጋፊው ስለሆነ ተመልሶ የሚወደውን ቡድን የሚወደውን ድባብ እንዲያይ ምኞቴን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እፈልጋለሁ።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!