ፕሪምየር ሊጉን የሚመሩት የቦርድ አመራሮችን በተመለከተ ገለፃ ተደርጓል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዛሬ 9 ሰዓት በጠራው መግለጫ ላይ ሊጉን የሚመሩት የቦርድ አመራሮችን በተመለከተ የተሰጠውን ውሳኔ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሚወዳደሩበትን ሊግ ራሳቸው ለማስተዳደር ዓምና አክሲዮን ማኅበር አቋቁመው ነበር። በወቅቱ ይህንን ማኅበር እንዲያቋቁሙም 7 አባላት ያሉት የቦርድ አመራሮች ተመርጠው ነበር። ማኅበሩም ትላንት እና ዛሬ በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል ባከናወነው አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቦርድ አመራቶቹን በተመለከተ ውይይት አከናውኗል። ይህንን ተከትሎም በጉባኤው ላይ የተነሱትን ሃሳቦች እና የተላለፉተን ውሳኔዎች የማኅበሩ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል።

“ያኔ 7 ሰዎች ሲመረጡ ማኅበሩን እንዲያቋቁሙ ነበር። ማኅበሩ ሲቋቋም ደግሞ የቦርድ አባላት መታወቅ ስለነበረባቸው የእነዚህ 7 ሰዎች ስም በህጋዊነት እንዲገባ ተደርጓል። በአክሲዮን ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ደግሞ የተመረጡት እና ስማቸው የተላለፈው የቦርድ አመራሮች ለሦስት ዓመታት ማገልገል ይችላሉ። ይህንን ተከትሎም በጉባኤው ላይ ይህ ደንብ ተነስቶ እኛ እንድንቀጥል ነገርግን ከክለብ ስራ ውጪ የሚገኝ አባል ካለ በእርሱ ምትክ ብቻ የማሟያ ምርጫ እንዲደረግ ተወስኖ እኛ እንድንቀጥል ተደርጓል። አንድ አባል ግን በአሁኑ ሰዓት በክለብ ውስጥ ስለማይገኝ በእርሱ ቦታ ብቻ የማሟያ ምርጫ ተከናውኗል። ስለዚህ ያሉት የቦርድ አባላት ለቀጣይ 2 ዓመታት እንዲቀጥሉ ሆኗል።”

የውድድር እና ስነ-ሥርዓት ኮሚቴ ሊቀመንበር ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኮቪድ-19ኝን የዋጀ ደንብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ግለሰቡ አክውም በጉባኤው ላይ ኮቪድ እያለ ውድድሮቸ እንዴት እናድርግ እንዲሁም በየትኛው አማራጭ ውድድሩን አከናውነን ወጪዎችን እንቆጥብ በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት አዘጋጅተው ለጉባኤው እንዳቀረቡ አስረድተዋል። በዚህም 8 የሊግ አካሄድ አማራጮች (Format) ቀርበው እንደነበር ጠቁመዋል። ከቀናቶች በፊት ከጤና ሚኒስቴር እና ከክለብ ላይሰንሲንግ የተወጣጣው ኮሚቴም የውድድር ስፍራዎቸን ገምግሞ እንደነበረ ተናግረው ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሃሳብ መሰረት የውድድር ሜዳዎች እንደሚለዩ ገልፀዋል።

የሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ አማረ ደግሞ በጉባኤው ላይ የቦርድ አመራሮችን ከመምረጥ በተጨማሪ የዓምናውን የስራ አፈፃፀም መገምገማቸውን እና የቀጣይ ዓመት እቅዶች መቅረባቸውን ተናግረዋል። በዚህም ሊጉ ከመቋረጡ በፊት እና ከተቋረጠ በኋላ ማኅበሩ የሰራቸውን ስራዎች ካብራሩ በኋላ በያዝነው 2013 ዓመት ማኅበሩ 29 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማለሙን አስረድተዋል። ስራ አስኪያጁ ጨምረውም የ2012 የውድድር ዓመት ላይ ክፍያ ፈፅመው የነበሩ ክለቦ ያልተጫወቱት የ13ቱ ጨዋታ ተሰልቶ ለቀጣይ ዓመት እንደሚዘዋወርላቸው መግባባታቸውን ገልፀዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