“ለኢትዮጵያ እግርኳስ አለማደግ ዋነኛው ችግር ታዳጊ ላይ አለመስራታችን ነው፡፡” ተብሎ በተደጋጋሚ የሚሰነዘር አስተያየት አሰልችቶናል፡፡ በእርግጥ የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በበቂ ሁኔታ አልሰራንም፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት በመንግስት ድጋፍ፣ በስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ በተለያዩ አሰልጣኞች አማካኝነት የተቋቋሙ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ነበሩ-አሁንም አሉ፡፡ ለሃገራችን እግርኳስ ዕድገት መፍትሄ እንደሚሆኑ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች ዛሬም የሚጠበቅባቸውን ማበርከት ተስኗቸዋል፡፡በዚህኛው ጽሁፌ በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ሥር ያለውን የታዳጊዎች ስልጠና ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
በቅርበት የማውቀው እና በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሸን የሚመራው የታዳጊዎች ስልጠና በ1990 ዎቹ መጀመሪያ ስራውን እንደጀመረ ይታወቃል፡፡ በተለይም እኔ በተሰማራሁበት የእግርኳስ ሥልጠና ዘርፍ በደካማ አመራር እና በኋላ-ቀር የስልጠና ሥርዓት ሳቢያ ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡ ለፕሮጀክቱ ከሚመደበው በጀት እንዲሁም ከሚወጣው ወጪ አንጻር ብቁ ተተኪዎችን ሳያፈራ ላለፉት ሃያ ዓመታት በስራ ላይ ቆይቷል፡፡ በእርግጥ የአስተዳደራዊ መዋቅር፣ የአመራር ክህሎት፣ የእግርኳስ መሰረተ ልማት መሟላት እና የዘመናዊ ሥልጠና ችግር ያለበት የሃገራችን እግርኳስ ታዳጊዎች ላይ ብቻ ስለተሰራ ለውጥ ማምጣት የሚታሰብ አይሆንም፡፡ እንደውም በእኔ እምነት ለውጡ ከላይ መጀመር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ በሃገራችን በሁሉም ዘርፍ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ግልጽ ቢሆንም የእግርኳሱ ግን ከሁሉ የከፋ ይመስላል፡፡ ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠረው የሀገራችን የታዳጊዎች ስልጠና ከኢትዮጵያ እግርኳስ በደረጃቸው ከፍ ባሉ ሃገራት መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን ሊያፈራ ቀርቶ ለሃገራችን ክለቦች እንኳ በቂ ተተኪዎችን ማበርከት አቅቶት ይታያል፡፡ በክ/ከተሞችና በከተሞች ደረጃ የተቋቋሙት እነዚህ የታዳጊ ማሰልጠ ማዕከላት ውጤታማ ላለመሆናቸው በርካታ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንዲሁም በክፍለ ከተማ እና በከተማ የስፓርት ቢሮዎች ውስጥ የሚሰሩ ባለሞያዎች በአግባቡ ያልተሰራበት እና ውጤታማ ያልሆነውን የታዳጊዎች ስልጠና እንደ ማሳያ በማቅረብ በታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ መስራት ውጤት አያመጣም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ለመሆኑ እነዚህ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ለምን ውጤታማ መሆን አልቻሉም? ችግሮቹን እና የመፍትሄ ሃሳቦችን አያይዤ ላማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
