የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከኤልያስ አሕመድ ጋር…

በቅርብ ዓመታት በሊጉ እየታዩ ከሚገኙ ጥሩ የአማካይ መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ኤልያስ አህመድ በዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ላይ እንግዳ ሆኗል።

ብዙዎች ‘ኳስ እግሩ ላይ ታምራለች’ የሚሉለት የዛሬው እንግዳችን ኤልያስ በመዲናችን አዲስ አበባ ተወልዶ አድጓል። በታዳጊነቱም ተወለዶ ባደገበት ልደታ አካባቢ ኳስን መጫወት ጀምሯል። የአስራዎቹን ዕድሜ ሲጀምርም ለአጭር ጊዜ በፕሮጀክት ደረጃ ታቅፎ መሰልጠን የሚችልበትን እድል አግኝቶ ነበር። ነገርግን በቀለም ትምህርቱ እንዲገፋ በሚል እድሉን ሳይጠቀምበት ቀረ። ምንም እንኳን ተጫዋቹ በፕሮጀክት እና አካዳሚ ባይታቀፍም ባለው ልዩ ብቃት በሰፈር እና በትምህርት ቤት ደረጃ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። በመቀጠልም ተጫዋቹ የትውልድ አካባቢው ቀበሌን ወክሎ ሲጫወት የወቅቱ የልደታ ክፍለ ከተማ አሰልጣኝ ብዙዓየሁ በብቃቱ ተማርኮ ወደ ስብስቡ አካቶት በከፍተኛ ዲቪዚዮን ውድድር ላይ መጫወት ያዘ። በክለቡም ለጥቂት ጊዜያት ተጫውቶ ራሱን ካሳደገ በኋላ የልደታ ኒያላን ተቀላቅሎ ግልጋሎት ሰጠ። ከዛም ጉዞውን ወደ ምስራቃዊ የሀገራችን ክፍል በማድረግ ሐረር ሲቲን ተቀላቀለ። ከሐረር ሲቲ የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ 2008 ላይ ሰበታ ከተማ ገባ። በሰበታ ቤት በከፍተኛ ሊጉ ለሁለት ዓመታት ተጫውቶ 2011 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መጫወት የሚችልበትን እድል አግኝቶ ወደ ባህር ዳር ከተማ አቀና። በክለቡም ለአንድ ዓመት ቆይታን ካደረገ በኋላ ዓምና ወደ ጅማ አባጅፋር ተጉዞ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል።

በሁሉም የአማካይ ቦታዎች ላይ መጫወት የሚችለው ይህ ተጫዋች እስካሁን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ጥሪ ባይቀርብለትም ወደፊት ግን ሃገሩን ወክሎ መጫወት እንደሚሻ ይናገራል። በተለይ በቴክኒካዊ ብቃቱ ብዙዎች የሚወዱት ኤልያስ አሕመድ በሶከር ኢትዮጵያ አዝናኝ ጥያቄዎች ቀርበውለት ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥቶናል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

ከሰፈር ጀምሮ እስማኤል አቡበከርን እየተመለከትኩ ነው ያደኩት። እርግጥ በእነሱ ጊዜ በደንብ ደርሼ ባልመለከትም ትንሽ ትንሽ ሰፈር ውስጥ ስለእሱ ሲወራ እሰማ ነበር። እያደኩም ሰፈር ውስጥ ሲጫወት እመለከተው ነበር። በተጨማሪም በእግርኳሱ እንድንቀጥል ይመክረኝ ስለነበረ ለእርሱ ጥሩ ስሜት አለኝ።

ሊጉ በኮቪድ ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ኤልያስ ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው የሚገኘው?

ኮቪድ ሊጉን ካቋረጠው በኋላ ጊዜዬን ቤት ነው የማሳልፈው። እርግጥ ድሮም ከቤት መውጣት ብዙም አልወድም። ግን ይባስ ኮሮና ሲመጣ ከቤት የማልወጣበት ጊዜ ጨመረ። እቤትም ልምምዴን በደንብ እሰራለሁ። ከዚህ ውጪ መጽሐፍት በማንበብ እና ፊልሞችን በማየት ነው ጊዜዬን የማሳልፈው።

ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ የለመድከው ልማድ አለ?

