የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ደሞዝን በተመለከተ ውሳኔ ተላልፏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ገደብ ተጥሎበት የነበረውን የተጫዋቾች ደሞዝ አከፋፈል በተመለከተ ውሳኔ አስተላልፏል።

ትናንት እና ዛሬ አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል ያደረገው ይህ አክሲዮን ማኅበር የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አከናውኖ ውሳኔ አስተላልፏል። በጉባዔው ላይም ከተነሱት አጀንዳዎች መካከል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች የደሞዝ ጣሪያን የሚመለከት ይገኝበታል።

እንደሚታወሰው 2010 ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ባልተገኙበት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ እግርኳክ ፌዴሬሽን የክለብ ተወካዮቸን ሰብስበው የተጫዋቾች ደሞዝ ላይ ምክክር አድርገው ነበር። በዚህ ውይይት ላይም ክለቦች ‘ለተጫዋች የምንከፍለው ወርሃዊ ክፍያ ገደብ ይኑረው’ በማለት የተጫዋቾች ደሞዝ ከ50 ሺ እንዳይበልጥ ወስነው ወጥተዋል። ይህንን ተከትሎ የተለያዩ ጥያቄዎች ከጉዳዩ አፈፃፀም ጋር በተገናኘ ሲነሱ ቆይተው በዛሬው ዕለት አክሲዮን ማኅበሩ ጉዳዩ ላይ አዲስ ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም መሰረት በርካታ ክለቦች ‘ከጠረጴዛ ሥር’ የሚባል አከፋፈል በማምጣታቸው እና መንግሥት ማግኘት የሚገባውን የታክስ ክፍያ በአግባቡ ባለማግኘቱ አከፋፈሉ ከ2014 ጀምሮ እንዲቀር ተወስኗል። ይህ በገደብ የነበረው አከፋፈል ቀርቶም ክለቦቹ በአቅማቸው እንዲከፍኩ መብት ይሰጣል ተብሏል። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ግን ክለቦች 2010 ክረምት ወር የተላለፈውን ውሳኔ አክብረው እንዲከፍሉ እና ለ2014 አከፋፈል ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ተጠቁሟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!