1) ዘላቂ የሆነ ስልታዊ እቅድ አለመኖር
ያለ ጥልቅ እና በቂ ጥናት የተጀመረው ይህ የታዳጊዎች ስልጠና ከመነሻው ምን ማሳካት እንደሚፈለግበት በግልፅ ያስቀመጠ አልነበረም፡፡ዝርዝር እቅዶችም በደንብ ተጠንተው አልቀረቡበትም፡፡ ተገቢውን የስልጠና አካባቢ ከመምረጥ አንስቶ ለምልመላ፣ ክህሎት ለመለየት፣ ተሰጥዖን ለማጎልበት፣ የታቀደባቸው የልምምድ መርኃግብሮችን ለማዘጋጀት፣ የተለያዩ የሥልጠና ሃሳቦች በተግባር ለመሞከር እና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ዝግጁ የሆነ የረጅም ጊዜ ስልታዊ እቅድ አልተነደፈም፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነቶቹ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ሲወጠኑ የረጅም ጊዜ እቅድ ሊወጣላቸው ይገባል፡፡ የምልመላ፣ የስልጠና፣ የውድድር እና ክትትል ሂደቶችን በዝርዝር ያካተተ ዳጎስ ያለ የሰነድ ዝግጅትም ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስርዓተ-ስልጠና (Coaching-Curriculum) በማዘጋጀት ታዳጊዎቹ ተመሳሳይ ስልጠና የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት የግድ ይላል፡፡
2) አስተዳደራዊ ችግሮች
በርካታ ገንዘብ የሚባክንበት ይህ የታዳጊዎች የስልጠና ፕሮጀክት አስተዳደራዊ ችግሮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ለአሰልጣኞች ወርሃዊ አንድ ሺህ ብር ብቻ በደመወዝ መልክ መክፈሉ የመጀመሪያው ችግር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ተገቢ እና በቂ ደመወዝ የማይከፈላቸው እነዚህ አሰልጣኞች ማሰልጠኑን እንደ ትርፍ ስራ በመያዝ ሲፈልጉ የሚሰሩት ሳይፈልጉ ደግሞ የሚተውት ኃላፊነት እንዲሆን አድርገውታል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ የስልጠና መገልገያ መሳሪያዎች እጥረት ይታያል፡፡ ኳስን እና ኮኖችን ጨምሮ የተለያዩ የሥልጠና ግብዓቶች በአስፈላጊ ጊዜ አይቀርቡም፡፡ አልፎአልፎ ደግሞ በግዢ ክፍል ከስንት አንዴ የሚገዛውም ቢሆን የስልጠና ዓመቱ ሊጋመስ ሲቃረብ እደላው ይጀምራል፡፡ ገንዘብ መውጣቱ ካልቀረ ጥራቱን የጠበቀ መገልገያ መሳሪያ ግዢ ቢፈጸም ምናለበት! መገልገያ መሳሪያው ከተገኘ – የጥራት ችግር ያለበት አለበለዚያም በወቅቱ የሚደርስ አለመሆኑ የከፍተኛ አስተዳደራዊ ክፍተት ማሳያ ይሆናል፡፡ በተለይ በዚህ ባገባደድነው ዓመት በአንዳንድ የስልጠና ጣቢያዎች ከአስራ ሦስት ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች 43-ቁጥር ጫማ ገዝቶ መስጠትን የመሰለ ተግባርም ተፈጽሟል፡፡ ይህ በጣም አሳፋሪና ቸልተኝነትን የሚያመለክት ድርጊት ነው፡፡ አብዛኞቹ ይህንን የፕሮጀክት ስልጠና በበላይነት የሚመሩ እና የሚቆጣጠሩ አካላት በእግርኳስ ስልጠና ላይ በቂ እውቀት ስለሌላቸው ውጤትን የሚለኩት በዋንጫ ብቻ ይሆናል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ተገቢው ስልጠና ሳይሰጥ በዓመቱ መጨረሻ ለሚደረግ ውድድር ከየቤታቸው ተጫዋቾችን ጠርቶ ማሳተፍስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ይሆን?