እውነት ለመናገር ብዙም የለም። ግን መጽሐፍትን የማንበብ ልማድ ትንሽ የጨመርኩ ይመስለኛል። በተለይ መንፈሳዊውን የቁርአን ቃል አነባለሁ። ከዚህ መነሻነት ወደ መንፈሳዊ ህይወት የማዘንበል ልማድ አዘውትሬ ይሆናል።

ኮሮና ጠፍቷል ቢባል ኤልያስ መጀመሪያ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?

ይሄ እማ ምን ጥያቄ አለው። እግርኳስ ነው መጀመሪያ የምጫወተው። ኳስ በጣም ናፍቆኛል።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?

በኒያላ የነበረኝ ቆይታ ለእኔ ጥሩ ነበር። ክለቡ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊገባ ጫፍ ደርሶ ነበር። በወላይታ ድቻ በፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈን ነው ወደ ሊጉ ሳናድግ የቀረነው። በዓመቱ አላማችንን ባናሳካም ግን እኔ በግሌ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ።

ኤልያስ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

አሁን ላይ ይህንን ማሰብ ይከብደኛል። ግን እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል። አላቅም ለምን እንደሆነ ግን አሁን አዕምሮዬ ላይ የመጣው መልስ ይህ ነው።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች አለ?

መስዑድ ሲጫወት በጣም ደስ ይለኛል። የእሱ ሁሉ ነገር ይስበኛል። ከዚህ መነሻነት ከመሱዴ ጋር አብሬ ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድህ ተጫዋች ይኖር ይሆን?

እውነት ለመናገር እስካሁን የሚከብደኝ ተጫዋች አላገኘሁም። ግን በአንፃራዊነት ከገጠምኳቸው ውስጥ የማደንቃቸው እና ጎበዝ ተከላካዮች አሉ። እነሱም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ እና የኢትዮጵያ ቡናው ወንድሜነህ ደረጄ ናቸው።

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?

ሳልሃዲን ሰዒድ ለእኔ ምርጡ ተጫዋች ነው። በዚህ አጋጣሚ ሳላን እንደማደንቀው መናገር እፈልጋለሁ።

ቅፅል ስም አለህ?

አይገርምም! እስካሁን ቅፅል ስም አልወጣልኝም። ሁሉም ኤልያስ ወይንም ኤላ እያለ ነው የሚጠራኝ።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አጋራኝ?

በክለብ ደረጃ ብዙም ስኬት የለኝም። ግን ካሳለፍኩት አጭር የእግርኳስ ህይወት ውስጥ በጣም የተደሰትኩት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጫወት ባህር ዳር ከተማ ስገባ ነው። ዝውውሩንም አድርጌ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዬን ሳከናውን በጣም ነበር የተደሰትኩት።

ከየትኛው የሊጉ ክለብ ጋር ስትጋጠም ነው ደስታ የሚሰማህ?

ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር። ማንኛውም ተጫዋች በሃገራችን ከሚገኙት እነዚህ ሁለት ታላላቅ ክለቦች ጋር መጫወት ይፈለጋል። እኔም በተመሳሳይ ከሁለቱ ጋር ስጫወት ደስታ ይሰማኛል።

በእግርኳሱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛህ ማነው?

አብዛኞቹ ጓደኞቼ ከእግርኳስ ውጪ ያሉ ናቸው። ግን በመድን እና ሰበታ አብሮኝ የተጫወተው ኢብራሂም ጥሩ ጓደኛዬ ነው። በተጨማሪም ጅማ አብረውኝ ከተጫወቱት አብርሃም እና ሰዒድ ጋር ቅርበት አለኝ።

እግርኳስ ካቆምክ በኋላ ምን ለመሆን ታስባለህ?

ይህንን ጉዳይ አስቤው አላቅም። ግን አሁን ላይ ወደ ስልጠናው ዓለም ለመግባት አላልምም። ይልቁንም የንግዱን ዓለም የምቀላቀል ይመስለኛል።

የግል ህይወትህ ምን ይመስላል?

ትዳር አልመሰረትኩም። እስካሁን ከቤተሰብ ጋር ነው የምኖረው። ትዳርን እያሰብንበት ነው። ግን በቶሎ የሚሆን አይመስለኝም። ገና በእቅድ ነው የተያዘው።

ኤልያስ ምን የተለየ ባህሪ አለው?

እኔ ዝምተኛ ነኝ። አንዳንድ ሰዎች እንደውም ከናካቴው የማወራ አይመስላቸውም። ዝምተኛ ብሆንም ግን ከቀረብኩት ሰው ጋር በጣም ነው የምግባባው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