3) የአሰልጣኞች ምልመላ እና ቅጥር
ለዚህ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ፍሬያማ አለመሆን ሌላኛው ተጠቃሽ ምክንያት የአሰልጣኞች ምልመላ እና የቅጥር ሁኔታ ነው፡፡ የታዳጊዎች ስልጠና እግርኳስ ተጫዋቾችን ከማፍራት አልፎ ነገ ሃገርን ለመረከብ የሚችሉ በአካልና በአዕምሮ ብቁ የሆኑ ዜጎችንም የማዘጋጂያ ቦታ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም እዚሁ ዘርፍ ውስጥ በእውቀት፣ በፍላጎት እና በስነ-ምግባር ደካማ የሆኑ አሰልጣኞች መስኩን ሲቆጣጠሩት ለመታዘብ ችለናል፡፡ በፍፁም የታዳጊዎች ስልጠና አካባቢ መድረስ የማይገባቸው አሰልጣኞች ደግመው-ደጋግመው ለማሰልጠን ሲመለመሉ እና ሲያሰለጥኑ መመልከት ልማዳችን ከሆነ ሰነበትበት በልልኝ፡፡
4) ምልመላ
በታዳጊ የእግርኳስ ስልጠና ምልመላ በጣም ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ ምልመላ ታዳጊው አሁን ላይ ያለውን እምቅ አቅም በመመልከት ከጥቂት ዓመታት በኋላ የት ሊደርስ እንደሚችል የመገመት ብቃት ነው፡፡ ስለዚህ በምልመላ ወቅት ይህንን እውነት ሳንረዳ ምንም አቅም የሌላቸውን ልጆች ከመለመልን ከዛ በኋላ የሚኖረው ልፋት ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡ በከተማው በዚህ የፕሮጀክት ስልጠና የተመለከትኩት አንዱ ችግር የምልመላ ሥርዓቱ አስተማማኝ አለመሆኑ ነው፡፡ በዚሁ ተሰዖን የመለየት ቀዳሚ ተግባር አለመስተካከል ምክንያት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተመልማዮች በእግርኳስ ረጅም ጉዞ ሳያደርጉ በአጭሩ ይቀራሉ፡፡ምልመላ ላይ ብዙ መስራት፣ የሌሎች ሃገራትን ተመክሮዎች ማጤን፣ ለሃገራችን ታዳጊዎች የሚመጥንና ሁሉን አካታች የምልመላ ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅብናል፡፡
5) ሥልጠና
ከላይ (ቁጥር-3) እንደጠቀስኩት ስልጠና በዋናነት ከአሰልጣኞች እና ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ይያዛል፡፡ በታክቲክ፣ ቴክኒክ፣ አካል ብቃት እና ስነ-ልቦና ዘርፎች በቂ እውቀት፣ ሰፊ ልምድ፣ የዳበረ ተመክሮ የሌለው አሰልጣኝ ተገቢውን ስልጠና ለታዳጊዎቹ ሊሰጥ አይችልም፡፡በሌላ በኩል አሰልጣኞቹ ብቁ ሆነው ቢገኙ እንኳ የሜዳ፣ የኳስ እና የኮን ችግሮች ለስልጠናው ደካማነት አሉታዊ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ጥንቃቄ በሚፈልገው የታዳጊዎች ስልጠና ልምምዱ ያለ በቂ እውቀት ከመሰጠቱ የተነሳ አንዳንድ ተስጦኦ ያላቸው ታዳጊዎች ተሰናክለው ቀርተዋል፡፡
6) ውድድር
ታዳጊ ተጫዋቾች በስልጠና ብቻ ሳይሆን በውድድርም ያድጋሉ፡፡ ደካማው የሥልጠና ስርዓት እንዳለ ሆኖ በዓመት አንድ ጊዜ እየተጠበቀ በሚካሄደው ውድድር ታዳጊዎቹ ቢበዛ አምስት ጨዋታዎች ብቻ የመጫወት ዕድል ቢያገኙበት ነው፡፡ በሒደቱ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ተመርጠው በመላው ኢትዮጵያ የፕሮጀክቶች ውድድር ይሳተፋሉ፡፡ ሃገር-ዓቀፉ ውድድር ሲደረግ ደግሞ አልፎአልፎ የማጭበርበር ተግባራትን የመምረጥ አዝማሚያዎች ይታያሉ፡፡ በፕሮጀክት ስልጠና ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸውን ተጫዋቾች በመምረጥ-ከክለቦችም ጭምር እየወሰዱ በውድድር ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋሉ፡፡በሃገራችን የታዳጊዎች ስልጠና ውጤታማነት በዋንጫ ብቻ መለካቱ ለዚህ ብልሹ አሰራር ዳርጎናል፡፡
እነዚህ ከላይ የዘረዝርኳቸው ችግሮች ባለፉት ሃያ ዓመታት የታዳጊዎች ፕሮጀክት ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሆነዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ካልተቻለ በቀጣይም ውጤታማ ስራ ለመስራት ያስቸግራል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ችግሮች መቅረፍ የፕሮጀክቶቻችን ስልጠናዎችን ውጤታማ እንዲሆኑ መጣር የግድ ነው፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
ስለ ፀሐፊው
የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!